ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ህወሓት እና ሸኔ በአሸባሪነት መሰየማቸውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ…!!!
(ኢ ፕ ድ
ባለፉት 3 ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በዚህም ምክንያት የበርካታ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል እንዲሁም ቤት ንብረታቸው ወድሟል፣ ብዙዎችም ከቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል።
እነኚህ ጥቃቶች ህብረተሰቡ ከስጋት እና ፍርሀት ተላቆ በነጻነት እንዳይኖር እንዲሁም ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ በማድረግ የሀገረ-መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈፀሙ የነበሩ መሆኑን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።
እነኚህ ጥቃቶች ከጀርባቸው የፖለቲካ አስተሳሰብን መነሻ በማድረግ እና የፖለቲካ ዓላማን ወይም ግብን ለማሳካት በማሰብ በንጹሀን ዜጎች እና በሕዝብ መሰረተ-ልማቶች ላይ ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የቆዩት እነዚህ ጥቃቶች በተለያዩ ቡድኖች የተፈጸሙ ቢሆንም ከጥቃቶቹ ጀርባ ግን በዕቅድ፣ በገንዘብ፣ በሀሳብ እና በሰው ሀይል ስልጠና በመደገፍ፣ የሚዲያ ሽፋን እና እገዛ በመስጠት ረገድ የመሪነት ሚናውን ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖች አሉ።
ኢትዮጵያን የማመሰቃቀል፣ የማዳከም እና የማፍረስ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች እነዚህን ቡድኖች እየተጠቀሙባቸውም እንደሆነም አያሌ ማሳያዎች አሉ።
እነዚህ ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ የቆዩት፣ አሁንም በመፈፀም ላይ ያሉት ድርጊቶች የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ስር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ ለሙሉ የሚያሟሉ ድርጊቶች እንደሆኑ በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል።
ይህንን የሽብር ድርጊት የሚፈጽሙ ድርጅቶች አባላትን እና ደጋፊዎችን እንደ ግለሰብ በተናጠል በሽብር ወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቶቹን በሽብርተኛነት በመሰየም በህጉ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይቻላል።
ይህን ማድረግ እነዚህ ቡድኖች በሰላማዊ ዜጎች ህይወት፣ ደህንነት እና ንብረት ላይ እያደረሱ ያለውን ጥፋት፣ በሀገርም ላይ የደቀኑትን ከባድ አደጋ መከላከል ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የትጥቅ ትግሉ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ በሀገር ደረጃ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመጣመር በሀገሪቱ የመንግሥትን ስልጣን ይዞ ቆይቷል።
ሆኖም በፌዴራል መንግሥት አስተዳደር ላይ ጉልህ ሚና ይጫወት በነበረበት ወቅት በተነሳው ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በተፈጠረ ለውጥ ምክንያት ህገወጥ ጥቅማቸው የሚነካባቸው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ሀገራዊ ለውጡ ያመጣውን መንግሥት በኃይል እና በማንኛውም መንገድ ከስልጣን ለማስወገድ በማሰብ በ2011 ዓ.ም የ “ትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ” በማለት ሕገወጥ የታጠቀ ኃይል እንዲደራጅ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወስኗል። ወታደራዊ ኮማንዱን ለማደራጀት እንዲመች በክልሉ ፀጥታ ቢሮ ስር የኃይል ስምሪት ዘርፍ የሚባል አዲስ የስራ ክፍል ተዋቀረ።
ይህ የሥራ ክፍል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት በጡረታ በተገለሉ ጄኔራሎች እና ኮሎኔሎች እንዲመራ ተደርጓል። ወታደራዊ መኮንኖቹ የትግራይ መከላከያ ኃይል የተባለ ወታደራዊ ኃይል ለመገንባት የሚያስችል ወታደራዊ ዶክትሪን አርቅቀው ለሕወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅርቦ ኮሚቴውም ዶክትሪኑ ላይ ተወያይቶ በማፅደቅ እንዲተገበር ወስኗል።
የኃይል ስምሪት ዘርፉ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት እና ቪ.አይ.ፒ ጥበቃ አባላትን በመያዝ ከፍተኛ ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ለጦርነት ያዘጋ ሲሆን በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት ሚሊሻን በደረጃ በመክፈል ለጦርነት ብቁ የሆነ ደረጃ 1 ሚሊሻ የሚባል የሚሊሻ ክፍል በማቀፍ ከፍተኛ የጦር ስልጠና በመስጠት አደራጅቶመ ነበር።
ይህ ደረጃ 1 ሚሊሻ የሚባለው ሰራዊት እድሜያቸው 40 ዓመት ያልበለጡ፣ ሙሉ ጤነኛ የሆኑ እና ጦርነት ላይ ለመሳተፍ የሚችሉ አባላትን የያዘ ነው። ይህኛው የሚሊሻ ክፍል በማንኛውም ሁኔታ ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ ጥቃት ማድረስ የሚችል ሲሆን እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ጊዜ ቀለብ ተሰፍሮለት፤ ደመወዝ የሚከፈለው ስብስብ ነው።
ይህ ዘርፍ የክልሉን ልዩ ኃይል እና ደረጃ 1 ሚሊሻ በብዛት ከማሰልጠን አልፎ ቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ውስጥ አገልግለው በተለያዩ ምክንያቶች ከሰራዊቱ የለቀቁ አባላት አሰባስቦ በጊዜያዊነት እና ቋሚ ቅጥር በመቅጠር ኃይል ማደራጀት ቀጠለ። በተለይም መካናይዝድ መሳሪያ ለመተኮስ ሞያ ያላቸውን እና የተለያየ ወታደራዊ ሞያ ያላቸውን የቀድሞ ወታደሮች በመሰብሰብ ወታደራዊ ኃይል አደራጀ።
የተደራጀው ወታደራዊ ኃይል በማንኛውም ሁኔታ የክልል መንግሥታት ሊታጠቁ የማይገባውን መካናይዝድ እና የቡድን መሳሪያ ስልጠና በመስጠት ለጦርነት ዝግጅት አደረገ።
ወታደራዊ ኃይሉ በዚህ ሁኔታ የጦርነት ዝግጅት ሲያደርግ ዝግጅቱ ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እየቀረበ ይገመገም እንደነበር እና በዝግጅት ሂደቱ የጎደለ ነገር እየተሟላለት እና የስራ አቅጣጫ ላይ መመሪያ እየተሰጠ የበለጠ እንዲጠናከር ይደረግ እንደነበር ከወንጀል ምርመራው ሂደት ማረጋገጥ ተችሏል።
ሕወሓት የፌዴራል መንግሥትን ለመጣል ከነበረው ጽኑ ምኞት በመነሳት ከወታደራዊ ኃይል ዝግጅቱ ጎን ለጎን ሕዝቡ ለጦርነት እንዲዘጋጅ ያደርግ ነበር። ለዚህ እንዲረዳው ድርጅቱ ሕዝብን ማንቃት፣ ማደራጀት እና ማሰማራት ያስፈልጋል በማለት ካድሬዎቹን በማሰማራት ሕዝቡን ለጦርነት ዝግጅት እንዲያደርግ ያነሳሳም ነበር።
በ2012 ዓ.ም መጀመርያ ወራት በድብቅ ዝግጅት ሲደረግለት የነበረውን የጦርነት ፍላጎት “ዘመኑ የመከታ ነው” በሚል ይፋ በማድረግ አንዳችም ጥቃት ሳይሰነዘርበት ጥቃት እንደተሰነዘረበት በማስመሰል ሕዝቡ በሙሉ ተነስቶ የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ ላይ ምንም አይነት ስልጣን እንዳይኖረው እንዲያደርግ ቅስቀሳ ከማድረጉም በላይ በክልሉ ይገኝ የነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ እንዳይችል በየቦታው ኬላዎችን በማቋቋም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ፍተሻ እንዲካሄድበት አድርጓል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በትግራይ ክልል ውስጥ የሚሰራቸው ስራዎች ብቻ የፌዴራሉን መንግሥት ለማዳከም በቂ እንዳልሆነ በመገንዘብ በየክልሉ ችግር ለመፍጠር በማሰብ ለዚህ ዓላማ የሚሆኑትን ቡድኖች መመልመል ጀመረ።
ለአብነትም የአፋር ክልል ላይ ችግር በመፍጠር ደጋፊ እንዲሆነው የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ለተባለ ፓርቲ በጀት በማቅረብ እና የጦር መሳርያ በማስታጠቅ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር።
የአማራ ክልልን ሰላም ለማደፍረስም ከተለያዩ አካላት ጋር ስምምነት አድርጎ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ባደረገው ስምምነት መሰረትም የቅማንት ሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ በሚል ከፍተኛ ገንዘብ እና የጦር መሳርያ በመመደብ በአካባቢው ላይ የሚነሳ ግጭትን በመሳርያ እና ገንዘብ ሲደግፍ ነበር።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ከአፋር ሕዝብ ጋር እንዲጋጭ የመሳርያ ድጋፍ አድርጎ በሕዝቦች መሃል ግጭት ለማባባስ አስቦ ከ100 በላይ ክላሽንኮቭ መሳርያ ለማስታጠቅ ሙከራ አድርጎ በፀጥታ ኃይሎች ክትትል መሳርያውን የሚቀበል ሰው በመያዙ ውጥኑ ሳይሳካለት ቀርቷል።
በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሕዝባዊ ግጭት እንዲነሳ እና ሕዝቦች ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትህ ለሰላም ልማትና ዲሞክራሲ እና የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ለሰላም እና ዲሞክራሲ ለሚባሉ ድርጅቶች የመሳርያ እና ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ግጭት ለመቀስቀስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
የድርጅቶቹን ታጣቂ ኃይል በክልሉ ውስጥ በማሰልጠን እና ወታደራዊ አቅም ግንባታ በመስጠት በክልሎቹ ውስጥ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል ላይ ጉዳት እንዲደርስ እና ዜጎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው በተለምዶ “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራው ቡድን ጋር ውይይት በማደርግ ቡድኑን በገንዘብ እና በመሳርያ በመርዳት የቡድኑን ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ የሰው ህይወት እንዲያጠፉ፣ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ እና ዜጎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል። እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በሕወሓት ሀይል ጥቃት ሲያደርስ የዚህን ቡድን ታጣቂዎች በአጋዥነት አሰልፎ በጋራ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን አጥቅቷል። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል አመፅ ለማነሳሳት እንዲረዳው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን መቐለ ድረስ ወጪ ሸፍኖ በማጓጓዝ ስልጠና እና ገንዘብ በመስጠት በክልሉ ውሥጥ አመፅ እንዲያስነሱ ሙከራ አድርጓል።
በሌላ በኩል በተለምዶ “ሸኔ” በመባል የሚታወቀው ቡድን የትጥቅ እንቅስቃሴውን እንዲያቆም ከሕዝብ የተውጣጡ አባገዳዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የኃይማኖት አባቶችን ያቀፈ ስብስብ ተዋቅሮ ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለስ ጥሪ ተደርጎለት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ይልቁንም በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ውስጥ እንዲሁም ከክልሉ ውጪ በመንቀሳቀስ ሰላማዊ ህብረተሰብን በመግደል እና ከቤት ንብረት በማፈናቀል የሽብር ወንጀል መፈጸሙን ቀጠለ።
በቡድኑ የሽብር ተግባር በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ አደጋ ደርሷል። 112 የፖሊስ አባላት፣ 57 ሚሊሻ አባላት እና 18 በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች ህይወት አልፏል። 76 ፖሊሶች 36 ሚሊሻ እና 2 አመራሮች ላይ አካል ጉዳት ደርሷል።160 መኖርያ ቤቶች 44 ተሽከርካሪዎች እና 84 የመንግሥት መስርያ ቤቶች ተቃጥለዋል።
ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም እስከአሁን በምርመራ በተረጋገጠው መሰረት በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንካ ቀበሌ ንፁሃን ዜጎች ላይ በፈጸመው ጥቃት 36 ንፁሃን ዜጎችን በመግደል እና በርካታ ቤቶች በማቃጠል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ከአካባቢው እንዲፈናቀል አድርጓል።
በጫካ ውስጥ ሆኖ ለሕዝብ እታገላለሁ የሚለው በተለምዶ ሸኔ ተብሎ የሚጠራው ቡድን ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል እና ጥቃት ለማድረስ አባ ቶርቤ የተባለ የገዳይ ቡድን በማዋቀር ይንቀሳቀሳል። ይህ የገዳይ ቡድን በተለይ የመንግሥት አመራሮች ላይ በማተኮር በአሳቻ ሰዓት በመጠበቅ የመንግሥት አመራሮች እና ንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽም ስለመሆኑ የተለያዩ የምርመራ ውጤቶች ያስረዳሉ።
በዚህም መሰረት ከላይ የሽብር ድርጊት ተሳትፏቸው የተብራራው ሁለቱ ቡድኖች የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና ተከታዮቹ መሰረት በአሸባሪነት እንዲሰየሙ የቀረበለትን ምክረ ሀሳብ የኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎ ያጸደቀ በመሆኑ ከዚህ በኋላ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 2 (4) መሰረት አሸባሪ ድርጅት ወይም ቡድን ተብለው የሚጠሩ ሲሆን የመሰየሙ ዓላማም፡-
1. የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 9፣ 29 እና 30 በአሸባሪነት ለተሰየመ ድርጅት ድጋፍ እና እርዳታ ማድረግ፣ በእንደዚህ አይነት ድርጅት በአመራርነትም ሆነ በአባልነት መሳተፍ በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል። ስለዚህ አንድን የሽብር ድርጊት በመፈጸም የሚታወቅን ድርጅት ወይም ቡድን በአሸባሪነት መሰየም ሰላማዊ ዜጎች ከድርጅቱ ጋር እንዳይተባበሩ ለድርጅቱም ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ ይጠቅማል። በመሆኑም ድርጅቶችን በአሸባሪ ድርጅትነት የመሰየም ዋነኛው አላማ በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የሽብር ተግባር ለማስቆም እና ለህግ አስከባሪ አካላትም ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር እና
2. በአሸባሪነት ለተሰየመ ድርጅት የተለያየ እርዳታ የሚሰጡ እንዲሁም አባል የሚሆኑ ግለሰቦችን ለድርጅቱ የሰጡትን እርዳታ ወይም አባልነታቸውን ብቻ በማስረዳት ማስቀጣት የሚቻል በመሆኑ ይህን በመገንዘብ ሰዎች ከእንዲህ አይነት ድርጅት ጋር እንዳይተባበሩ ለማድርግም የሚረዳ ከመሆኑም በላይ አንድ ድርጅት በሽብርተኛ ድርጅትነት ከተሰየመ በኋላ ንብረቶቹ ይወረሳሉ፣ በዚህም የሽብርተኛ ቡድንን የፋይናንስ አቅም ለማዳከም እና በድርጅቱ ሊኖር የሚችለውን የሰው ኃይል ተሳትፎም ለመቀነስ ነው።
ድርጅቶቹን በአሸባሪነት ለመሰየም መነሻ የሚሆኑ ምክኒያቶች እና የመሰየም ሂደቱን በተመለከተም ድርጅትን በአሸባሪነት የመሰየም ስልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በግልጽ ይደነግጋል። በዚሁ ህግ መሰረትም የውሳኔ ሃሳቡ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አማካኝነት ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ሲያገኝ እና ይኸው የውሳኔ ሀሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ሲደገፍ በውሳኔ ሀሳቡ የተመለከተው ድርጅት በአሸባሪ ድርጅትነት ይሰይማል። አንድን ድርጅት በአሸባሪነት ለመሰየም የሚቻለው በአንቀጽ 19 መሰረት ከሶስት አማራጮች ቢያንስ አንዱ መስፈርት ተሟልቶ ሲገኝ ነው። አማራጮቹም፡-
● ድርጅቱ የሽብር ወንጀልን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ እንደሆነ፤
● የድርጅቱ የሥራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጭ አካላት የሽብር ወንጀሉን የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን የመሩ እንደሆነ ነው፤ ወይም
● የድርጅቱን ጠቅላላ መገለጫ ወይም የብዙሃኑን የድርጅቱ ሰራተኞች አፈፃፀም ወይም ድርጊት መነሻ የሚያደርግ ነው።
በዚህም መሰረት በአሰራር ወይም በአፈጻጸም ወንጀሉ የድርጅቱ መገለጫ ሲሆን ወይም አብዛኛው የድርጅቱ ሠራተኛ የሽብር ወንጀሉን በሚያውቁት አኳኋን የሚንቀሳቀስ እንደሆነ ድርጅቱን በአሸባሪ ድርጅትነት ለመሰየም ይቻላል በሚል የተደነገገ በመሆኑ ከላይ ከተጠቀሱት ዝርዝር መነሻ ሀሳቦች እና ምክኒያቶች በመነሳት የድርጅቶቹ ድርጊት የአዋጁን ድንጋጌዎች የሚያሟላ፣ የመሰየም ሂደቱም በሕጉ የተቀመጠውን ሥነ-ሥርዓት በሚገባ የተከተለ መሆኑን መረዳት ይቻላል።