>
5:18 pm - Thursday June 15, 2620

ታላቁ ጃጋማ ኬሎ—ጸረ ፋሽስቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ምልክት...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ታላቁ ጃጋማ ኬሎ—ጸረ ፋሽስቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ምልክት…!!!

አቻምየለህ ታምሩ

ጀግናው ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም. በጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንቢ ዮብዲ ወረዳ ዮብዶ በሚባል ቦታ የተወለዱ የአምስት ዓመት የኦሮሞ አርበኛ ናቸው። ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ልጅ ቢሆኑም ከሁሉም ጎበዝና ብርቱ ነበሩና አባታቸው የቤተሰቡ አለቃ አደረጓቸው። ስማቸውንም ያገኙት ብርቱ መሆናቸውን አባታቸው በማወቃቸው ገና ሳይወለዱ ለወላጅ እናታቸው ‹‹ጥር 21 ቀን ትወልጃለሽ ስሙንም ጃጋማ ብየዋለሁ›› በማለት ነበር ጃገማ የሚለውን መጠሪያ የሰጧቸው። “ጃገማ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን፤ የአማርኛ ፍቺው ሀይለኛ ማለት ነው። ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ እሲኪወለዱ ድረስ የፈረሳቸውን ስም የሚሰጡት ሁነኛ ልጅ ያላገኙት አባታቸው፤ በልጃቸው በጃገማ ይኮሩ ነበር።
ጀግናው የኦሮሞ ልጅ ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ለአገራቸው ነጻነት ሲሉ ከፋሽስት ጥሊያን ጋር ሲፋለሙ የደሙ፣ ዳር ድንበር ለማስከበር የወደቁ፣ ሕይወታቸውን ሙሉ ለወገናቸው ክብር የገበሩና የቆሰሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው።
ፋሽሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ በወረረበት ዘመን ጀነራል ጀጋማ በ15 ዓመታቸው ሸፈቱ ። በአፍላው የወጣትነት ጊዜያቸው የ3500 አርበኞች አለቃ ነበሩ ። በምዕራብ ሸዋ የነበረውን የፋሽስት ጦር ሰቅዘው የያዙት ጀግናው ጃጋማ ኬሎ፤ አምስት አመት ሙሉ በጀግንነት ሲጋደሉ ከማሸነፍ በቀር አንዴም ቢሆን ተማርከውም ሆነ ተሸንፈው አያውቁም ነበር። በተለያዩ የጦር ውሎዎች ላይ ባደረጉት ተጋድሎ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጀብዱን ከመቀዳጀት ባሻገር፤ በርካታ የጥሊያን የጦር አዝማቾችን ማርከው ለጨካኝ ፋሽስቶች የኢትዮጵያውያንን ርህራሔ አሳይተዋል። የማረኳቸውን በርካታ የጥሊያን ጀኔራሎችም ለእንግሊዝ አስረክበዋል።
ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ከሸዋ እስከ ጅማ በመዝመት « ጃጋማን ጥሩት» እየተባሉ በርካታ አስቸጋሪ የፋሽስት ምሽጎችን ሰብረዋል። ከነደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አርበኞች እስከ መጨረሻው በመምራት ጥሊያንን ቁም ቁምጥ ነስተው ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርገው አስወጥተውታል። ከዚህም ባሻገር ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ወደር የማይገኝላቸው የአገር ባለውለታ ናቸው። ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የስምንቱ ጠቅላይ ግዛቶች የሰራዊት ኃላፊም ነበሩ።
የጀግኖቿን ውለታ ቅርጥፍ አድርጋ የምትበላ አገር ሆና ነው እንጅ፤ ታላቁ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ ከነ ዊንተን ቸርችል እና ቻርለስ ደጎል እኩል ሐውልት የሚቆምላቸው የአፍሪካ ጸረ ፋሽስት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ጀግና ነበሩ። ራሱን እንደ ኦሮሞ መንግሥት የሚቆጥረው የዐቢይ አሕመድ የአፓርታይድ አገዛዝ ግን ጀኔራል ጃገማ ለማረኩት የግብጽና የሶማሊያ አገር በቀል ወኪል ለነበረው ለባንዳው ዋቆ ጉቱ ሐውልትና ፋውንደሽን አቁሞ ማራኪውን ጄኔራል ጃገማን ሲያዋርድ ይውላል።
የበጋው መብረቅ በሚል የሚታወቁት መልከ መልካሙ ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ  ለአገራቸው እንደተቃጠሉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ከአራት ዓመታት በፊት ነው። እኒህ አርበኛ ከአውሮፕላን ሳይቀር ወድቀው ከሞት ጋር ተጋፍተው ለታምር የተረፉ፤ ሆለታ የጦር ትምህርት ቤትና አሜሪካን አገር ድረስ ተጉዘው ዘመናዊ የጦር ትምህርት የተማሩና በሺዎች የሚቆጠሩ ያገራቸውን ልጆች ያስተማሩ አገር ወዳጅ ጀግና ናቸው።
ስመጥሩ ጀግና ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ስለአገራቸው ምን እንደሚያስቡ  በአንድ ወቅት ተጠይቀው ፤ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን ግጥም በማውሳት. . .
አገሬ ኢትዮጵያ ውዲቱ ውዲቱ፣
በሶስቱ ቀለማት የተሸለምሽቱ፣
ላንቺ የማይረዳ ካለ በህይወቱ፣
በረከትሽን ይንሳው እስከ እለተ ሞቱ። ነበር ያሉት።
ከሸዋ እስከ ጅማ ዘምተው በማረኩትና ባሸነፉት ጥሊያን ልክ፤ ምሽግና የመሳሪያ ግምጃ ቤት ሰብረው ተከታዮቻቸውን ባስታጥቁት ቁጥር እንዲህ ተብሎ ይገጠምላቸው ነበር፤ ይህን ፉከራም እሳቸው ራሳቸው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርበው ፎክረዋል፤
ጃጋማ ኬሎ የጦር መድኃኒት፣
አባሮ ገዳይ ግፈኛ ጠላት፤
ገዳይ በልጅነቱ፣
ማርዳው ሳይፈታ ባንገቱ፤
ጃጌ ጃጋማቸው፣
እንደገጠመ የሚፈጃቸው፤
ባባት በናቱ ጋላ፣
ከመውዜሩ ጋር ያለው መሐላ፣
ጠመንጃው አይስቱ አይኑ ተመልካች፣
ነጭ አባራሪ ሠርክ ሳይሰለች፤
ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የማረኩትን ነጭ የጥሊያን ወታደር መቶ ብር  ሸጠዋል። ከእሳቸው መቶ ብር የገዛው  ደግሞ ጥሊያኑን  5000 ብር ሽጦታል። ጄኔራል ጃጋማ ፈረንጅ ወይንም ነጭ የሸጡ ብቸኛው ጥቁር አፍሪካዊ ጀግና ይመስሉኛል።
ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የሚያህል ወደር የለሽ ኢትዮጵያዊ አርበኛ የከሀዲ ጥርቅም ሁሉ  ሊያሳንሳቸው ቢሞክሩም ታሪክና ትውልድ ግን ውለታቸውን ሲዘክር ዝንታለም ይኖራል። ክብር ለአገራዊ ቅርሳችን ለጀግናው ሌፍተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ!
Filed in: Amharic