>

ታዲዮስ ታንቱ፣ ግሥላ ጅራቱ — የአባቶርቤውን ሰይጣን ያወጡ ታላቅ አርበኛ! (አሰፋ ሀይሉ)

ታዲዮስ ታንቱ፣ ግሥላ ጅራቱ — የአባቶርቤውን ሰይጣን ያወጡ ታላቅ አርበኛ!

አሰፋ ሀይሉ

*…. ወጣቱ እስክንድር ነጋ የቤተመንግሥቱን አባቶርቤ ማንነት እርቃኑን አውጥቶ አሳይቶናል፡፡ አሁን ደግሞ እኚህ አዛውንት ምሁር የአባቶርቤውን ሰይጣን መሀል አራት ኪሎ ላይ አውጥተው አፍርጠው አሳይተውናል፡፡ ታጋዮቹ አባቶርቤውን በአደባባይ እያስጣጡ ሲያሳዩን፣ ያየነውን የአባቶርቤ ሰይጣን የአባቶቻችንን ጀግንነት ለብሰን መዋጋት የኛ ፋንታ ነው….!
 
ለውጡ ተጠልፏል…!!!
እነ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ ከወያኔ ጋር ሲተናነቁና እስር ቤት ሲወረወሩ በነበሩበት አስከፊ የትግል ወቅት፣ አብይ አህመድ የኢንሳ ሃላፊ ሆኖ ለወያኔ ጆሮ እየጠባ ለትግል የተሰለፉትን ያሳፍን የነበረ ሰው ነው፡፡ እነ እስክንድር ነጋ ቤተሰባቸውን በትነው ከወያኔ ጋር በአደባባይ ሲፋለሙ፣ አብይ አህመድ ለወያኔዎች ወሬ እያቃጠረ ከእነ በረከት ስምዖንና ደብረጽዮን ጋር በሚኒስትር ሹመት በምቾት አልጋ ሲገላበጥ የኖረ ሰው ነው፡፡ አሁን ለውጥ የተባለው ሲመጣ፣ የወያኔ አቃጣሪና የታጋዮችን ድምጽ አፋኝ የነበረው ጆሮ ጠቢ ቤተመንግሥት ገብቶ፣ የሕዝቡን ድምጽ ይዘው ሲታገሉና የህዝብን ተቃውሞ ሲያቀጣጥሉ የነበሩት አርበኞች ከርቸሌ ተወረወሩ፡፡
ለውጡ የታሰበው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለንተናዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለማምጣት የታለመ ሕዝባዊ ብሶትና አመጽ የወለደው ለውጥ ይሆናል ተብሎ ነበር፡፡ በመሐል ግን ኢህአዴግ ‹‹መተካካት›› ብሎ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ካስቀመጣቸውና – የወያኔን ሥልጣን ለመረከብ እጅጉን ከጓጉት የወያኔ ቡችሎች ጋር – እንደ ኢዜማ ያሉ የሕዝብን ትግልና መስዋዕትነት የካዱ ሰዎች በጓሮ በር ተደራድረው – የሕዝቡ አርበኞች አንድ በአንድ እየተገደሉ፣ እየተገለሉና እስርቤት እየተጣሉ – ሕዝቡን ሲያደሙ የኖሩ፣ በህዝቡ ላይ ሲያቃጥሩ፣ ሕዝብን ሲያሳፍኑ የነበሩ ባንዶች ደግሞ ቤተመንግሥት ገብተው መንግሥት የሆኑበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ባጭር አነጋገር ለውጡ ተጠልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉና በመስዋዕትነቱ ያንገፈገፈውን ኢህአዴግና ሥርዓቱን ሊጥል አንድ ሀሙስ ሲቀረው፣ ‹‹መተካካት›› በሚል ባዶተስፋ ዝግጁ አድርጎ ባስቀመጣቸው የሥልጣን ተኩላዎች እጅ ቀድሞ ተበልቶ፣ እነዚሁ የወያኔ ተተኪ ቡችሎች ከእነ ብርሃኑ ነጋ ጋር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ጓሮ ለጓሮ ተደብቀው ባደረጉት ሴራ – የለውጥ ሀዋርያ መስለው፣ በህዝብ ትግል ያበቃለትን የኢህአዴግን ሥርዓት በለውጥ ስም ተረክበው በማስቀጠል፣ ታላቁን የሕዝብ መስዋዕትነትና ትግል ለግልና ለጎሳ የሥልጣን ጥማታቸው ማርኪያ ቆምረውታል፡፡
ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣት ደምቶና ሥጋው ተተልትሎ የፈጠረው የለውጥ ተስፋ፣ በወያኔ የሥልጣን ተተካኪዎችና በእነ ብርሃኑ ነጋ አጋፋሪዎች ታግዞ – ከኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ተፈልቅቆ ወጥቷል፡፡ ለውጡ ተጠልፎ፣ በለውጥ ስም፣ እውነተኛ ታጋዮች እስር ቤት ተወርውረው፣ ሀገር በባንዳዎች እጅ ወድቃለች፡፡
ከወያኔ ጋር ሲተናነቁና መከራ ሲቀበሉ የኖሩት እነ እስክንድር ነጋና ታዲዮስ ታንቱ እስር ቤት ተወርውረው – የወያኔ የኢንሳ ጆሮ ጠቢ የነበረ የህዝብ ትግል አምካኝ ቤተመንግሥት የገባበት ለውጥ – ለውጥ ሳይሆን፣ በህዝባችን ደም ላይ የቀለደ አስቀያሚ ነውጥ ነው! ይህ በህዝባችን ላይ የተቀለደበት ታላቅ የለውጥ ክሽፈት፣ ከ1966 ዓ.ም ወዲህ ኢትዮጵያችን ያጋጠማት፣ ከክሽፈቶች ሁሉ የከፋ ክሽፈት፣ ከሽንፈቶች ሁሉ የከፋ ሽንፈት፣ ከቀልዶች ሁሉ እጅጉን የመረረ በሕዝብ ደም ላይ የተቀለደ ሀገራዊ ቀልድ ነው፡፡
ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልና ጩኸት መና ቀርቷል፡፡ ለውጡ ተጠልፏል!! የወያኔ ጆሮጠቢዎች  ቤተመንግሥት እየተገማሸሩ፣ ወያኔን የታገሉት ከርቸሌ ተጥለው የሚቀጥል ለውጥ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳግመኛ የዲሞክራሲ ትግሉን መጀመር ይኖርበታል፡፡ ከነበረከት ስምዖን ጋር ሲፏልል የነበረውን አብይ አህመድን አንግሦ፣ ወያኔ ሲያማቅቀው የኖረውን እስክንድር ነጋን እስርቤት የጨመረ ለውጥ – ለውጥ ሳይሆን – ነውጥ ነው!
ከወያኔ ጋር ከሥልጣን ሥልጣን ሲንፏቀቅ የነበረው አብይ አህመድ የለውጡ ሃዋርያና አምጪ ተደርጎ ቀርቦ፣ የወያኔን ዘረኛ ሥርዓት ፊት ለፊት በብዕራቸው ደንቁለው ለዓለም ያስጣጡትና መከራን የተቀበሉት እነ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ የለውጡ አደናቃፊ ተብለው በስተርጅና እስር ቤት የሚወረወሩበት ለውጥ – ለውጥ ሳይሆን መራር ቀልድ ነው!
ትናንት ከወያኔ ጋር ሆነው ሕዝብን ሲቦጠቡጡና ሲያደሙ የኖሩ በህዝብ ደም ላይ የቀለዱ ባንዳዎች መንግሥት ሆነው ቀጥለው፣ በወያኔ እጅ ለህዝባቸው ሲሉ መከራን የተቀበሉ እነ አሳምነው ጽጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ እነ ታዲዮስ ታንቱ፣ ሌሎችም ከርቸሌ ተጥለውና በግፍ ተገድለው – በሠላም የሚተኛ ሕዝብ አይኖርም! ለውጡ ከሽፏል! ለውጡ ተጠልፏል! የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጠለፈበትን ለውጥ በትግሉ ማስመለስ አለበት! ጊዜው ምርጫ የማይሰጥ ነው! ጊዜው የምርጫ ሳይሆን፣ የታላቅ ሀገራዊ ተጋድሎ መባቻ ነው! ይኸው ነው!
ሌላም አርበኛ ያስፈልገናል!
 
የቤተመንግሥቱ አባቶርቤ ጭምብሉን ገፎ ዘልሎ እንዲከመርባቸው ለማማለል ቢያንስ ለአንድ ዓመት ሳይታክቱ እስኪበቃው ነግረውታል! መጨረሻ ግን አልቻለም! መጀመሪያ መናፈሻ ውስጥ ገባ፤ ላፕቶፕ ይዞ፡፡ ጫካው ጠራው፡፡ ደም ሸተተው፡፡ በመጨረሻ ዘልሎ ተከመረባቸው፡፡ በ70 ዓመት ሽማግሌ ላይ፡፡
ምንም ጦር ሳይነቀንቁ፣ ምንም ስናይፐር ሳይታጠቁ፣ በቃላትና በዕውቀት አልመው ሚጢጢ ጭንቅላቱን ፈረቃቀሱት፡፡ አሁን በቤተመንግሥቱ ያደፈጠው አባቶርቤ ማንነቱ ገሃድ ወጣ፡፡ እኚህን ምሁር አለማድነቅ ንፉግነት ነው፡፡ እንደ ድግምት ነው ዓመት ሙሉ በጆሮው ላይ አነብንበው አነብንበው ዛሩን ጎልጉለው ያወጡት!
የአባ ቶርቤው ሰይጣን እስኪወራጭ ድረስ እሳቸውን በተከታታይ እያቀረበ ታላቅ የትግል አርማ የሚሆኑን የወላይታ ጀግና የፈጠረልንን ሚዲያም አድንቄው አላባራሁም፡፡ የወላይታ ህዝብ ከጎናችን ሆኖ አባቶርቤውን እንደሚፋለመው እናምናለን! ሰይጣኑ ከጎሬው ወጥቷል! ሰይጣኑን ከጎሬው እያወጣን መፋለም ደግሞ የኛ ፋንታ ነው!
ወጣቱ እስክንድር ነጋ የቤተመንግሥቱን አባቶርቤ ማንነት እርቃኑን አውጥቶ አሳይቶናል፡፡ አሁን ደግሞ እኚህ አዛውንት ምሁር የአባቶርቤውን ሰይጣን መሀል አራት ኪሎ ላይ አውጥተው አፍርጠው አሳይተውናል፡፡ ታጋዮቹ አባቶርቤውን በአደባባይ እያስጣጡ ሲያሳዩን፣ ያየነውን የአባቶርቤ ሰይጣን የአባቶቻችንን ጀግንነት ለብሰን መዋጋት የኛ ፋንታ ነው፡፡ የጠላትን ማንነት ከነደካማ ጎኖቹ በማያወላዳ አኳኋን ማወቅ፣ የድል ግማሽ መንገድ ነው!
ጋሼ ‹‹ታዲዮስ ታንቱ፣ ግሥላ ጅራቱ›› በአርበኞች መታሰቢያ በዓል ላይ ታላቅ የአርበኝነት ተጋድሎ የፈጸሙ የዘመናችን ጀግና ናቸው! በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሀውልት ሊቆምላቸው ይገባል!
አሁን ታላቅ የወላይታ ጀግና ይዘናል! ከጋሞ አይረሴው ጋሼ አሰፋ ጫቦ አለልን! ከየብሔረሰቡ የትግላችን አርማ የሚሆኑ ጀግኖች ያስፈልጉናል! ሚዲያዎች በምታውቁት መንገድ የአባቶርቤውን ሠይጣን አውጥተው የሚያስጨፍሩ ኢትዮጵያውያን የትግል አይከኖችን እየፈለጋችሁ አምጡልን! ውለታችሁን ይህቺ ሀገር አትረሳባችሁም!
ታዲዮስ ታንቱ፣ ግሥላ ጅራቱ — ትውልድን በትኩስ የጀግና ትንፋሽ የቀሰቀሱ፣ የዘመናችን ታላቅ አርበኛ ናቸው!
ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ተጋድሎ ለዘለዓለም ትኑር!
አባቶርቤ ይውደም! 
ኢትዮጵያ ትቅደም!
Filed in: Amharic