>

ግፉ አልበቃ ብሎ ለተገፉ ሰዎች ድምጽ የሚሆኑ ሰዎችን ማፈን፤ ነውራችን ለከት ማጣቱን ነው የሚያሳየው...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ግፉ አልበቃ ብሎ ለተገፉ ሰዎች ድምጽ የሚሆኑ ሰዎችን ማፈን፤ ነውራችን ለከት ማጣቱን ነው የሚያሳየው…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

 በትግራይ የደረሰውን ግፍ በሰላሳ መንገድ ልንሸፋፍነው ብንሞክር ገና ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል። የግፍ ጽዋ አልነጥፍብሽ ያላት አገር ዛሬም ዜጎቿ በየመንደሩና በየስርቻው  እያለቁ ነው። የትግራዩ የከፉ ቢሆንም ተመሳሳይ ግፍ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም እየተፈጸሙ ቸው። ግፍን ማንጠፍ እንጅ መሸፋፈን ከተጠያቂነት አያድንም።
ብዙ ግዜ የመንፈስ አባቶች እንዴት አፍንጫቸው ስር ግፍ ሲፈጸም፣ የመንፈስ ልጆቻቸው ሲሳደዱ፣ ሲዋረዱ፣ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉ እያዩ ለምን ዝም ይላሉ እያልን እንወርፉቸው ነበር። ዛሬ ጳጳሱ ለወራቶች የደረሰባቸውን የፖለቲከኞች ጫና እና አፈና ተቋቁመው ለግፉአን ድምጻቸውን ቢያሰሙ  የሰው ስቃይ ደንታ የማይሰጣቸው ግልብ ካድሬዎችና ጭፍን ደጋፊዎቻቸው ፍጹም ባልተገራ አንደበታቸው ጳጳሱን ሊያዋርዱ፣ ሊያሸማቅቁ እና ሊያስፈራሩ ሱሞክሩ አየሁ። ያሳፍራል፤ ግፍን ማውገዝ እና ግፈኞችን መታገል ቢያቅት ዝም ይባላል እንጂ ለግፉአን የቆሙ ሰዎችን ለማሸማቀቅ መሞከር ግፍን ከማጽናት እና ግፈኞችን ከማጀገን ሌላ ምንም ፋይዳ አይኖረውም።
አድርባይ ምሁር፣ አድርባይ አክቲቪስት፣ አድርባይ የሲቪክ ማህበራት፣ አድርባይ ፖለቲከኛ፣ አድር ባይ የመንፈስ አባቶች፣ አድር ባይ ጋዜጠኛ፣ አድር ባይ የመብት አቀንቃኝ በሞላበት አገር ለእውነት መቆም ከባድ ብቻ ሳይሆን የህይወት ዋጋም ያስከፍላል። አድር ባይነት በነገሰበት አገር ግፍን ማንጠፍ ከባድ ነው።
ግፍን ተጠየፍ፣ ግፍን አውግዝ፣ ለግፉአን ድምጽ ሁን፣ ግፈኞችን ታገል። ይህን ማድረግ ያልቻለ ሰው ዝም ይበል። ዝምታውም ትብብር ነወ።  ለግፉአን የሚጮሁ ድምጾችን ለማፈን የዘር፣ የሃይማኖት እና ሌላ ታርጋ እየመዘዙ በአደባባይ ግፍን የሚቃወሙ ሰዎች ላይ መለጠፍ ከግፍ ፈጻሚዎቹ ተርታ መሰለፍ ነው። አንድ ቀን ያስጠይቃልም። አባታችን ባቋምዎ ይጽኑ። ሌሎች አባቶችም ከፍርሃት ቆፈን ተላቃችሁ እውነትን አርነት አውጧት።
Filed in: Amharic