>

አራቱ ጸረ ፋሽስት ወንድማማች አርበኞች! (አቻምየለህ ታምሩ)

አራቱ ጸረ ፋሽስት ወንድማማች አርበኞች!

አቻምየለህ ታምሩ

ከታች የሚታዩት አራት ሰዎች ከግራ ወደቀኝ ደጃዝማች ክፍሌ እንቁ ሥላሴ ፣ ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ፣ ቀኛዝማች ታደሰ እንቁስላሴ እና ደጃዝማች ወርቁ እንቁሥላሴ ይባላሉ። ወንድማማቾቹ  የመርሐቤቴ አማሮች ሲሆኑ አምስቱን  አመታት በሙሉ ፋሽስት ጣሊያንን በዱር በገደል የተፋለሙ የአርበኛ መሪዎች ናቸው። ከወረራው በኋላ አራቱም ወንድማማቾች አገራቸውን በተለያየ ደረጃ አገልግለዋል።
የአራቱ ወንድማማቾች ታላቅ ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ናቸው። ደጃዝማች ፀሐዩን የዚህ ዘመን ወጣት የሚያውቃቸው “የአማራ አንገቱ አንድ ነው” በሚለው ንግግራቸውና በአማራው ላይ የተጋረጠውን የኅልውና አደጋ አስቀድመው በማየታቸው ነው። አርበኛው ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ፋሽስት ጥሊያን ከአገራችን ከተባረረ ከዓመታት በኋላ የተማሩ የአማራ ወጣቶችን  ወደ ቤታቸው ጠርተው በአማራው ላይ የተደቀነውን የኅልውና አደጋ በሚመለከት አወያይተዋቸው ነበር።
ደጃዝማች ፀሐዩ  ወደ ቤታቸው ጋብዘው ካነጋገሯቸው ወጣት የአማራ የተማሩ ሰዎች መካክል በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የወልቃይት ተወላጁ አቶ ብርሀኑ አስረስ አንዱ ነበሩ። አቶ ብርሀኑ አስረስ «የታሕሳስ ግርግርና መዘዙ. . .ማን ይናገር የነበረ. . .» በሚል ርዕስ ባሰናዱት የ1953ቱ ስዒረ መንግሥት ታሪክ መጽሐፋቸው ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ቤታቸው የጠሯቸውን የአማራ ወጣቶች ምሳ ከጋበዟቸው በኋላ ሁሉም ወጣቶች ያልጠበቁትን አስተያየት እንዲህ ሲሉ በጥያቄ መልክ እንዳነሱላቸው ጽፈዋል፤
«እንዳያችሁት ፋሽስት ጥሊያን ፊት ለፊትና በጀሌዎቹ አማካኝነት አገሩ ድረስ ወጥቶ ቤቱን ያቃጠለው፤ የዘረፈው፤የገደለው፤ ባገሩ እንዳይኖር ያሰደደው በብዛት አማራውን ነው። ይህ ጠባሳ በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም። እንደሚመስለኝ ከእንግዲህ በኋላም ማንም ቢመጣም የሚገድለውና ጠላት የሚያደርገው አማራውን ነው፤አማራ ዛሬ ካልተደራጀ ወደፊት የሚገድለው ጠላቱ ብዙ ነው። እናንተ ምን ታስባላችሁ?»
ልብ በሉ! ደጃዝማች ፀሐዩ «ካሁን በኋላም ማንም ቢመጣ የሚገድለው አማራውን ነው!!» ያሉት ከዛሬ ስድሳ ዓመታት በፊት ነበር።  «ካሁን በኋላ ማንም ቢመጣ የሚገድለው አማራውን ነው» ባሉ በአመታት ውስጥ በጥራዝ ነጠቅ የተማሪዎች ንቅናቄ በተቀነቀነው የኢትዮጵያ የግራ ፖለቲካ ምክንያት ላለፉት አርባ ስድስት አመታት የአማራ በደልና መከራ ምድሪቷ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ሆኗል።
ደጃዝማች ፀሐዩ የልማትም ሰው ነበሩ። የጎጃም ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በነበሩ ጊዜ የጠቅላይ ግዛቱ ተወላጅ ነን ይሉ የነበሩት እንደራሴዎች ሊያደርጉ ቀርቶ ሊያስቡ ያልቻሉትን ማድረግ ጠቅላይ ግዛቱን ለማልማት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። የጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ የሆነችውን የደብረ ማርቆስ ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ያሰሩት፣ ዛሬ የከተማው ምልክት ተደርጎ የሚቀርበውን የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን አደባባይ ያስገነቡት፣ በከተማው የተከፈተውን የመጀመሪያውን ባንክ ያስጀመሩት፣ የራስ ኃይሉ ልጅ ደጃዝማች አድማሱ ኃይሉ በ1924 ዓ.ም. ያቃጠለውን የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ቤተ መንግሥት፣ ወዘተ ድንጋይ ሳይቀር እየተሸከሙ ያሰሩት ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ናቸው።
የተቀሩት ሶስት የደጃዝማች ፀሐዩ ወንድሞች ከአርነኝነቱ ዘመን በኋላ በእውቀትና በችሎታቸው እየተመደቡ አገራቸውን በቅንነት አገልግለዋል።
እኒህን አራት አርበኛ ወንድማማች ማን የገደላቸው ይመስላችኋል? ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁስላሴ ደርግ ሊገድል ሲያሳድዳቸው አንድ ጥይት እስክትቀራቸው ድረስ ተዋግተው መጨረሻ ላይ እራሳቸውን ሲያጠፉ ፤ የተቀሩት ሶስት ወንድሞቻቸው ግን የተገደሉት በደርግ ጥይት ነው፡፡ ምን ይሄ ብቻ! ደጃዝማች ፀሐዩ ራሳቸውን ካጠፉ በኋላ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አስከሬናቸው በመርሐቤተና ሰላሌ ገበያ  እንዲጎተት አድርጓል።
እነዚህ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በግፍ የታረዱ አራት የአንድ እናት ልጆች ጥፋት ጀግና አርበኞች መሆናቸው፤ አገር በጠላት ስትወረር ስጋዊ ድካምና ወጣትነት ሳያሸንፋቸው አርበኛ በመሆን በዱር በገደሉ ከጣሊያን ጋር በመዋጋት አገራቸውን ለማገልገል መወሰናቸው ብቻ ነው። ዘላለማዊ ክብር የማይጠፋ ሥራ ሰርተው ላለፉ ጸረ ፋሽስት ጀግኖች ሁሉ ይኹን!
ቡሬ ውስጥ የተጀመረው የመጀመሪያው የአማራ አርበኞች ጸረ ፋሽስት ተጋድሎ
ኢትዮጵያ በጣሊያን ከያዘች በኋላ የመጀመሪያው “የአማራ አርበኞች ጸረ ፋሽስት ተጋድሎ” የተጀመረው ጎጃም ውስጥ ቡሬ ምድር ነው። ይህን ታሪክ የሚነግረን ታዋቂው ጣሊያናዊ  የታሪክ ፕሮፈሰር አልቤርቶ ሰባቺ እ.ኤ.አ. በ1986 ዓ.ም. “Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience” በሚል ባሳተመው መጽሐፉ 3ኛ እትም ገጽ 199 ላይ ነው። ቡሬ ውስጥ የተጀመረው የመጀመሪያው የአማራ አርበኞች ጸረ ፋሽስት ተጋድሎ መሪ ደግሞ ታላቁ አርበኛ ደጃዝማች በቀለ ካሣ ናቸው። ከታች በሚታየው ፎቶ ተቀምጠው የሚታዩት አዛውንት የአማራ አርበኞችን ጸረ ፋሽስት ተጋድሎ በቡሬ ምድር የጀመሩት ታላቁ አርበኛ ደጃዝማች በቀለ ካሣ ናቸው። ዘላለማዊ ክብር የማይጠፋ ሥራ ሰርተው ላለፉ ጸረ ፋሽስት ጀግኖች ሁሉ ይኹን!
Filed in: Amharic