>

የእዬዬ ፖለቲካ፣ የልመና ተቃውሞ - ጋት አያራምድም...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የእዬዬ ፖለቲካ፣ የልመና ተቃውሞ – ጋት አያራምድም…!!!

አሰፋ ሀይሉ

 
(«መንግሥት የሞቱን መንሥዔ አጣርቶ እንዲያሳውቀን!» የሚል እዬዬአቸውን እያቀለጡት ሳይ አፈርኩ!)
አንዳንዴ የኛ ሀገር ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ነገር ከመጠን በላይ ይገርመኛል፡፡ እና እነሱስ ሥልጣነ መንበር ላይ ቢወጡ አሁን ካለው ገዢ የተሻለ ነገር ማሰብና መሥራት ይችላሉ ወይ? ብዬ በብርቱ እንድጠራጠር ያደርጉኛል፡፡
አሁን በደም በተጨማለቀው መንግሥት ከፖሊስ ኮሚሽነርነት ሥልጣኑ የተሻረን ሰው፣ የሰው-በላውን መንግሥት ምሥጢር እንደሚያወጣ የዛተን ሰው፣ እና ሙሉ ጤንነት ላይ የነበረ ሰው፣ ከሥልጣኑ ከተሻረና ከዛተ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሞቶ ሲገኝ – የሞቱን መንሥዔ ማጣራት ያለበት ማን ነው? የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሳይቀር – «መንግሥት የሞቱን መንሥዔ አጣርቶ እንዲያሳውቀን!» የሚል እዬዬአቸውን እያቀለጡት ሳይ በጣም አፈርኩ፡፡
ሕዝብ በመንግሥት ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እምነት አጥቷል፡፡ የመንግሥት ተቋማት እምነት የሚጣልባቸው አይደሉም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ በደም የተነከሩ፣ ሴረኛና ሕዝብ የሚያውቀውን እውነት በአደባባይ ሙልጭ አድርገው የሚክዱ ሸፍጠኞች መሆናቸውን ከሀገር ውስጥ አልፎ ዓለም ያወቀው ጉድ ሆኗል፡፡ በዚህ ሰው በላና ቀጣፊ መንግሥት ላይ የመጨረሻው ሽራፊ እምነት ሊኖራቸው የማይገባው የተቃዋሚ ፖለቲከኞች – መንግሥትን የተቃወመ ባለሥልጣን ከሥልጣኑ ተሽሮና በጥቂት ቀናት ውስጥ ሞቶ ሲገኝ ምን ማድረግ ነበረባቸው?
– በሙያቸው የታወቁ ገለልተኛ የሞት ምክንያትን የሚመረምሩ የህክምና ባለሙያዎችን ፈልጎ በማግኘት፣ በመቅጠር፣ የሟቹን ቤሰብ አስፈቅዶ፣ እነርሱም የሞቱን መንሥዔ በራሳቸው ገለልተኛ ምርመራ እንዲያረጋግጡ መጠየቅ፣ ያ እንዲሆን በአደባባይ መግለጫ ማውጣት፣
ሟቹ ከመሞቱ በፊት ሞተ ለተባለበት ዓይነት ሰበብ የሚያበቃው የህክምና ታሪክ የነበረው መሆኑንና አለመሆኑን ከቅርቡ ሰዎች፣ ከህክምና ተቋሞች፣ ከግል ሀኪም፣ ከቤተሰብ፣ ወይም ከባልደረቦቹ በማጣራት – የሞቱ መንሥዔ ተፈጥሮአዊ አለመሆኑን የሚያመለክቱ ሁኔታዎች ካሉ ያንን ለሕዝብ ማሳወቅ፣
– የሟቹ የሞት መንሥዔ በገለልተኛ ዕውቅ ሃኪሞች ወይም የህክምና ተቋማት እንዳይጣራ መንግሥት ለመከልከል እንቅስቃሴዎችን ካደረገ፣ ካስፈራራ፣ ከከለከለ፣ ይህ አዳሄዱ ምስጢሩ እንዳይጋለጥበት የተደረገ እንደሚሆን ቀላል ግምት ማሳደር የሚያስችል ነውና – ይህንኑ የወንጀል መሸፋፈን ተግባር ለህዝብ ማጋለጥ፣ ወዘተ ወዘተ ወዘተ.
የተቃዋሚ ፖለቲካው ጎራ – በአባላቱ፣ በደጋፊዎቹ ፣ በገንዘብና ማቴሪያል በሚረዱት የቅርብና የሩቅ ደጋፊዎቹ፣ በዘረጋው ሀገራዊ መዋቅርና ድርጅታዊ ትስስር የተነሳ – እንደዚያ ያሉ ለአንድ የፖለቲካ ተቃዋሚ ሀይል እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ተግባራት ለማከናወን – በእጁ ላይ በቀላሉ ሊያንቀሳቅሳቸው የሚችሉ የመረጃና የሰው ሀይል ስብስቦች አሉት፡፡
እነዚያን ተጠቅሞ የመንግሥትን ሸፍጥ ማጋለጥ፣ በደም የተነከረው መንግሥት ዜጋን እንዳሻው እያረደ መቀጠል እንደማይችል ማሳወቅና አደብ ማስያዝ፣ ሕዝብን በመንግሥት ላይ ጥያቄና ተቃውሞ እንዲያሰማ መገፋፋት፣ ለሕዝብና ለሀገር እውነቱ እንዲታወቅ የተቻለውን ያክል ጥረት ማድረግ፣ የጥረቱ አካል ለመሆን ባለው ሀይል በፍጥነት ተንቀሳቅሶ በሀገራዊ ክስተቶች – ከሕዝብ ሀሜትና ከገዳይ መንግሥት የይስሙላ ማረጋገጫዎች ኋላ እየተከተለ ከመጓዝ ወጥቶ – ከህዝብ ፊት ህዝብን እየመራ የሚጓዝ ንቁ ጎራ ለመሆን የሚችልበት ሰፊ ዕድል ነበረው፡፡
የተቃዋሚው ጎራ ከተሽከርካሪ ወንበር ሳይነቃነቅ ከሚሰጡ ተራ መግለጫዎች ወጥቶ፣ ከገዳይ መንግሥት እጅ አንዳች እውነት ጠብ ይልልኛል ከሚል የተስፈኝነት ልመና ወጥቶ፣ ራሱ በቻለው ተንቀሳቅሶ የተቃውሞ ፖለቲካውን ለመምራት፣ የህዝብን ብሶት ለማሰማት፣ እውነትን ለማጋለጥ፣ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ፣ ከዚህ የተሻለ ብዙ ብዙ ነገር መሥራት ይችል ነበር፡፡
ሕዝብ ያላመነው ገዳይና አፋኝ ሴረኛ መንግሥት ባለበት ሀገር፣ ያንኑ ህዝቡ እምነት ያጣበትን መንግሥት – የሻርከውን አጋልጥሃለሁ ያለህን ባለሥልጣን ገድለኸውም እንደሆን፣ ታሞም እንደሆን፣ እባክህ መርምረህ ሳትዋሽ አሳውቀኝ ብሎ እየየ መግለጫ ማውጣት – እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ በዚህ ተደጋግሞ በሚታይ መሬት ያልረገጠ አካሄድ – የተቃውሞው ጎራ – እልፍ ብሎ ሊራመድ አይችልም!
የተቃውሞው ፖለቲካ ከቢሮ አንበሳነት እልፍ ብሎ መውጣት አለበት! መሬት ረግጦ መቆም አለበት! እስቲ ወደ መሬት እንውረድ፡፡ እስቲ ወደ ህዝባችን እንጠጋ! እስቲ ሰው ተገደሎ ወደተወሰደበት ወደ ሆስፒታሉ አጥር እንጠጋ! እስቲ ወደ ባለሙያዎቹ እንጠጋ! በተፈጠሩ ህዝብን በሚመለከቱ ወቅታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የህዝብ አስተያየትን ሰብስቦ፣ ያንን በሚዲያ ለህዝብ መልሶ ማስተላለፍም እኮ አንድ ራሱን የቻለ ከአፋኙ መንግሥት የተለየ የእውነት አማራጭ መፍጠሪያ መንገድ ነው፡፡ የታሪክ ማህደር ውስጥ የሚኖር ማስረጃና መረጃ አኑሮ ማለፍም ነው፡፡
እንዲሁ ከሩቅ ቁጭ ብሎ ፋሺስትነቱን ካረጋገጠ የቆየን አራጅ መንግሥት እባክህ ሳትዋሽ የሞቱን መንሥዔ አረጋግጠህ ስጠኝ የሚል ፖለቲካ ሩቅ አያስኬድም፡፡ በያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከዚህ የለማኝነት ፖለቲካ ሰብረን ለመውጣት መታገል ያስፈልጋል፡፡ ትናንት ብዙዎች በመርዝ ወይም በሌላ የረቀቀ መንገድ ሳይሆን በተተኮሱ ጥይቶች ተገድለዋል፡፡ ዛሬ እገሌ ይገደላል፡፡ ነገ ስም ያላቸው ሌሎች ይገደላሉ፡፡
ዛሬ ከቢሮአቸው ሆነው በዜጎች ሞት ላይ መግለጫ የሚተይቡ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች ነገ ይህ የሞት ዕጣ እነሱንም ይጎበኛቸዋል፡፡ እና ለሌላ ሰው ብሎ ሳይሆን ለራስም ብሎ፣ ከቢሮ የኮምፒውተር መስተዋት ፊት ወጣ ብሎ፣ ግድያ ወደተፈጠረበት አካባቢ ዝር ማለት ነው ትግልን ከሀሳብ ወደ ምር፣ ከቲዎሪ ወደ ተግባር የሚያሸጋግረው፡፡ ገዳዩን፣ አፋኙን፣ አምካኙን የስልጣን ጅብ በመለመን እውነት አትገኝም፡፡ መቼውኑም እኔ ገድዬአለሁ ሊልህ አይችልም፡፡
ያንን ‹‹ሰልፍ-ፕሩቭን›› አፋኝ አካል፣ እባክህ እውነቱን ሳትውል ሳታደር መርምረህ ንገረኝ፣ ብለህ የእግዚኦታ መለማመኛ መግለጫ ማውጣት ማለት፣ ወይ ከእውነታው ፍጹም ተለይቶ በይሆናል አለም መነሁለል (ማበድ) ነው፡፡ አሊያም የአዛኝ ቂቤ አንጓች ከንፈር መጠጣ ነው፡፡ አንዳንዴ እኮ መናገር ስላለብን ብቻ ከመናገር፣ ዝም ማለትም ራሱን የቻለ ብልህነት ነው፡፡
በዜጋ ሞት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አለመጣር ግብረገብነት የተሞላው ሆኖ ሳለ፣ ከገዳይ እጅ እውነትን አጣርተህ ንገረን ብሎ፣ የራስን ሥራና ኃላፊነት ቸል ብሎ፣ ሀገርንና ህዝብን ለመምራት ያለመቻል ስንፈተ-ፖለቲካ ግን – ሁልጊዜም ለማኝ አድርጎ ያስቀራል፡፡ ከልመና ፖለቲካ እንውጣ! ከቢሮ እንውጣ! ወደ ክስተቶች ጠጋ እንበል! መሬት የረገጠ ተጨባጭ ፖለቲካ እናስኪድ! እውነተኛ ለውጥ፣ በተግባር የሚገለጽ ለውጥ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ ተቃውሞ በተግባር የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ ተቃውሞ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ ትግል በተግባር የሚታይ ትግል ብቻ ነው፡፡
የግድያውን ቁጥር አንድ ተጠርጣሪ – እባክህ አንተው መርምርና – አንተው ንገረኝ ማለት – የክፍለ ዘመኑ ቂልነት ነው፡፡ ይኸው ሃኪም፣ ይኸው ተቋም፣ ይኸው ባለሙያ፣ እነዚህም የሟችን አስከሬን ይመርምሩና ያረጋግጡልን ማለት – በተጨባጭ የሚታይ እውነቱን ለማረጋገጥ የሚደረግ ሙግት ነው፡፡ አንድም ብልህነት ነው፡፡ ሁለትም መሬት ላይ መገኘት ነው፡፡ ሶስትም የሟች ቤተሰቦችና የሟች ቤተሰቦች ብቻ የሚወስኑት የማያንገራግር መብት ነው፡፡
ይህን መሬት ላይ ወርዶ መሞገት፣ እና ለሕዝብ ማሳወቅ የአንድ ተቃዋሚ ጎራ ትልቅ ሀብቱም፣ ግዴታውም፣ እና የተሰለፈበትምና ሊሰለፍለት የሚገባም ቁርጠኛ ዓላማ ነው፡፡ ከሕዝብ ጎን እንቁም! እና ገዳዩን እናውጣ! ከሩቅ ሆነን የልመና እዬዬአችንን ማቅለጥን በመረጥን ቁጥር፣ እውነት ተሸፋፍና ትቀራለች! በልመናችን እየየ ገዳዮችን እያበረታታን ነው! ከውሽልሽልነት ያውጣን የኢትዮጵያ አምላክ!  ከወረቀት ነብርነት ትገላግለን እምቤታችን እግዝዕትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ፡፡ ሌላ ምን እንበል?!
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ ለዘለዓለም በክብር ትኑር! 
Filed in: Amharic