>

ማሾምና ማሸለም ያለበት የሀገርና የወገን ፍቅር በግድያ ያስቀጣል (አምባቸው ደጀኔ- ከወልዲያ)

ማሾምና ማሸለም ያለበት የሀገርና የወገን ፍቅር በግድያ ያስቀጣል!

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


በሌሎች ሀገራት የሚያሸልምና የሚያሾም የሀገርና የሕዝብ ፍቅር እንዳለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያ በግድያ ያስቀጣል፡፡ ይህ ዓይነቱ እንግዳ ጠባይ በግልጽ ከተጣባን 30 ዓመታት አለፉን፡፡ በዚህ ጠባያችን ምክንያትም ሀገራችን ቁልቁል ጉዞዋን እያገባደደች ናት፡፡

በወያኔ ዘመን ስለኢትዮጵያዊነት ማቀንቀንና ኢትዮጵያን ከልብ ማፍቀር በግልጽና በሥውር ለኅልፈተ ሕይወት ይዳርግ እንደነበር ቅዠቱ አሁንም ድረስ የሚያሰቃየን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በሞት መቀጣት ትልቁ ቅጣት ይሁን እንጂ ከዚያ በመለስና አንዳንዴም ባልተናነሰ ሁኔታ ለከፍተኛ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረግ የለት ከለት ገጠመኛችን እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

አሁን ያለው የዚያው የወያኔ ዘመን ቅጣይና በጭካኔው ከወያኔም የከፋው የኦሮሙማ መንግሥት ደግሞ የወጣበትን የወያኔን ሥርዓት ዕጥፍ ድርብ በሚያስከነዳ መልኩ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ባልተለመደ ዐረመኔነት እያጨደ ይገኛል፡፡ አጨዳውን እያጧጧፈ የሚገኘው ደግሞ ከላይም ከታችም ነው፡፡ ከላይ አመራሩን፣ ከታች ሕዝቡን፡፡ በሁለቱም መንገድ በተለይ አማራን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቀን ከሌት እየለፋ ነው፡፡ ለዚህ ዘመቻው ደግሞ አማራንና ኢትዮጵያን እንዲሁም ኦርቶዶክስን የሚጠሉ የውጪ ኃይሎች ከጎኑ ተሰልፈው የሚፈለገውን ስንቅና ትጥቅ የማቀበል፣ የሞራል ድጋፍና መረጃን የማጥፋት ወይ የመደበቅ እገዛ እያደረጉለት ናቸው፡፡ ይህ ቀረሽ የማይባል የጥፋት ዘመቻ!

ወያኔዎች ለሚከተሉት የአፓርታይድ ሥርዓት አደገኛ ነው ብለው የሚያስቡትን አንድ ሰው እንዴት ያጠፉት እንደነበር እነአለማየሁ አቶምሳንና  አየነው ቢተውልኝን በምሣሌነት መጥቀስ ይቻላል – ካስፈለገም ኪሮስ አለማየሁን፣ ኢያሱ በርሔንና ብአዴኖቹን ሙሉዓለምንና ተስፋዬ ጌታቸውን መመረቅ ይቻላል፡፡ ወያኔዎች የአቢይ አህመድን ያህል ባይሆኑም እጅግ ክፉዎች ነበሩ፡፡ ጥንታውያኑ የግሪክ ፈላስፎች “ተማሪ ከመምህሩ ካልበለጠ መማሩ ከንቱ ነው” እንደሚሉት አቢይ አህመድም ጭካኔነትንና ሤረኝነትን ከልጅነቱ ጀምሮ በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ጭምር በመሰልጠኑ ለራሳቸው ለወያኔዎችም አልበጃቸውም እንጂ የሕወሓታውያን ድካም ፍሬ አፍርቷል፡፡ ስለሆነም አቢይ የተባለው ከይሲ ልጃቸው እነሱንም እነሱ ሊያጠፉት የጀመሩትን አማራንም በአንድ ድንጋይ ድራሻቸውን የሚያጠፋ ፍጹም ጨካኝ ልጅ ስለወለዱ ሊኮሩ ይገባቸዋል፡፡ ግን የልጁ ጭካኔ ፈጣሪዎቹንም የማይምር በመሆኑ ወላጆቹን እነአቦይ ስብሃትን ሣየቀር ለጸጸት ሳይዳርጋቸው አልቀረም፡፡

ለማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ለመሆን ከመሞከርህ በፊት ዕድር መግባትህንና ከሰበካ ጉባኤ አባልነት ውዝፍ ዕዳ ነፃ መሆንህን አረጋግጥ! እንዲህ የምልህ ከሰሞነኛ ጉዳዮች ተነስቼ አካሄዳችንን ስገመግም ከዚህ ከአቢይ የግድያ ሤራ የሚያመልጥ አለመኖሩን በመገመት ነው፡፡ ወያኔ በዚህ ዓይነቱ ሥውር ግድያ የተዋጣላት እንደነበረች ሁሉ ይህም ልጃቸው የተጨበጨበለት ገዳይና አስገዳይ ሆኗል፡፡ እርሱ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በኢንጂኔር ስመኘው የጀመረው ግድያ አሁን ላይ አበረ አዳሙ ላይ ደርሷል፡፡ አበረ አዳሙ በርግጥም በተፈጥሯዊ ሞት ተወስዶ ሊሆን ይችላል፡፡ የተፈጥሮ ሞት በግድ ከመሻርና ከመሾም ጋር ሊገናኝ አይችልምና ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ቢከሰት ብዙም አይደንቅም፡፡ ይሁንና የአቢይን ፈለገ-ድርጊት ለሚያጤን የአበረ ድንገተኛ አሟሟት ጥያቄዎችን ማጫሩ አይቀርም – ተዘውትራ እንደምትነገረው አዲስ አባባል ነጥቦችን የማገናኘት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በኔ ዕይታ በተፈጥሮ ማለትም “ዶክተር” ሥዩም ተሾመ አስቀድሞ በሶሻል ሚዲያ እንዳሰራጨው አበረ በልብ ኬዝ የመሞት ዕድሉ 49 መቶኛ ቢሆን ከአማራ እስከአፋር ሁሉንም በተቆጣጠሩት በአቢይ ሠርጎ ገቦች የመገደል ዕድሉ 51 በመቶ ነው፡፡

ይህን ለማለት ያበቃኝ አምባቸው መኮንንና አሣምነው ጽጌ የሞቱበት ሀገርንና ሕዝብን የማስቀደምና ለዚያም ስኬት ሲባል የጀመሩት እንቅስቃሴ በአቢይ ዘንድ ጥርስ አስነክሶባቸው በጭካኔ እንደተመቱ ስለምናስታውስ ይህ አበረም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልብ እየገዛና ወደ ኅሊናው እየተመለሰ መጥቶ ሰው ሰው መሽተት መጀመሩ የመቃብሩን ቁፋሮ እንዳፋጠነበት መገመት አይከብድም፡፡ የቅርብ ጊዜው የአበረ ደብዳቤ ጠንካራ ነው፡፡ አንድ ሞት ብቻ ሳይሆን ብዙ ሞቶችን ሊጋብዝበት የሚያስችል ብርቱ ደብዳቤ ነው የጻፈው – ግን እጅግ የዘገዬ ደብዳቤ፡፡ ስለሆነም የምን የልብ ድካም የምን ስኳርና ኮሌስትሮል – የሞቱ መንስኤ ያው ከአቢይ ራስ አይወርድም ባይ ነኝ፡፡ ብሳሳት ደስ ባለኝ፡፡

አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፤

አቃጥሎ ለብልቦ አንድዶ ፈጃችሁ፡፡  ተብሎ ለአፄ ቴዎድሮስ የተገጠመው አለጊዜው ነበር፡፡ አሁን ነበር ያን ግጥም ገጥሞ በዘፈን ጭምር ማስቀለጽ፡፡ ይህ አቢይ እኮ በኢትዮጵያ የበቀሉ የየዘመናቱ ጨካኝ መሪዎችን ገና በሦስት ዓመታት አገዛዙ በዕጥፍ ድርብ በለጣቸው፡፡

“ማነህ ባለሳምንት ያስጠምድህ በአሥራ ስምንት!” እንላለን የጽዋ ማኅበርተኞች ቀጣዩን ከፋይ ለማነቃቃት፡፡ እኔም “ማነህ ባለሣምንት ያስችልህ እስኪ እስክትሞት የአቢይ ጭዳ ለመሆን የተዘጋጀህ …” ብልስ? ከአንድ ወዳጄ የቅርብ ጊዜ ጽሑፍ አንድ ነገር ልዋስና ልሰናበት፡-

“… ስለሆነም ኦህዲድ ሸኔ ማንንም ለማይምረው ነገር ከሥሩ ሆናችሁ የምታሸረግዱ ብአዴንን መሰል ድንዙዛን አያልቅም እንጂ አማራን ከጨረሰ በኋላ ቀጣይ ዒላማዎች እናንተ መሆናችሁን ተገንዝባችሁ ንስሃ ለመግባትና ከገባችሁበት የሆዳምነት አዙሪትና የእሽክርና አባዜ ለመውጣት ብትሞክሩ የመጀመሪያ ተጠቃሚዎች እናንተና የናንተው ቀጣይ ትውልድ ነው፡፡”

Filed in: Amharic