>

ቅዱስ ፓትርያርኩ  "ታፍኛለሁ!" ማለታቸው ስለምን ጫጫታ አስነሳ...!!! (ዘመድኩን በቀለ)

ቅዱስ ፓትርያርኩ  “ታፍኛለሁ!” ማለታቸው ስለምን ጫጫታ አስነሳ…!!!

ዘመድኩን በቀለ


በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ብዙ ግፍ ተሠርቷል…!  በትግራይ ላይ የተደረገው ግን ይበልጣል ማለት ሀጥያቱ ምኑ ላይ ነው…???
ለዓለም መንግሥታት፣ ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት የተለየ የድጋፍ ጥያቄ ጠይቀዋል። 
… ትናንት በዘመን መለወጫ ዕለት በመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው በመላ ኦሮሚያ ለሚታረደው ኦርቶዶክሳዊ ሁሉ እንባቸውን መንታ መንታ እያፈሰሱ አልቅሰው አይተናል።
… ትናንት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና በካህናቱ ፊት ቆመው በመላው ኢትዮጵያ ለሚፈሰው የኦርቶዶክሳውያን ደም ” ሰው እንዴት ይታረዳል? እንደምን ያለ ጭካኔ ነው? ” በማለት ጠይቀው በሁሉ ፊት ሲያለቅሱ አይተን አብረን አልቅሰናል።
… በመሃል የትግራዩ ውዝግብ ሲመጣ እነ ደብረጽዮን በዚያኛው ጫፍ፣ አሁን በደብረ ጽዮን ቦታ ትግራይን ይመራ ዘንድ በሞጋሳ ስሙ ተቀይሮ ዶር ገዳ ኦላና ተብሎ የተሰየመው ዶር አብርሃም ተከስተ በዚህኛው ጫፍ የብልጽግናን ፓርቲ ይደግፉ ዘንድ ላቀረበላቸው ጥያቄ የህወሓትንም፣ የብልጽግናንም ከእኛ ጋር ይሥሩ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ” እኔ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ነኝ። በእናንተ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም። ” በማለት ለሁለቱም ጎታቾቻቸው ምላሽ መስጠታቸው ይታወቃል።
… ቅዱስ ፓትርያርኩ አሁን የቁም እስረኛ ናቸው። አጠገባቸው የሚገኙ ረዳቶቻቸው በሙሉ እንዲወገዱ ተደርገዋል። የሚሰድቧቸው፣ የሚያንጓጥጧቸው፣ በትግሬነታቸው የሚያበሻቅጡአቸው እንዳሉ በግልጽ ተነግሯል። አረጋዊ፣ ሽማግሌም ናቸው። በተቻላቸው ሁሉ ሚዛናዊ ለመሆን የሚጥሩም ናቸው። ደግሞም በዚህ የዘር ፖለቲካ በጦዘበትና ሕገ መንግሥታዊ ይሁንታ በተሰጠው ሃገር ላይ ምንስ ብለው ቢናገሩ ይደመጣሉ?
… በአሜሪካ በነበሩ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ የሚደግፉት የፖለቲካ ፓርቲ ይኖራል። ልክ ዛሬ ብልጽግናን እንደግል አዳኛቸው የሚቆጥሩ ብፁዓን አባቶች እንዳሉ ማለት ነው። ባይሆን ጥሩ ነበር። ነገር ግን እንደዚያ ቢያደርጉም አይፈረድባቸውም ባይ ነኝ። ለባለ ጊዜ የማይንበረከክ፣ የማይላላክ እጅግ ሲበዛ ጥቂት ነው። ከዚያኛው ይሄኛው ይሻላል በሚል ማለት ነው።
… ዛሬ ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ መታፈናቸውን የሚገልጽ ቪድዮ ተለቅቆ አይቼዋለሁ። ይሄ ይሆን ዘንድ ሳይታለም የተፈታም ነው። ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ሲባል ሁሉን ችለው እንደተቀመጡ እንጂ ወደገዳም ሄደው መቀመጥ እንደሚፈልጉ ሁላ ለእኔው ለራሴ እንደነገሩኝ ባለፈው ጊዜ እንደገለጽኩላችሁም ይታወሳል። ነገርየው ከባድ ብቻ የሚለው ቃል የሚገልጸው አይደለም። እጅግ በጣም ከባድ ነው።
… ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ከባድ መከራ ውስጥ ሆነው ነው ዛሬ በወዳጃቸው ስልክ በተቀረፀ ምስል በአጠቃላይ በኢትዮጵያ፣ በተለይ ደግሞ በትግራይ እየተፈጸመ ነው ያሉትን ዘግናኝ ሰብአዊ ቀውስ እና ወንጀል የሚቃወም መልእክት ያስተላለፉት። ቅዱስ ፓትርያርኩ ያስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ካስተላለፈው ቢያንስ እንጂ አይበልጥም። የተባበሩት መንግሥታትና የአውሮጳ ኅብረት ካስተላለፉት ቢያንስ እንጂ አይበልጥም። ራሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ፓርላማ ቀርቦ ” ችግሮች ይኖራሉ፣ ችግር የፈጠሩ አካላትን አጣርተን ለፍርድ እናቀርባለን” ያለበትን እኮ ነው  ተናገሩት። እናም ዛሬ ምን የተለየ ነገር ቢናገሩ ነው እንዲህ ወቀሳው የበዛባቸው?
… ቅዱስነታቸው አሁን በትግራይ የሚፈጸመው ግፍ በኦሮሚያ አለ። በቤኒሻንጉልም አለ። በሸዋሮቢትም አለ። በሃገሪቱ በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ሁሉ አለ…  በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉልም ብዙ ግፍ ተሠርቷል። በትግራይ ላይ የተደረገው ግን ይበልጣል። የዘር ማጥፋት እየተፈፀመ ነው ያለው ነው ያሉት። መልእክቱንም ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያውያት ይድረስልኝ ብለው ነው ያስተላለፉት። ለትግራይ ተወላጆች ይድረስልኝ አላሉ።
… ስለ ትግራይ ስናገር ድምጼ ይታፈናል። በትግራይ ጭካኔ የተሞላበት የአረማዊነት ድርጊት እንዲቆም ብዙ ጊዜ ሞክሬ አልተሳካም። ሚያዝያ 7 ያደረኩት ኢንተርቪው ታግዷል። ስቃወም ድምጼ ይታፈናል። የዓለም ሚዲያ እየተናገረው እኛ እንዳንናገር ታፍነናል ነው ያሉት ብፁዕነታቸው። ስለሌሎች ክልሎች በእንባ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ስለ ትግራይ በቁጭት ብቻ በሀዘን ልብ መናገራቸው ልብ ይሏል።
… እደግመዋለሁ ቅዱስ ፓትርያርካችን አሁን የቁም እስረኛ መሆናቸውን ነግረውናል። “እኔ ያለሁበትን ሁናቴ ማንም አልተረዳልኝም፣ ብዙ ችግር አለ” ብለው ከመናገር በላይ ምን እንዲያስረዱ ነው የተፈለገው? ወደ እሳቸው ጋር ገብተው የሚወጡ የትግራይ ልጆች ትግሬ በመሆናቸው ብቻ በልዩ የደኅንነት ክትትል ውስጥ እንደሚወድቁ ሰምተናል። ፖሮቶኮላቸው ታስሯል። ብቸኛ እና የቁም እስር ሰለባም ናቸው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በዚህ ሰዓት ምን እየተፈጸመ እንደሆነም የሚያውቁት ነገር የለም። የሚደርሳቸው መረጃ እጅግ ውስን ሆኖ እኛ በኢንተርኔት የምናየውን የትግራይ ግድያ ብቻ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ከሁሉም የአስተዳደር ሥፍራዎች አርቀዋቸዋል። ደብዳቤዎች የሚበሩት በዋና ጸሐፊውና በዋና ሥራ አስኪያጁ ነው። የአዲስ አበባ ሃገረስብከትን ሹመት በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩና ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢቃወሙትም ከአሜሪካ የመጡት ዋና ጸሐፊው በራሳቸው ፊርማ ደብዳቤ አውጥተው መሾማቸው ይታወሳል። እናም አሁን እሳቸው በዘራቸው ምክንያት ባይተዋር እንደተደረጉ ነው የሚነገረው።
… ዛሬ ምድረ የኦነግ አሽቃባጭ በሙሉ ትናንት “የትግራዩን ጦርነት ባረኩ ብሎ ቁጭ ብድግ ሲያደርጋቸው የከረመ ሁላ ድንገት ከመሬት ተነሥቶ የእሳቸው ደጋፊ ሆኖ የአዞ እንባውን ሲያነባ ማየት እጅግ ያሳፍራል። የህወሓት ደጋፊዎች በሙሉ ትናንት እንደ ተራ ሰው ሲሰድቧቸው የከረሙትንና ለብልጽግና ያደሩ፣ የዐቢይ አሕመድ ተላላኪ አሽከር ሲያደርጓቸውና ሲወቅሷቸው፣ ሲሰድቧቸውም የነበሩትን አባታችንን ዛሬ ሲያወድሱ ስታዩ መጠርጠር፣ ንቆ ማለፍ እንጂ አብሮ ማጨብጨብ ተገቢ አይደለም። በተለይ የወሃቢ እስላሞቹ ፔጅ ከመስቀል አደባባይ ንትርክ በቀጥታ ወደ ፓትርያርኩ ንግግር ዞረው ለትግራይም ለፓትርያርኩም ያዘኑ መስለው የአዞ እንባ ሲያወርዱ እንደማየት የሚያስቅ ነገር የለም።
… እንደ አቶ ታዬ ቦጋለ ዓይነት በሞቀበት የሚፈላ። ነገሮችን አላምጦ መዋጥ፣ አስሬ ለክቶ አንዴ መቁረጥ የማይችል፣ ስሜቱ አፍንጫው ስር የሆነች፣ በሁሉ ነገር ልክ ነኝ ባይ፣ በኢትዮጵያዊነት ካባ ተጠቅልሎ መርዙን የሚረጭ ዓይነት ሰው “ደመራው የሚወድቅበትን አቅጣጫ” እያየ ትንቢት ልናገር ባይ አውርቶ አደር፣ የላይክ ጥመኛ በሞቀበት ፈልቶ ከመስመር ወጥቶ ቅዱስነታቸው ላይ አፉን ሲያላቅቅ እያየን አብረን ልናቦጀቡጅ አይገባም።
… እንደ ገመድ አፉ ተብታባው የብልጽግና ፖፖ ያዡ መናፍቁ ደሳለኝ መሃል ሜዳው ይፍረስና ከመኔሜንጤ ጋር አብረን ልንንቦጃቦጅ አይገባም። ሃይማኖት አልባ ከሆኑ፣ ፀረ ተዋሕዶ ከሆኑ፣ ገና ብዙ ድግስ ከደገሱልን ሰዎች ጋር አብረን ቆመን በቅዱስነታቸው ላይ አፋችንን ልናላቅቅ አይገባም። የህወሓት፣ የብልጽግና፣ የኦነግ፣ የአክራሪ ጴንጤና የአክራሪ እስላሞችን የአዞ እንባ ተከትለን አብረን ወላይትኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ፣ ምንጃርኛ፣ ጎንደርኛ፣ ጎጃምኛና ሲዳምኛ፣ እንዲሁም መንዙማ ከፍተን ልናሽቋልጥ አይገባም።
… ስለ ዐማራ መታረድ፣ ስለ ወለጋው እልቂት፣ ስለ ኦሮሚያ ጭፍጨፋ፣ ስለ ሰሜን ሸዋ ውድመት፣ ስለመተከል እርድ እስቲ የትኛው የብልጽግና መሪ ነው አውግዞ ያየነው? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሁለት መስመር የጻፈ ሰው አሳዩኝ ጠቁሙኝ እስቲ። ፓትርያርኩ የትግራዩን ጦርነት ባረኩ ብሎ ፕሮፓጋንዳ የሠራባቸው ራሱ ብልጽግና አይደለም ወይ? እና ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው ፓትርያርኩን ለመውቀስ መንደፋደፍ ያስፈለገው። በተለይ አቶ ታዬ አረጋ የሚባል አጋሰስ ” አንተ እያላቸው ሲያብጠለጥላቸው ማየት ያማል። እሳቸው ባሉበት አንጻር አሁን ልክ ናቸው? ደግሞም የተቀነጨበ ቪድዮም ሊሆን ይችላል። ስለብዙ ነገር ተናግረው ኤዲት ተደርጎም ሊሆን ይችላል።
… ቅዱስነታቸው መልእክቱን የላኩት ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ነው። የዐማራ ጳጳሳት፣ የኦሮሞ ጳጳሳት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊት በሙሉ ሳያወግዙ ፀጥ ብለው ተቀምጠው ሳለ ቅዱስ ፓትርያርኩም እንዳይናገሩ አፍነው አሳፍነው ሲያበቁ አሁን ቅዱስነታቸው በስንት መከራ በተገኘ ቀዳዳ ተጠቅመው፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል፣ በዐማራ ሸዋሮቢት የተፈጸመውን ሲያወግዙ የትግራይን ዝም እንዲሉ መፈለግ ይሄ ራሱ አረመኔነት ነው። ሲበዛም ጨካኝነት ነው። የጎደለ፣ የተሳተ፣ የተገደፈ ነገር ካለም በጨዋ ደንብ እንጠይቃለን እንጂ ከወሃቢ እስላም፣ ከአክራሪ ጴንጤ፣ ከፀረ ኦርቶዶክስ እና ከአንዳንድ ጥቂት ከትግሬ ጠል የዐማራ ካድሬዎች ጋር በመሆን አፋችንን በአባታችን ላይ አንከፍትም።
… እኔ ግን እላለሁ ቅዱስ አባቴ ሆይ ቡራኬዎት ይድረሰኝ። አደራ አባታችን አደራ፣ አደራ፣ አደራ ደግሜ እማጸንዎታለሁ “ኢትዮጵያን አይርገሟት።”
ሻሎም !   ሰላም !
Filed in: Amharic