>

የጦስ ዶሮ ፍለጋ ...! !!  (ዘመድኩን በቀለ)

የጦስ ዶሮ ፍለጋ …! !! 

ዘመድኩን በቀለ

በዓለም ላይ ያሉ አብዛኛዎቹ መንግሥታት በሙሉ የጦስ ዶሮ አላቸው። የሚከሱት… በከሰሱት የጦስ ዶሮ ስም ተቀናቃኞቻቸውን የሚያስሩበት… የሚያስወግዱበት የጦስ ዶሮ አላቸው። አንዳንዶቹ ራሳቸው የጦስ ዶሮ ይፈበርኩና አርብተው አራብተው ሲያበቁ በራቡት የጦስ ዶሮ መልሰው ኋላላይ ፍዳ መከራቸውን ይበላሉ። 
… ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚባል የጦስ ዶሮ አዘጋጁ። ኢሱ የጦስ ዶሮው በኢትዮጵያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ ሥልጠና ሲሰጠው ቆየ። ሥልጠናውን ሲጨርስም የጦስ ዶሮው በኢትዮጵያ ፓስፖርት ወደ ሱዳን አቀና። ከዚያም ወደ ኤርትራ በረሃ አመራ። ጀብሃን ተቀላቀለ። ጀብሃም ሳያውቀው ለከፍተኛ ሥልጠና ወደ ቻይና ላከው። በዚያም ቆይቶ ሲመለስ የጦስ ዶሮው ኢሱጭሱ ጀብሃን ድራሽ አባቱን አጥፍቶ ሻአቢያን አቋቋመ። የጦስ ዶሮው ኢሱ ተልዕኮውን ሲፈጽም ለንጉሠ ነገሥቱ መልዕክት ላከ። ” ሥራዬን ጨርሻለሁ፣ ተልዕኮዬን ፈጽሜያለሁ፣ የበረሃም ኑሮ ስለመረረኝ ወደ ሰላማዊ ኑሮዬ ልመለስ ይፍቀዱልኝ” ብሎ ተማጸነ። በልበል አልሰማህም፣ በዚያው ሁን። የሚፈጠረው አይታወቅምና ከዚያው ቆይ የሚል መልስን ከጃንሆይ አገኘ።
… የጨነቀው የጦስ ዶሮ ኢሱ የሚያደርገው ግራገብቶት ሳለ የቃኘው ሻለቃ አማሪካኖቹ አገኙት። ለእነሱም አማከራቸው። ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ እንደሚፈልግ እና ወደ ንጉሡ ሽምግልና እንዲሄዱለት አማከራቸው አሉ። አማሪካኖቹም ለምን? አሉት። ለምን ብለህ በእጅህ የገባውን ዕድል አሳልፈህ ትሰጣለህ? ሽማግሌም አትላክ፣ ንጉሡንም አትለማመጥ። እኛ እንረዳሃለን። የሚረዱህንም ዓረቦች እናዘጋጃለን። ኤርትራን ገንጥል። የዕድሜ ልክ መሪም ትሆናለህ። እስክትሞት ኤርትራ የአንተ የግል ንብረት ትሆናለች። እኛም አንቃወምህም። የሚቃወምህም እንዳይኖር እናደርጋለን። “ፕሮሚስ” አሉት። በግድ ቅር እያለው ተስማማ። የጦስ ዶሮነቱን መረጠ።
… ደርግ ሲመጣ ኢሱ ለደርግ ዋነኛ የጦስ ዶሮው ነበረ። ኢሃፓም የጭዳ በጉ ነበረ። ስንቱ ምሑር ታረደ? ኢምፔሪያሊዝም፣ ፊውዳሊዝም፣ ሸኣቢያ፣ ወራሪው ሱማሌ፣ ኦነግ፣ ወያኔ፣ ኢዲዩ፣ ኢህአፓ፣ የአረብ ቅጥረኞች… ወዘተረፈ ለደርግ የጦስ ዶሮዎቹ ነበሩ። ሱዳን ኤርትራን ለመገንጠል ስትደግፍ ደርግም ደቡብ ሱዳንን የሚገነጥል የጆንጋራንግን ቡድን ደገፈ። ሱዳን ኤርትራን ስታስገነጥል፣ ደርግና ህወሓት ደቡብ ሱዳንን አስገነጠሉ። ሶማሊያ እነ ኦነግ ሸአቢያን ስትረዳ ኢትዮጵያም ሶማሊያን መቶ ቦታ ሸነሸናት። ህወሓትም ከረፈደ የደርግን መንገድ ነበር የተከተለችው። በእነዚህ የጦስ ዶሮዎች ስም ደርግ የጠላውን ሁሉ ነፃ እርምጃ ይወስድበት ነበር። ይረሽናል፣ ይዘርፋል፣ ይገድላል። የጦስ ዶሮ ነገር።
… ህወሓት መሩ ኢህአዴግ መጣ። መጀመሪያ አካባቢ የጦስ ዶሮው ደርግ ብቻ ነበር። በደርግ ስም ህዝቤን ፈጀው። ኋላ ላይ ብዙም ሳይቆይ የደርግ የጦስ ዶሮነት አላዋጣ ሲለው ኦነግን ሱሪውን አውልቆ በሳማ ከገረፈው በኋላ ኦነግ ፈርጥጦ ከሃገር እንዲወጣ አድርጎ የጦስ ዶሮ አደረገው። አልኢትሃድን ሶደሬ ላይ መስርቶ የጦስ ዶሮ አድርጎ ወደ ሶማሊያ ላከው። በዚያም እነ አልሸባብ ተፈጠሩለት። በምሥራቅ አልኢትሃድ፣ ኦብነግ። በኦሮሚያ ኦነግ የጦስ ዶሮዎቹ ሆኑለት። በሰሜን ፈልጎ ሲያጣ ከትልቁ የጦስ ዶሮ፣ ከፈጣሪውና ጃንሆይ ካቋቋሙት ከሻአቢያ ጋር ተላተመ። የጦስ ዶሮም አደረገው። ዐማራው ቀረው፣ ደቡብም የጦስ ዶሮ አስፈለገው። ቅንጅትን አፈረሰው። በቅንጅት ስም የጦስ ዶሮ አድርጎ በዙዎችን አስወገደ። ቅንጅቱ ግንቦት ሰባት ነኝ ብሎ ዋናው የጦስ ዶሮው ሸአቢያ ጋር ሄደለት። ለህወሓት ሰርግና ምላሽ ሆነላት። መላ ዐማራውን፣ ደቡቡን ግንቦቴ ናችሁ እያለች ወደ ወኅኒ ታግዛቸው ጀመር። የግብጽ ተላላኪ፣ የሸአቢያ ተላላኪ፣ የሃገር ከሃዲው የግንቦት ሰባት አባል እየተባለ ፒፕሉ ፍዳውን ይበላ ጀመር። ኋላ ላይ ህወሓት ተነነች። እሷም ጁንታ ተብላ በተራዋ የጦስ ዶሮ ሆነች።
… ኃይለማርያም በህወሓት መንገድ ዊኒጥ ዊኒጥ ለማለት ሞክሮ ሳይሳካለት ቀረ። ዐቢይ አሕመድ በሥፍራው ተተካ። ዐቢይ ህወሓት አምጣ በኦህዴድ ማኅጸን ተከራይታ የወለደችው ልጇ ነው። ኦነግ ወላጅ አባቱም ነው። ሻአቢያም ወዳጁ ነው። ምስጢረኛው። ታስታውሱ እንደሆነ ዐቢይ የሬድዮ ኦፕሬተር ሆኖ በሰሜኑ ግንባር ሲሠራ ሳለ በባድመ ግንባር ” እኔ እና የጦር ጓደኞቼ አብረን ቁጭ ብለን ነበር። ቆይቼ ወደ ቁጥቋጦ ዞር ብዬ ስመለስ እኔና ጓደኞቼ በነበርንበት ቦታ ላይ ከሻአቢያ ተተኩሶ ጓደኞቼ በሙሉ አለቁ። ሥጋቸው ብጥስጥስ ብሎ ነበር የደረስኩት” ነበር ያለን። ይሄን የሚለው የሬድዮ ኦፕሬተሩ ዐቢይ አሕመድ ነው። ለሻአቢያ ምን የሚል መልእክት ቢልክላት ነው እሱ ዞር ሲል ጠብቃ የምትተኩሰው። ይሄን ጊዜ ያወጣዋል።
… ዐቢይ ሥልጣን ያዘ። አማሪካም ካለ ዐቢይ ሞቼነው ቆሜ ብላ ሄጵ አለች። አቢቹ ታዲያ የጦስ ዶሮዎቹን በሙሉ ፈትቶ ለቀቃቸው። ሸኣቢያን አዲስ አበባ አመንሸነሸው፣ ደቡብ፣ ዐማራ ኦሮሚያ ጭኮ፣ ገንፎና ዶሮወጡን ከጨጨብሳ ጋር እንደጉድ ሲጋበዙት ከረሙ። ለኢትዮጵያ ገዢዎች ትልቁ የጦስ ዶሮ የነበረው ሸኣቢያ እና መሥራቹ አይተ ኢሳይያስ የኢትዮጵያ ሞግዚት፣ የአቢቹ አሳዳጊ ሆነው ተመደቡ። አቢቹም ለውለታው አስመራና ምጽዋ ሲምነሸነሽ ከረመ።
… ግብጽ የጦስ ዶሮ ነበረች። ዐቢይ ካይሮ ድረስ ሄዶ ወላሂ፣ ወላሂ፣ ወላሂ ብሎ ምሎ ወዳጁ አደረጋት። ሱዳንም ወዳጅ ሆነች። ሶማሌም ወዳጅ ሆኑት። የጦስ ዶሮ ጠፋ። በሙሉ በስብከትም በብልጠትም የጦስ ዶሮዎቹን አስወገደ። ሸኣቢያም የኢትዮጵያ የጦስ ዶሮ የነበሩትንና በጉያው አቅፎ ሲቀልባቸው የነበሩትን በሙሉ ጦሴን ጥንቡሳሴን ይዛችሁ ውጡልኝ። ድራሽ አባታችሁ ይጥፋ እዚያው ሄዳችሁ እንደፍጥርጥራችሁ ብሎ ወደ ኢትዮጵያ መለሰ። የቤኒሻንጉል ጉምዝ ነጻ አውጪ እና ኦነግ ከነ ሙሉ ትጥቃቸው እንዲገቡም ተደረገ። የትግራዩ በትግራይ ገባ። የዐማራ ኃይልና አርበኞች ግንቦት ሰባት ባዶ እጃቸውን እያጨበጨቡ ወደ አዲስ አበባ ገቡ። ዐቢይ የጦስ ዶሮ አጣ። በገዛ እጁ የጦስ ዶሮዎቹን አጣ።
… ቆይቶ አቢቹ… አሰበ፣ አሰበ፣ አሰበና ያለ ጦስ ዶሮ ሃገር መምራት እንደማይቻል ተረዳ። እናም የጦስ ዶሮ ፍለጋ ይኳትን ገባ። ጃንሆይ ሸኣቢያን እንደመሰረቱት ሁሉ እሱም መቼም ኩረጃ አንደኛ ነውና ሸኣቢያ የሚለውን ስም ወስዶ #ሸኔ የሚል የጦስ ዶሮ መሰረተ። ፈጠረም። ኦነግ ሸኔም ይሉታል። ኦነግ ሄጵ ሲል ኦነግ የሚለውን አውጥተው ሸኔ ብቻ ብለው ይጠሩት ጀመር። ከትግራይ ህወሓት የጦስ ዶሮ ሆነች። ስሟም ጁንታ ተባለ። በኦነግ ሸኔ ስም እነ ጃዋር ተወገዱ። የጦስ ዶሮ ጥቅሙ ታወቀው። ጣፈጠውም። ከመሃል ሃገር ባልደራስ ለጦስ ዶሮነት ታጨ። ድርጅቱ ለሰበብ ብቁ ባይሆንም መሪው እስክንድር ነጋ ለጃዋር ማጀቢያ ለኦሮሞዎች ማስተንፈሻ ተደርጎ የጦስ ዶሮ ሆነ። እንደምንም ብሎ የጦስ ዶሮዎችን ፈጠረ።
… ጭራሽ ይባስ ብሎ የኋትስአፕ ግሩፖችን፣ ሕጋዊ ማኅበራት ሁሉ በአሸባሪ ስም ለጦስ ዶሮነት ተዘጋጁ። አሁን ዐብን ብቻ ነው የቀረው። ዐብን ቢገለብጠው፣ ቢያሰጣው፣ ቢጨምቀው ለጦስ ዶሮነት አልመች አለው። በዚያ ላይ ብአዴንም አለ። ሂኢ… የጁንታ ተላላኪ፣ የግብጽ ቅጥረኛ፣ የሱዳን ጉዳይ አስፈጻሚ፣ ተልዕኮ ፈጻሚ፣ አረመኔው ሸኔ የሚሉ ታፔላዎች አሁን የዐቢይ አሕመድ የጦስ ዶሮ ስሞች ናቸው።
… መፍትሄው የጦስ ዶሮ ማዘጋጀት አይደለም። መፍትሄው ሰላምና ዲሞክራሲን ማስፈን። የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማቆም። መፍትሄው ብሔራዊ ስምምነትን ማስፈን፣ ብሔራዊ ዕርቅን መፍጠር። መፍትሄው የሕግ የበላይነትን ማስፈን፣ ተረኝነትን ማስወገድ። እሱ ብቻ ነው መፍትሄው። አትግደሉኝ፣ ዘራችንን አታጥፉን፣ አትረሽኑን፣ አታፈናቅሉን፣ አትዝረፉን የሚሉ ሰላማዊ ፍትህ ጠያቂዎችን በሙሉ የጦስ ዶሮ ማድረግ መፍትሄ አይሆንም። ገዳይን እየተንከባከቡ ሟችን ማሸማቀቅ መፍትሄ አይሆንም።
… የተራበ፣ የተጠማ፣ ፍትሕ የራቀው፣ በገዛ ሃገሩ የመኖር ዋስትና ያጣ ህዝብ መንግሥቱን ይበላል። መንግሥት ህዝብን አያሸንፍም። ሚልዮን ሚሳኤል፣ ሺ ፈንጂ ቢኖርህ ህዝብን የምትገዛው በፍቅርና በሕግ ብቻ ነው። የኋትስአፕ ግሩፕ ውስጥ ተዘፍዝፈህ እየዋልክ አሸባሪ ምንትስዮ፣ ቅብጥርስዮ ብትል አያዋጣም። የሚያዋጣው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መመሥረት ብቻ ነው። የጦስ ዶሮ ጥቂት ጊዜ ዊኒጥ ዊኒጥ ቢያደርግህ እንጂ አያዛልቅህም። የጦስ ዶሮ ተጠቃሚ ከነበሩት ጃንሆይ፣ ደርግ፣ መለስና ኃይልሻ መማር ነው። ለእነሱም አላዋጣም። የአጣዬን ህዝብ አሁን አትቃወመኝ ብትለው አይሰማህም። እግሩ ላይ ጩቤ ሰክተህ ጉንጩን እያሻሸህ ብታባብለው አይሰማህም።
… ጦሴ ሰምተሃል  !!
Filed in: Amharic