>

የትግራይ ቤተ ክህነት? (ጌጥዬ ያለው)  

የትግራይ ቤተ ክህነት?

ጌጥዬ ያለው
‹አግርር ፀረ ዕቀብ ሕዝበ ወሰራዊት ለሀገሪትነ ትግራይ. . . › ይህ ሰሞነኛው የወያኔ ካህናት ፀሎተ ቅዳሴ ነው፡፡ ትርጓሜውም ‹ለሀገራችን ትግራይ ሰላሟን ስጣት፤ ሕዝቧን ሰራዊቷን ጠብቅልን› እንደ ማለት ነው፡፡ እነኝህ የሃይማኖት አባቶች ለአገልግሎት የበቁትም ሆነ አገልግሎት የሚሰጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስር ቢሆንም ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ትግራይ በሚሏት ምናባዊ ሽራፊ ሀገር ስም አድርገውታል፡፡ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ እና በአሜሪካ አሕጉረ ስብከቶች እና ሀገረ ስብከቶች በየደረጃው የሚያገለግልሉ አባቶች አገልግሎት አሰጣጣቸውን ሁሉ ወደ ትግርኛ እየቀየሩት ይገኛል፡፡ በርግጥ ይህ ከትግራይ ተወላጆች ውጭ ያሉትን አይመለከትም፡፡ በተለይ አማርኛን ቤተ መቅድስ ውስጥ እንዳይገባ አውግዘውታል፡፡ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በአሜሪካ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ ይህ ገጥሞታል፡፡ በሰሜን አሜሪካ እናት ቤተ ክተርስቲያን የማታውቀው ‹ማሕበረ ካሕናት ዘትግራይ አሜሪካ› የሚባል ቡድን ተመስርቶ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ በአማርኛው የትግራይ አሜሪካ የካሕናት ማሕበር ማለት ነው፡፡ ስያሜው ኢትዮጵያን የገደፈ ወይም የካደ ከመሆኑ በተጨማሪ ሳያውቁት ይሁን ወይም ሆነ ብለው አሜሪካንም እንደ ኢትዮጵያ በጎሳ ለመሸንሸን የዳዳው ይመስላል፡፡ ‹United States›  ከሚለው የአንድነትና የሕብረት ስሪት የተቀዳ አይደለም፡፡ ‹ክልሎች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ አባል ቢሆኑም በፈለጉ ጊዜ መውጣት ይችላሉ› ከሚለው ወያኔያዊ አስተሳሰብ የተቀዳ እንደሆነ ያስጠረጥራል፡፡ ምክንያቱም የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች እንጂ የትግራይ አሜሪካ፣ የገለመሌ አሜሪካ የሚባል የለም፡፡ ሁሉም በሕብረት እኩል ይኖራል፡፡ ለዚህም ነው ከወያኔ የ‹ክልልነት› እሳቤ የመነጨ ነው የምለው፡፡ ሜክሲኳውያንን በግንብ አጥር ያገለለው ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ቢሰማ ምን ያደርግ ይሆን?  የሆነውስ ሆነና ትግርኛ ተናጋሪ ካሕናቱ እናት ቤተ ክርስቲያንን ብሎም ኢትዮጵያን መክዳታቸው እንዴት መጣ?
                           
ክህደት ሲወረስ
በአንድ ወቅት የወያኔ የንግድ ኩባንያ ለነበረው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ከቻይናውያን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይጀመራል፡፡ እንደ ኤርሚያስ ለገሰ የዓይን ምስክርነት ከኢትዮጵያ በኩል የልዑክ ቡድኑን መርቶ የሄደው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለቻይናውያን የነገራቸው ስለ ኢትዮጵያ አይደለም፤ ስለ ትግራይ ሪፐብሊክ እንጂ፡፡ ይህም የታወቀው ቻይናውያን ኢትዮጵያውያን እንግዶቻቸውን ከትግራይ ሪፐብሊክ እንደመጡ አድርገው ሲናገሩ ኤርሚያስ ትግራይ የኢትዮጵያ ትንሽ አካል እንጂ ሀገር እንዳልሆነች፤ የሄዱትም ኢትዮጵያን በመወከል እንደሆነ ባስረዳበት ጊዜ ነው፡፡ በትግራይ ስም የመቀደሱም ሆነ በትግራይ ስም የካሕናት ቡድን ማቋቋሙ የዚህ መንትያ ፕሮጀክት ነው ማለት ይቻላል፡፡  ወያኔ ኢትዮጵያን አፈራርሶ የራሱን ሀገር የመመስረት ትልም እንደነበረው ግልፅ ነው፡፡ የፌዴራሊስት ሃይሎች የሚሉት የቅርብ ጊዜ ስብስብ ኢትዮጵያን እና ማዕከላዊ መንግሥቷን በማፍረስ ትግራይን ሀገር ለማድረግ ብሎም አንዳንድ ሌሎች ብሔሮችን በኮንፌዴሬሽንነት የትግራይ አካል ለማድረግ ያለመ ነበር፡፡
ይህ የወያኔ ክፉ መንፈስ ያደረባቸው ሰዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከድቁና እስከ ጵጵስና ደርሰዋል፡፡ ክፉ መንፈሱ አድሮባቸው ብቻ ሳይሆን ራሱ መልምሎ የሰገሰጋቸውም ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያኗን ለመከፋፈል እና የትግራይ ቤተ ክህነትን ለመመሥረት የሚንቀሳቀሱትም እነኝሁ ናቸው፡፡ ለዚህ እንቅስቃሴያቸው ሁለት አይነት ድጋፎች አሏቸው፡፡
የመጀመሪያው እና ዋነኛው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ አገዛዝ ነው፡፡ አገዛዙ ኢትዮጵያን አፍርሶ እንደገና በኦሮሙማ ቀለም መሥራት ይፈልጋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ የባህል አብዮት (Cultural Revolution) መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሀገረ መንግሥቱ ሥሪት ላይ የሰሜን ወይም የአማራና የትግራይ የበላይነት እንዳለ ስለሚያምኑ ይህንን ወደ ኩሻዊ አብዮት የመቀየር ስውር አላማ ታቅዷል ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴውም ተጀምሯል፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያን መሸንሸን ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ አካባቢውን ለዚህ አብዮት ምቹ ማድረግ ነው፡፡ ሀገረ መንግሥቱ ከሴማዊነት ወደ ኩሻዊነት እንዲቀየር ለማድረግም ቀድሞውኑ የተሰራበትን አምዶች ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ አካላት መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የሚስተካከላት ማግኘት ያስቸግራል፡፡ በመሆኑም የአብይ አገዛዝ ይህቺን ቤተክርስቲያን ማጥፋት ስለሚፈልግ ‹የትግራይ ቤተክህነት፣ የምንስ ቅብጥስ ቤተክህነት› እየተባለ እንዲከፋፈል ይደግፋል፡፡ ወያኔ የከፋፈላቸውን ሁለቱን ሲኖዶሶች ወደ አንድነት ለማምጣት ቢያግዝም አዛኝ፤ በጎ አሳቢ ለመምሰል ይጠቀምበታል እንጂ የጭቃ እሾህነቱን አይተውም፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ይፋ ባደረጉት የኦሕዴድ የማሳመን (Convince) እና ማደናገር (Confuse)  ቀመር መሰረት ይህ በማደናገር ውስጥ ይካተታል፡፡
ሁለተኛው ድጋፍ ሰጭዎቻቸው ደግሞ የኦሮሚያ አቻወቻቸው ናቸው፡፡ ሁለቱም አብሮ ሊያስኬድ የሚችል ሰማያውይም ሆነ ምድራዊ የጋራ መንገድ የላቸውም፡፡ አንዱ በትግርኛ ሌላኛው በኦሮምኛ በመቀደስ ለአማርኛ እና ለኢትዮጵያዊነት ባላቸው ጥላቻ ይመሳሰላሉ እንጂ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉት ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤዎችን በመፃፍ አሉታዊ ጫና እንዲፈጥሩ የሚያግዝ መዋቅር በጠቅላይ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት ውስጥ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሰረት ከሀይማኖት አባቶችና ከምዕመናን እርስ በእርስ ተፃራሪ የሆኑ ደብዳቤዎች ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል፡፡
 የደብዳቤዎች ተቃርኖ 
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ሰሎ በዴሴምበር ዘጠኝ 2020 በአውስትራሊያ አሕጉረ ስብከቶች ከሚገኙ አምስት ቤተክርስቲያናት የተፃፈ ፖለቲካዊ የጋራ ደብዳቤ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት ደርሷል፡፡ በሚልበርን ደብረ ፅዮን ቅድስት ማርያም፣ በፐርዝ ደብረ አሚን ተክለ ኃይማኖት፣ በፐርዝ ፅርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ፣ በአደላይድ ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት እና በስድኒ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚያገለግሉ ትግርኛ ተናጋሪ ቄሶች ናቸው ደብዳቤውን የፃፉት፡፡ ደብዳቤው የሚከተለውን መልዕክት ይዟል፡-
‹‹. . .የትግራይ ሕዝብ የብልፅግና ፓርቲ፣ የዐማራ ልዩ ሃይል፣ የዐማራ ሚሊሻ እና የዐማራ ፋኖ በተባሉ የጥፋት ኃይሎች እንዲሁም በአምባገነኑ የኤርትራ መሪ ወታደሮችና በኢምሬት ድሮውን የጅምላ ጭፍጨፋ እየተካሄደበት ይገኛል›› ይህ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ለምን ዝም እንዳለ ማብራሪያ እንዲሰጥና ይቅርታ እንዲጠይቅ ያዝዛል፡፡ ለተጎጂዎችና ለሟች ቤተሰቦች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግም አስጠንቅቋል፡፡
‹‹አሁንም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ዝምታውን በመስበር በትግራይ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲያወግዝ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡ ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን ሌላ አማራጭ ለመጠቀም እንደምንገደድ ከወዲሁ ልናሳስብ እንወዳለን›› ይላል፡፡ እነኝህ ሰዎች ራሳቸውን ‹ማሕበረ ካሕናት› በማለትም ይገልፃሉ፡፡ ደብዳቤው ፖለቲካዊ ከመሆኑም በላይ የአማራ ፋኖን፣ ሚሊሻ እና ልዩ ሃይልን ያላግባብ በመወንጀል ጥላሸት የቀባ ነው፡፡ ከሃይማኖታቸው ይልቅ ለብሔር ፖለቲካቸው ጠበቃ ሆነው የመጡት እነኝህ ቄሶች ካድራ ወንዝ (ማይካድራ) ላይ ከስድስት መቶ በላይ ዐማራዎች በጅምላ ሲጨፈጨፉ ያሉት ነገር አልነበረም፡፡ ሕወሓት እና ማዕከላዊ መንግሥቱ ሰላም እንዲያወርዱ ፓትሪያርኩን አቡነ ማትያስን ጨምሮ የተለያዩ ሀይማኖቶች አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከአዲስ አበባ መቀሌ ድረስ ሄደው መማፀናቸውን ሸምጥጦ የካደ ደብዳቤ ነው፡፡ ‹‹ቃታ ልንስብ ስንል ነው ያመጣችሁት›› ተብለው አባቶች አንገታቸውን ደፍተው መመለሳቸውንም ዘንግቷል፡፡
ጉዳዩን ይበልጥ ግልፅ የሚያደርገው ደግሞ ከላይ በተጠቀሱት ቤተክርስቲያናት የሚገለገሉ ምዕመናን የይዘት ተቃርኖ ያለው ደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ መላካቸው ነው፡፡ በዴሴምበር 26 ቀን 2020 ከፐርዝ ፅርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ሰበካ ጉባዔ ፅህፈት ቤት የተፃፈው ደብዳቤ ቀዳሚውን ደብዳቤ በግልፅ ይቃወማል፡፡ ‹‹እኛ የደብሩ ሰበካ ጉባዔ አባላት በቅድሚያ ከደብሩ አስተዳዳሪ ጋር ባደረግነው አስቸኳይ ስብሰባ የተላከው ደብዳቤ የአጥቢያው ሰበካ ጉባዔና ምዕመናን እውቅና የሌለውና የደብዳቤው ይዘትና ጭብጥም በፍፁም የፐርዝ ፅርሐ አርያም ቅድሥት ሥላሴ ቤተክርስቲያንን የማይወክል የግለሰብ ሃሳብ እንደሆነ መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ አስተዳዳሪያችን መላከ ገነት ቀሲስ መሃሪ ወ/ኪዳን ተድላ ለፈጠሩት ችግር ሰበካ ጉባዔውን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ እንዲሁም የአጥቢያውን ሕዝበ ክርስቲያን ይቅርታ እንደደሚጠይቁ በሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ ፊት ቃል ገብተዋለል፡፡›› ይላል ደብዳቤው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ሁለቱንም ደብዳቤዎች ተቀብሎ መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡ ይሁን እንጂ በጠቅላይ ቤተክህነት ፅህፈት ቤት ውስጥ የሚያገለግሉ የሃይማኖት አባቶች ከኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ ጋር በመተባባር የትግራይ ቤተክህነት እንዲቋቋም እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንድትዳከም በህቡዕ እየሠሩ መሆኑን የቤተክርስቲያኗ የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ በተለያዩ የእምነቱ ማሕበራት ውስጥ የሚገኙ አገልጋዮችም ጭምር የእኩይ አላማው ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በአውስትራሊያ ቄሶቹ ‹ከትግርኛ ውጭ በአማርኛም ሆነ በግዕዝ አንቀድስም› በማለታቸው  በርካታ ምዕመናን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ውጭ ሆነዋል፡፡ ገንዘብ ከፍለው ባቋቋሙት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባይተዋር ሆነዋል፡፡ በተለይም የፐርዝ ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት  ቤተክርስቲያን ምዕመናን ወደ ሌላ ተሰደዋል፡፡ በአቅራቢያቸው ቤተክርስቲያን ያላገኙ ሰዎች በቤታቸው ተቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በአብዛኛው የዐማራ ተወላጆች ሲሆኑ ከትግሬ እና ኦሮሞ ውጭ የሆኑ ሌሎች ብሔሮች ይገኙበታል፡፡ በፐርዝ ፅርሐ አርያም ቅድሥት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ውስጥ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር በተለየ መልኩ እንዲጨምር አዲስ የሰበካ ጉባዔው አባልነት መታወቂያ ካርድ ዕደላ ለማድረግ ሙከራዎች ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሰበካ ጉባዔ ፀሐፊዋ ለቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ቄስ የደብሩን ማህተም ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለጊዜው አልተሳካም፡፡
ከእነኝህ ክስተቶች ሁሉ መረዳት የሚቻለው ቤተክርስቲያንን ለማፈራረስ ሕወሓት ያደራጃቸው ፖለቲካዊ መዋቅሮች በደብሮቹ መኖራቸውን ነው፡፡ ስለ እነዚህ መዋቅሮች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ሳይናዘዝ ግብዓተ መሬቱ በመፈፀሙ የሚያደርጉት ቅጣምባሩ ጠፍቷቸዋል፡፡ በአንድ ጀምበር የወያኔን ህልም እውን ለማድረግ ሲቃዡም ይስተዋላል፡፡ እንደ ወጣቶች የፍቅር ደብዳቤ በስሜት የሚሞነጫጭሯቸው ደብዳቤዎችና እንደ ቁማርተኛ ስብስብ በየስርቻው የሚያቧድኗቸው ማሕበር ተብየዎችም የቅዠቱ ውጤቶች ናቸው፡፡ እንደ እየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መስለው ይታዩዋቸው የነበሩት አለቆቻቸው እነአባይ ፀሐዬ በጠራራ ፀሐይ በአፍ ጢማቸው ሲደፉ እያዩ ይህንን ባያደርጉ ነበር የሚገርመው፡፡
  ሕወሓትና ኦርቶዶክስተዋሕዶ
ወያኔ ክርስትናም ይሁን እስልምና በመሰረቱ እምነት ጠል ነው፡፡ የአልባኒያ ደቀ መዝሙር ስለነበር ክርስትና እና እስልምናን አይቀበልም፡፡ ወያኔዎች ሃይማኖት ከፋፍሎ መግዣ ነው እንጂ ረብ የለውም የሚል አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ይህንን በይፋ አይናገሩትም እያስመሰሉም ቢሆን ይኖራሉ፡፡ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ደግሞ የተለየ ጥላቻ አላቸው፡፡ ይህም በዋናነት ከሁለት ምክንያቶች የሚመነጭ ነው፡፡ አንደኛው ሃይማኖቱን የዐማራው መደብ የግል አስተሳሰብ አድርገው መረዳታቸው ነው፡፡ ይህም በጠላትነት የፈረጁትን ገዥ መደብ አስተሳሰብ መደገፍ መስሎ ስለታያቸው ጠልተውታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እምነቱ ከኢትዮጵያዊነት እና ከአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቃላማው ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው መሆኑ ነው፡፡
ደርግም እንዲሁ ቤተክርስቲያንን በጠላትነት ፈርጆ የተነሳ ነበር፡፡ ፈጣሪ መኖሩን እንኳን የሚክድ ኮምኒስታዊ ስርዓት ነበር፡፡ ይህ የአብዛኞቹ የ1960ዎቹ ፖለቲከኞች መገለጫ ሆኗል፡፡ እምነት ማርክሲዝም፣ ሌኒኒዝም፣ ሶሻሊዝም ይመስላቸዋል፡፡ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አክትሞ ወታደራዊው ደርግ መንበረ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠረ በከስክስ ጫማው የረገጣት ይችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከመሬት ነጠቃው እና አገልግሎት ከሚሰጡ ቀሳውስት ቅነሳ ጀምሮ ደርግ የወቅቱን ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን በመግደልም ይጠረጠራል፡፡ የደርግ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ቢያውጅም አስተዳድራዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ቤተክርስቲያንን ጎድቷል፡፡ በየሰበቡ በውስጥ አሠራሯ ጣልቃ በመግባት አበጣብጧል፡፡ ይህንን የሚያደርገውም ቤተክርስቲያን ውስጥ የተሀድሶ ጉባኤ የተባለ ቡድን በማቋቋም ነበር፡፡
ደርግ የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ.ም. አቡነ ቴዎፍሎስን ከመንበራቸው አውርዶ በሕይዎት እያሉ በምትካቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን በፓትሪያርክነት ሾመ፡፡ በታሰሩ በ12ኛው ቀን ከተሀድሶ ጉባዔ አባላት መካከል አንዱ መልዓከ ሰላም ቀሲስ ዳኛቸው ለሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት የደስታ መግለጫ ልከዋል፡፡ በቤተክነት መዛግብት ውስጥ የተሰነደው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ቀደምት አበው በፀሎትና በትሩፋት ያቆዩትን የምግባረ ሰናይ ውል አጥፍተው፣ የደገኛውን የቅድስና ክብር አበላሽተው፣ በየዋህነትና በቅን ህሊና የሚከተላቸውን መንጋ ከተመሳቀለ ጎዳና ላይ በትነው እንዲባዝን ያደረጉት፣ በስጋ ምቾት ተውጠው የግፉዓን ካሕናትን፣ የንፁሐን ምዕመናንን ዋይታና እንባ ከምንም ሳይቆጥሩ በማናለብኝነት የኖሩትን የአባ ቴዎፍሎስን ከመንበረ ሥልጣን መነሳት የተቀበልነው ተገቢ ውሳኔ መሆኑን ከልብ አምነንበት ነው››  የተሀድሶ ጉባዔ በቤተክርስቲያን ውስጥ የአብዮቱ ወኪል እንደነበረ ይህ ደብዳቤ የማያሻማ ማስረጃ ነው፡፡
ለፓትሪያርኩ መታሰር ቀጥተኛ ምክንያት የሆነው ደርግን ሳያስፈቅዱ መንግሥትና ሃይማኖት ለየቅል ናቸው በተባለው መሰረት የራሳቸውን ሦስት ጳጳሳት መሾማቸው ነበር፡፡ ሦስቱ ኤጲስ ቆጶሳትም አብረዋቸው ታስረዋል፡፡ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አስክሬን እንዲሰጣቸውና ተገቢው የቀብር ስነ ሥርዓት ወጉን ጠብቆ እንዲፈፀም በመጠየቃቸውም ጥርስ ተነክሶባቸው ነበር፡፡
የወያኔ አገዛዝ ደግሞ ከደርግም በላይ ለቤተክርስቲያን አደገኛ አውሬ ሆኖ ነው የመጣው፡፡ ገና ምኒልክ ቤተመንግሥት ሳይገባ ትግል ላይ እያለ ፀረ ቤተክርስቲያን ነበር፡፡  የአብይ አገዛዝም ቢሆን ከዚህ የተለየ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
የሕወሓት አባል የነበሩት ገ/መድኅን አርአያ ‹የወያኔ ታላቅ ሴራ በቀድሞ አባላቱ ሲጋለጥ› የተባለ መፅሐፍ አላቸው፡፡ ይህንን መፅሐፍ ጠቅሰው አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም፤ ዘዋልድባ ‹የዋልድባና የሕወሓት ፍጥጫ› በተባለው መፅሐፋቸው አክሱም ላይ ያደረሰውን ጥቃት አስፍረዋል፡-
‹‹በ1972 ዓ.ም. ኦፕሬሽን እንዲደረግ ዝርዝር ወጣ፡፡ ኦፕሬሽኑ ለሁለት ነገሮች ነው የተዘጋጀው፡፡ አንደኛው ቅድስት ማርያም የሚባል በጣም ዘመናዊ ሆስፒታል አለ፤ እዚያ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመዝረፍ፤ ሁለተኛው የአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያንን ለመዝረፍ ነው፡፡ የሆስፒታሉን ዕቃዎችና የቤተክርስቲያኑን ቅርሶች የሚወስድ ሰው ይመደብ ተባለ፡፡ ሰው ተዘጋጀ፡፡ ጦርነት ተከፈተ፡፡ በአክሱም ፅዮን በኩል ሰራዊቱ ስለተከላከለ ወያኔ መግባት አልቻለም፡፡ የቅድስት ማርያም ሆስፒታል ዕቃዎችን ግን በሽተኞችን ሳይቀር ከአልጋ አውርዶ መሬት ላይ እየጣለ ዘርፏል››
ወያኔዎች ወደ ጦርነት የሚገቡ ከሆነ በቻሉት መጠን ቤተክርስቲያናት አካባቢ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ትግል ላይ በነበሩበት ጊዜም ሆነ በቅርቡ ከአብይ አሕመድ አገዛዝ ጋር በተደረገው የዳግም ትግል ጦርነት ወደ ቤተክርስቲያን ለመጠጋት ሞክረዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት አራት ምክንያቶችን አስበው ይመስለኛል፡፡ እነርሱም፡-
 በጦርነቱ ጊዜ ቤተክርስቲያኑ እንዲወድም  ቤተክርስቲያኑ ቢወድም ሕዝቡ በገዥው መንግሥት ወይም በጠላታቸው ላይ እንዲነሳሳ ለማድረግ  ቤተክርስቲያኑን ላለማውደም ሲል የጠላት ጦር እንዳይጨክንባቸው ለማድረግና አዘናግተው ለማጥቃት  ራሱን የቤተክርስቲያኑን ቅጥር ግቢ እንደ ምሽግ ለመጠቀም በቅርቡ ውጅራት በሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ  ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ አከማችተው መገኘታቸውም እነኝህን ጠቀሜታዎች ያለመ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በልማት ሰበብ የአድባራትን ክብር መግፈፍ ሌላኛው የወያኔ መገለጫ ነው፡፡ ለአብነትም አዲስ አበባ፤ ከቦሌ ሚካኤል ወደ ሳሪስ አቦ ሲሄድ መሀል ላይ የሚገኘው ጥንታዊው ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ይጠቀሳል፡፡ ይህ ቤተክርስቲያን በመንገድ ግንባታ ሰበብ ቅጥር ግቢው ከሁለት ተከፍሎ ይገኛል፡፡ የሙታን አፅም ከጉድጓድ  እየተቆፈረ ወጥቶ በላዩ ላይ ‹አስፋልት መንገድ ተሠራበት፡፡ አንሺ ያጡ አፅሞችም መንገድ በሚሠራ ‹ዶዘር›፣ ‹ኤክስካቬተር› እና ‹ሮለር› እንዳልሆነ ሆነዋል፡፡ ወያኔ የሙታንን በሰላም የማረፍ መብት እንኳን አያከብርም፡፡ አገዛዙን ከእነኝህ የነጠቀው ቡድን ደግሞ ከዚህም በባሰ መልኩ የሰው ስጋ ተዘልዝሎ የሚበላበት፣ አስክሬን ተቆራርጦ አስፋልት መንገድ ላይ የሚጣልበት፣ ሰው ተዘቅዝቆ የሚሰቀልበት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች ቤት ውስጥ ተዘግተው በእሳት የሚጋዩበት ሲዖል ሆኗል፡፡
የአቶ ገብረ መድኅን ማስታወሻ ከላይ ያስቀመጥኳቸውን ግምቶች ያጠናክራል፡፡ ‹‹ወያኔዎች በቤተክርስቲያን ላይ ስለሚያደርሱት ጉዳት እኔም የማውቀው ጉዳይ አለ፡፡ የዐድዋ ደብረ ብርሃን ሥላሴ አፄ ዮሀንስ ያሠሩት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ሰዓሊዎች ከግብፅ መጥተው የሠሩትና ታሪካዊ ነው፡፡ እዚያ ወያኔ ምሽግ ሰርቷል፡፡ ቦታው ተራራማ ከመሆኑም በላይ ወደ ጦሩ የሚመለከት ነው፡፡ ተክሉ ሐዋዝን ካርቱም መጥቶ ‹እንዴት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትመሽጋላችሁ? ከተመታ በኋላ ደርግ ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳል ለማለት ነው? ለፕሮፖጋንዳ ከሆነ የምትጠቀሙት፤ እሱ ይበልጣል ወይስ የቅርስ መውደም? ይህ ቤተ ክርስቲያን እንደገና ቢሠራም እንደቀደመው አይሆንም፡፡ ያ ጊዜውን ጠብቆ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ይዞ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን እንዲፈርስ እንዴት እዚያ ትመሽላችሁ?›  አልኩት፡፡ ‹እኔ የምሠራው የስለላ ተግባር ነው፡፡ ይህንን የወታደራዊ ጉዳይ ሰዎችን ጠይቅ› ብሎ መለሰልኝ›› ይላሉ የሕወሓት አባል የነበሩት ገብረ መድኅን አርዓያ፡፡
ሕወሓት ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት አባላቱን ሥራዬ ብሎ ያሰለጥን ነበር፡፡ ለአብነትም በመስከረም፤ 1970 ዓ.ም. በድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ በኩል ፀረ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅስቀሳ ለማድረግ በእገላ ወረዳ መሬቶ በተባለ አካባቢ በተደረገው ሥልጠና የሚከተሉት ሰዎች ተገኝተዋል፡- አባይ ወልዱ፣ አዲሳለም ባሌማ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ መርሳ ረዳ፣ አለቃ ፀጋዬ በርሔ፣ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ ሀዱሽ አለሙ፣ ኃይለሥላሴ ገብረ ኪዳን፣ ሃሪያ ሰባጋዲስ፣ ጉዕሽ፣ ጓእዳን፣ ቢተው በላይ፣ ሃድሽ ገዛኸኝ፣ ሮማን ገብረ ሥላሴ፣ አፈራ ተክለ ሃይማኖት፣ እና ወልደ ገብርኤል ሞደርን ለሦስት ቀናት የተዘጋጀላቸውን ፀረ ኦርቶዶክስ ሥልጠና እንደጨረሱ በሦስት ቀጣና ተከፋፍለው ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ በመሆኑም በትግልም ሆነ በሥልጣን ላይ ቆይታቸው ቤተ ክርስቲያንን ክፉኛ ሲጎዱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬም ቤተ ክርቲያንን እያሳደደ ለሚያቃጥለው እና ለሚዘርፈው የእነ ሽመልስ አብዲሳ መንግሥት ተራውን ሰጥተዋል፡፡ አሁን ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል በውጭ ሀገራት እየታየ ያለው እንቅስቃሴም የእነርሱ ውጤት ነው፡፡
(ፍ-ት-ሕ መፅሔት ሦስተኛ ዓመት ቁጥር 117 ጥር 2013 ዓ.ም.)
Filed in: Amharic