>

የኢህአዴግ የስለላ መረብ !  (በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ  የተዘጋጀ  ጥናት)

የኢህአዴግ የስለላ መረብ !

 በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ  የተዘጋጀ  ጥናት

 

ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት (ብመደአ)እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) – ከውስጥ አዋቂዎች የተገኘ ግርድፍ መረጃ!!

ኢትዮጵያን በተለያዩ አቅጣጫዎች በማፈን በቁጥጥር መዳፉ ውስጥ አስገብቶ እየገዛ የሚገኘው ኢህአዴግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፈና ሥራውን ከማጠናከር አልፎ ዘመናዊ ወደ ማድረግ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ ለዚህም ተግባሩ በዋንኛነት እየተጠቀመበት ያለው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት (ብመደአ) በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS (National Intelligence and Security Service) የሚባለውን መስሪያቤትና፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ወይም በእንግሊዝኛው (Information Network Security Agency (INSA – ኢንሳ)) በመባል የሚታወቀውን ድርጅት ነው፡፡
እንደ መረጃ ምንጭነት የሚጠቀመው ደግሞ በአዲስ መልክ እየተዋቀረ የሚገኘውን ‹‹ኢትዮ ቴሌኮም››ን ወይም በቀድሞ ስሙ የሚታወቀውን የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽንን ነው፡፡ አገዛዙ እስካሁን ድረስ ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ በእነዚህም መስሪያ ቤቶች ለይስሙላ የተሾሙ “ባለሥልጣኖች” ቢኖሩም ዋናውን ሥራ የሚያካሂደው በየቦታው በሰገሰጋቸው ታማኞቹ ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ዋናው የስለላ መ/ቤት (NISS) ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ/ኢንሳ) በመረጃ መረብ ውስጥ የሚያልፉትን ማናቸውንም ጉዳዮች እየተቆጣጠረና እየተከታተለ ለዋናው የስለላና ደኅንነት መ/ቤት የሚያቀርብ፣ መገናኛዎችን የሚያግት፣ የቴሌኮም አገልግሎቶችን የሚጠልፍ፣ እና የሚተነትን ተቋም ነው።
 የዚህ ጽሁፍም ዋና ዓላማ ኢህአዴግ ይህንን ተቋም በመጠቀምና ሥራውን በአዲስ መልክ እያዋቀረ ካለው ኢትዮ ቴሌኮም ወይም ‹‹አዲሱ ቴሌ›› ጋር በማቆራኘት በአገራችን ሕዝብ ላይ እየዘረጋ ያለውን የስለላ መረብ የሚመለከት ይሆናል።
በተከታታይ ያለማቋረጥ አፈናና እንግልት ሲደርስበት የነበረው የግሉ ፕሬስ እንዲሁም በርካታ ከጉዳዩ ጋር አግባብ ያላቸው ባለሙያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሲጽፉና ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ …መጨረሻ ላይ ግን የተፈራው ሁሉ ደረሰ።
ቴሌ አገልግሎቱ መረጃ መሰብሰብ ሆነ። ሰዎች ገንዘባቸውን ከፍለው ከቴሌ የሚገዙት አገልግሎት በራሳቸው ላይ ጠላት የመግዛት ያህል ሆነ። በመሆኑም “አዲሱ ቴሌ” ይህንን የጀርባ ስለላ የሚያከናውንበት በቂ መንገድ ተመቻችቶ በአሁኑ ጊዜ ወደ ተግባር እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
ከዚህ በታች ከአዲሱ ቴሌ ጋር በቴክኖሎጂ እንዲተሳሰሩ የተደረጉትን የብሔራዊ ደህንነትና የኢንሳ መ/ቤቶች አሠራርና በዜጎች ላይ የሚፈጽሟቸውን የአፈናና ስለላ ተግባራት በየተራ በማሳየት፣ በመጨረሻም ዜጎች ከእነዚህ ድርጅቶች አፈና ራሳቸውን ለመጠበቅ ማድረግ ስለሚችሏቸው ቀላላል የጥንቃቄ ምክረ ሀሳቦችን እንለግሳለን፡፡
1ኛ/ ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት (NISS)
በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS (National Intelligence and Security Service) በመባል የሚታወቀው የስለላ መ/ቤት በድርጅታዊ አወቃቀር፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኒክ ብቃት፣ በገንዘብ፣ ወዘተ. በኢትዮጵያ ካሉት መ/ቤቶች በላቀ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ቁጥጥር ሥር ሆኖ የኖረ መ/ቤት አገዛዙ ለሥልጣኑ የሚያሰጉትን በሙሉ በማደን፣ በማሰስና በቁጥጥር ሥር በማዋል በአጠቃላይ በህወሀቶች ለሚዘወረው ጎሰኛ ሥርዓት የህልውና ስጋት የሆነን ሁሉ ከመንገድ የሚያስወግድ ኃይል ነው፡፡
ይህ የስለላና የደኅንነት መዋቅር በበላይነት የሚመራው በብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ሲሆን የምክር ቤቱ ዋና አባላትና ኃላፊዎችም ከገዢው ፓርቲ ከኢህአዴግ የተመረጡ ግለሰቦች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለምሳሌ የደህንነት ምክርቤቱ አባላት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (መለስ ዜናዊ)፣ የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ (ኃይለማሪያም ደሳለኝ)፣ የጠ/ሚ/ሩ ቢሮ ዋና ኃላፊ (ሙክታር ከድር)፣ የመከላከያ ሠራዊት ዋና ኃላፊ (ሲራጅ ፈጌሳ)፣ የፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኃላፊ (ወርቅነህ ገበየሁ)፣ የፌዴራል ጉዳዮች ዋና ኃላፊ (ሽፈራው ተክለማርያም) እና የራሱ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና (ጌታቸው አሰፋ) ኃላፊ በጥምረት በመሆን የሚሠሩበት ነው፡፡
ከ1989 ዓም ጀምሮ የስለላና የደኅንነት መ/ቤቱ (NISS) ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የፈሰሰበት የመዋቅርና የአሠራር ለውጥ እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን በተለይም በሥሩ የሚገኙትን ሁሉንም መምሪያዎች በኮምፒውተር በታገዘ ቴክኖሎጂ አዋቅሯል፡፡ በመሆኑም ካለፈው የኮ/ል መንግሥቱ አገዛዝ የተረከባቸውን የደኅንነት ፋይሎችን (መረጃዎችን) በአዲስ የደኅንነት መረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) ውስጥ አከማችቷል፡፡
ይህ የመረጃ ቋት ዋናው ዓላማ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የግል ማኅደር መሰብሰብ ሲሆን፣ በተለይም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ አገዛዙን ይቃወማሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን መረጃ የመሰብሰቡ ሂደት ዋንኛ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡
በአወቃቀር ደረጃ ይህ የስለላ መ/ቤት በሦስት መምሪያዎች የተከፋፈለ ነው፡፡ እነርሱም፡-
 የመጀመሪያው የደኅንነትንና የመረጃ (ስለላ) መምሪያ፣
 ሁለተኛው የድንበር ቁጥጥር መምሪያና
 ሦስተኛው የጸረ-አሸባሪነት መምሪያ ናቸው፡፡ (በዚህ መምሪያ ውስጥ እስላማዊ አክራሪነትን የሚከታተል የምስጢር መምሪያ የሚገኝ ሲሆን መምሪያው በፌዴራል ፖሊስና በክልል ፖሊስ አመራሮችና አስተዳደሮች ተዋቅሮ በአቶ ሃሰን ሺፋ ዋና ኃላፊነት የሚመራ ነው።)
አራተኛ ደረጃ ባይባልም በየቀኑ የሚተነፈሱትንና አዲስ የሚባሉትን መረጃዎች ከታች በመሰብሰብ ሪፖርት የሚያቀርቡ የበታች ተዘዋዋሪ፣ በቁጥር 2,400 የሚጠጉ እግረኛ ቃፊሮች አሉ። ባለስልጣናትንና ነጋዴዎችን የንግድ አጋርና የጥቅም ሸሪክ በማድረግ የሚመርዙትን ጨምሮ፣ በዋናነት አየሩንና የመረጃ ድሮችን በሙሉ የሚከታተለው ተቋም ኢህአዴግ የስለላና የአፈና አገዛዝ የጀርባ አጥንት ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱት ሦስት መምሪያዎች በሥራቸው የተለያዩ ንዑሳን መምሪያዎችና ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
 የአገር ውስጥ ደኅንነት ዋና መምሪያ፣
 የውጭ ደኅንነት ዋና መምሪያ፣
 የቴክኒክ አገልግሎት ዋና መምሪያ (ይህ መምሪያ ከኢንሳ ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን ዋና ተግባሩም የመረጃ መረብን መቆጣጠርና መከታተል ነው)፣
 የምልመላና ሥልጠና መምሪያ፣
 የቴክኒክ መረጃ ዋና መምሪያ (ይህ መምሪያ በውጭ ሀገራት በተለያዩ ቦታዎች የደኅንነት ሰዎች ያሉት ሲሆን፣ ዋና ተግባራቸውም ለደኅንነትና ለስለላ ተግባር የሚውሉ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ማፈላለግና መግዛት ነው)፣
 የደኅንነት ዋና መምሪያ፣
 የኢሚግሬሽንና የዜግነት ዋና መምሪያ፣
 የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ባለስልጣን፣ እና
 የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) – ይህ መ/ቤት በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ሲሆን ቴሌኮሙኒኬሽንን ጨምሮ ከሌሎች የመረጃ ተቋማት ጋር በመተባበር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስክ ስለላ የሚያደርግ ዋነኛ ተቋም ነው)፡፡
ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የስለላ መ/ቤቱ ዋነኛ መምሪያዎች ሲሆኑ፣ በተለይም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ – ኢንሳ – መረጃንና የመረጃ መረብን በተመለከተ ብቃት ያለውና ጥራቱን የጠበቀ መ/ቤት ሲሆን የአገሪቱን ልማት አውታሮች መጠበቅና ከጉዳት መከላከል ዋነኛ አገልግሎቱ ነው፡፡
ይህ ከውጪ የሚጠቀስለት ተግባር ሲሆን፣ ሌላኛው የኢንሳ ተግባር የመረጃ መረብ ደኅንነትን በተመለከተ የጥናት ማዕከል ሆኖ ማገልገል፣ በተለይም ከቴሌና ከሌሎች መ/ቤቶች በሚያገኘው መረጃ የስለላ መ/ቤቱን (NISS) እስኪበቃው በመረጃ በማጥገብ የህወሃት/ኢህአዴግን ጥቅም በማስጠበቅ የአገዛዙን ዕድሜ ከአደጋ መታደግ ነው፡፡
የስለላ መ/ቤቱ ከኢንሳ ከሚያገኘው መረጃ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች፣ በግልና በህዝብ ህንጻዎች፣ በትራፊክ መብራቶች ወዘተ ላይ የደኅንነት ካሜራዎችን በመትከል የዋና ከተማዋን ሕዝብ እንቅስቃሴ መከታተል ሌላኛው ተግባሩ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ንዑሳን መምሪያዎችና ክፍሎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍሎች አገዛዙ በሚያስቀምጠው የቅደም ተከተል መዘርዝር መሠረት መረጃ የሚሰበስብና የሚተነትን የስጋት ትንተና (threat analysis) ክፍል ያላቸው ሲሆን እነዚህ ክፍሎች በሙያው በተካኑ ሠራተኞች የተሞሉ ናቸው፡፡
ህወሃት የዚህን መ/ቤት አመራር መጀመሪያ ላይ ለአቶ መለስ በጣም ቅርብ ለነበሩት አቶ ክንፈ ገ/መድኅን ነበር የሰጠው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ የስለላና የደኅንነት መስሪያ ቤት የሚመራው በሚኒስትር ማዕረግ ሲሆን ዋና ኃላፊው ግማሽ ኤርትራዊ የሆኑት አቶ ኢሣያስ ወልደጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ሀገር የሚያውቃቸውና አቶ ክንፈ ገ/መድህንን የተኩት አቶ ጌታቸው አሰፋ የመረጃና ደህንነት መ/ቤቱ እውነተኛው መሪ አልነበሩም፡፡
/እንደሚታወቀው፣ ቆይቶ በሚኒስትር ማዕረግ የደህንነቱ መ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾመዋል፡፡/
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ SMNE በ2004 የተዘጋጀ  ጥናት
…/ ክፍል-2 ይቀጥላል
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ!
ስዕል 1. ኮ/ሎ ተስፋዬ ወልደሥላሴን የተኩት የቀድሞው የደኅንነት ኃላፊ አቶ ክንፈ ገብረመድኅን
ስዕል 2. ከብ/ጄ ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው በመሆን ኢንሳን የመሩት ኮ/ል አብዮት አህመድ
Filed in: Amharic