>

በዛሬይቷ ኢትዮጵያ መኖር ይቅርና መሞትም አልቻልንም (አምባቸው ደጀኔ- ከወልዲያ)

በዛሬይቷ ኢትዮጵያ መኖር ይቅርና መሞትም አልቻልንም

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


“ብሎ ብሎ ይሄ ሰው ዛሬ ደግሞ ምን ይዞብን መጣ” እንዳትለኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከዚህ ዘመን በከፋ አስደንጋጭና እንቅልፍ የሚነሣ ሆኖ አያውቅም፡፡ አሁን የምነግርህ ጉዳይ ደግሞ ይበልጥ ያሳብድሃል፡፡

የዛሬውን አያድርገውና በወያኔ ዘመን አንድ ወቅት መብራት የምናገኘው በፈረቃ ነበር፡፡ አንዲት ድሃ አሮጊት ያላቸውን ጥቂት ብር ይዘው ወደገበያ ይወጣሉ፡፡ ጤፉን ሲጠይቁ የያዙት ብር አይበቃም፤ የወጥ እህል ቢጠይቁ፣ አትክልት ቢጠይቁ፣ ላምባ ቢጠይቁ፣ … የጠየቁትን ቢጠይቁ የያዙት ብር ምንም ነገር ሊገዛላቸው አልቻለምና እጅግ ተናደው ባዷቸውን ወደምሥኪን ጎጇቸው ይመለሳሉ፡፡ ቤተሰባቸው ደግሞ የተገኘውን ቀማምሶ እንደነገሩም ቢሆን መኖርን ይፈልጋል፡፡ እንደተመለሱ ቤታቸውን ብቻውን በማግኘታቸው ደስ አላቸው፡፡ ምክንያቱም እቤታቸው እንደደረሱ ኮረንቲ በመጨበጥ ራሳቸውን ለማጥፋት እየዛቱ ነበርና፡፡ ግን እንዳሰቡት ኮረንቲውን ልጠው ሲጨብጡት የሰፈራቸው የመብራት ፈረቃ ያ ቀን አልነበረምና ያቀዱት ሞት ሳይሳካ ይቀራል፡፡ ያኔ ምን አሉ መሰለህ – “በዚህች አገር መኖር አይቻል፤ መሞት አይቻል”፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እኮ ሞትን የሚመኘው እየበዛ ነው፡፡ በፍካሬ ኢየሱስ “በዚያን የመጨረሻ ዘመን ሞትን ይመኙታል ግን አያገኙትም” ተብሏልና ሞትም ይጀነንብን ይዟል ወንድማለም፡፡ ታዲያ ምን ይዋጠን?

ቤተ ክርስቲያን ከሞተች ወዲህ ጳጳሣቱም፣ ካህናቱም፣ ቀዳሽ አወዳሹም በሞላ በመሞቱ ሕዝባችን ያለእረኛ ቀርቶ በቀበሮና በተኩላ እየተነጠቀ በመኖርና ባለመኖር መሀል እየተንከላወሰ ነው፡፡ አንድ ሀገር ከሃይማኖትና ከባህል ከወጣ ደግሞ የምታውቀው ነው፡፡ የሰው ልጅ በነዚህ ነገሮች ካልተገራና ከሞት በኋላ የሚፈራው ነገር ከሌለ የለዬለት ዐውሬ ይሆናል፡፡ ይህንን ደግሞ በሀገራችን በግልጽ እያስተዋልነው ነው፡፡ አንድ ፓትርያርክ ወይንም አንድ ጳጳስ ህገ እግዚአብሔርን በህገ-ሥጋ ለውጦ ዓለማዊ ከሆነ ምዕመናኑን ለጅብና ለቀበሮ መንጋ አስረክቦ ቃለ እግዚአብሔርንም አሽቀንጥሮ ጥሎ የዲያቢሎስ አሽከር ይሆናል፡፡ ከነዚህ የሃይማኖት አባቶች ይልቅ የለየላቸው የሰይጣን ቤተ አምልኮት ካህናትና ምዕመናን ተሻሉ፡፡ እነሱ እቅጭ እቅጩን ነው – አይዋሹም፤ አያታልሉም፤ አያጭበረብሩም፡፡ ከፈለጋችሁ “Church of Satan” በሚል ጠቋሚ ሐረግ ወደ ድረገጻቸው ግቡና አንብቡ (ለየዋሃን ግን አይመከርም! – መወሰድም አለና፡፡) አዎ፣ ከአስመሳይ ዘረኛና ሆዳም አጋንንት የለየላቸው ሉሲፈራውያን የተሻሉ ናቸው፡፡ ብቻ የእምነት ተቋማት በነዚህን ዓይነት የሁለት ዓለም ሰዎች በሚመሩ ጊዜ ሀገር ፈነዳች፣ ተቃጠለች … ሕዝብ በመትረየስ ተረፈረፈ፣ በእሳት ጋዬ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ይህንንም በ“ብፁኣን አባቶቻችን” እያየን ነው፡፡ ሕዝብ ሲታረድ ዝም የሚል አባት፣ አባት አይደለም፡፡ ታፈንኩ ቅብጥርሴ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ መችና ማን አፈናቸው!! በጂጂጋ ለተቃጠለ ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ተብሎ ከአንድ የውጭ ሀገር የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከተላከ 70 ሚሊዮን ዶላር ይሁን ብር የዕርዳታ ገንዘብ ውስጥ 60 በመቶው ለትግራይ ይሂድ ብዬ ላስገድድ የሞከርኩት እኔ አምባቸው ደጀኔ ከሆንኩ ልጅ አይውጣልኝ፡፡ ሃይማኖቱ የውሸት መንግሥታችንም የውሸት፡፡ ፌክ በፌክ ሆነናል፡፡ በወሬ ደረጃ ግን እኛን ቀድሞ የጽርሃ አርያምን ደጅ በናርዶስ ሽቱ የሚያውድና በከርቤ ዕጣን የሚያጥን የለም፡፡ ግብጽ እንኳን ለ1600 ዓመታት ያታለለችን ሞኞች … ቴዲ አፍሮ ተባረክ! ጉራ ብቻ!

የምን ዝባዝንኬ ነው …. ወደተነሳሁበት ልግባ፡፡ ሀገርህ ኢትዮጵያ መኖርም መሞትም የማትችልባት የሌባና የአጭበርባሪ ምድር ሆናልሃለች፡፡ መኖር እንዳትችል እንደምታውቀው ኑሮ እጅግ ውድ ነው፡፡ ሙስናውም ጫፍ በመድረሱ በእጅህ ካልሆነ በእግርህ ሄደህ የምታስፈጽመው አንድም ጉዳይ የለም፤ መብትህን ሁሉ በዜግትነና በሰውነት መብትህ ሳይሆን በገንዘብህ ብቻ ነው የምትገዛው – ቆንጆ ሴት ሆነህ ከተፈጠርክም በማን ዕድልህ – ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ለምን ብትል መሸራሞጥና በገንዘብ ኅሊናን መሸጥ የአጋንንቱ ዓለም ቋሚ መለያ ነውና፡፡ ስለመብትህ መጣስ አቤት የምትልበት ቦታ ደ’ሞ የለም፡፡ በኪነ ጥበቡ ነው የምትኖረው፡፡ ገንዘብ ያለው እንደልቡ ይኖራል፡፡ የሌለው ሞትን እየናፈቀ ይኖራል – አያገኘውም እንጂ፡፡

ሞትን ስትመኝ ታዲያ የመቀበሪያ ቦታ የማግኘትህ ነገር እንቅልፍ ይነሳሃል፡፡ ፉካ ለማግኘት ሰንበቴ ማኅበር መግባት ወይም ከአትራፊ መግዛት ይኖርብሃል – ለሰባት ዓመት ሊዝ፡፡ የሰበካ ጉባኤ ካለህ የተሻለ ዕድል አለህ – ያውም ገንዘብ ካለህ፡፡ ሰበካ ጉባኤ ከሌለህ (ኦርቶዶክስ ሆነህ ማለቴ ነው) ዕዳህ ብዙ ነው፡፡

ለማንኛውም የቤተ ክርስቲያናት የቀብር ቦታ ባለሀብቶች ተከራይተውት አንተ ሬሣ ይዘህ ወደአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንህ ብትሄድ የቀብር ቦታው እንደተከራዬ ይነገርህና ወደኢንቬስተሩ ትላካለህ፡፡ እሱም ያለ የሌለ ምክንያት ይደረድርልህና ከአራትና አምስት ሽህ ብር በታች ስንዝር መሬት እንደማታገኝ በመርዶ ላይ ሌላ መርዶ ይጭንብሃል – እሱ ምን ገዶት፡፡ አንተ ሰው ሞቶብህ ችግር ላይ ነህ፡፡ ቤተ ክርስቲያንህ ደግሞ የቀብር ቦታ ልታሳጣህ ነው፡፡ ዕድር ከሌለህ አስቀባሪ ድርጅት ልትኮናተር ስትሄድ የሌለ ሂሳብ ያሸክሙህና ሀዘንህን በዕጥፍ ድርብ ይጨምሩታል፡፡ መቼም ወግ ነውና ወደሬሣ ሣጥን መሸጫም ጎራ ማለትህ አይቀርም፡፡ የዛሬ አሥራ ምናምን ዓመት 50 እና 60 ብር ይገዛ የነበረው ተልካሻ ሣጥን ዛሬ በሱቲ ጨርቅ ተሸፋፍኖ አሥር ሽህ ብር ስትባል ሻጮቹ የሚሞቱ እንኳን አይመስላቸውም፡፡ “ምናለ ያኔ በሞትኩ” አይባል ነገር፡፡ 

ለነገሩ ይባላል፡- “ምነው አምና በሞትኩ እንዲያ እንዳማረብኝ፤ ሰው እንደበርበሬ ሳይለወጥብኝ፡፡” ይባላልም አይደል? “ያግቡብሽ እምቢ፤ ያውጡብሽ እምቢ” ይሉሃል ይሄኔ ነው፡፡ መኖርም መሞትም ችግር፡፡ በሰሌን ቅበሩኝ አይባል ነገር ሰሌኑም እንደሣጥኑ ዋጋው ተሰቅሏል አሉ፡፡ እሱስ ቢሆን የት ተገኝቶ!

ሆ! እናንትዬ ወዴት እየሄድን ነው? ሃይማኖቱ ከመንግሥቱ ወይም መንግሥቱ ከሃይማኖቱ – አንዱ ከአንዱ አይሻልም? ተያይዘን ቁልቁል እንውረድ? አሁን እኮ በአስተሳሰብ ዶሮም እየበለጠችነ ነው፡፡ ታድላ!

የኔ ቢጤ ድሃው ኑሮውን ግዴለም ሰዎች ሲኖሩ እያዬ በጉምጅት ይኑርና ዘልዛላ ዕድሜውን ይጨርስ፡፡ ሲሞትና ይህን ጉፋያ የምድር ኑሮ ሲገላገል ታዲያ የምን ዕዳ ማብዛት ነው? በገዛ አገሩ መቀበርም ይከልከል? በድህነት ኖሮ ሲሞት እንኳን ሦስት ክንድ መሬት ይጣ? ይህንን እግዜሩስ ይወደዋል? 

ኧረ የግፍ ግፍ ነው! በዚህኛው ዘመነ መንግሥት የመንግሥትም የሃይማኖትም ሰዎች ይህችን መልእክት ከሰማችሁ እባካችሁን ጥጋብና ዕብሪታችሁን ለደቂቃዎች ሰከን አድርጉና የምላችሁን ስሙኝ፡፡ ሰምታችሁም ይህን በኑሮ የተቃጠለ ሕዝብ ሲሞት እንኳን ቤተሰቡን መፈጠሩን ከሚያስጠላ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወጪ ታደጉት፡፡ ሕዝብ አምርሮ እያለቀሰ ነው፡፡ አንዳንዱ በይሉኝታ ተሸብቦ ተበድሮም ተለቅቶም የሚጠየቀውን ሁሉ ይገፈግፋል፤ ግን በውስጡ እየቆሰለና ከፍሎ ለማይጨርሰው ዕዳ እየተጋለጠ መሆኑን የሚረዳለት የለም፤ የተጠየቀውን ሁሉ ሲገፈግፍ የደላው ይመስለናል እንጂ በየቤቱ ብዙ ችግር አለ፡፡ አበሻ ደግሞ “ልጁ ሞቶ፣ ሚስቱ ሞታ፤ ለልጁ ያልሆነ፣ ለሚስቱ ያልሆነ ….” የሚል አቃቂር እንደሚሰነዝር ስለሚታወቅ ይህን ፍራቻ ድሃው ሁሉ በመከራ ቀን ያለ የሌለውን ጥሪት ይከሰክሳል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ግን ቤተሰቡ የሚላስ የሚቀመስ ያጣና ለከፍተኛ ችግር ይዳረጋል፡፡ ያኔ “ኤ!” እያለ ወደላይ ያነባል፡፡  የሕዝብ ዕንባ የሚያመጣውን ደግሞ አሁን ጥጋባችሁ ቢሸፍነውም ጠቅላላውን ትረሱታላችሁ ብዬ አልገምትምና እባካችሁን ለድሃው እዘኑለት፡፡ መኖሩን ብትከለክሉንም መሞትን እንኳን ፍቀዱልን፡፡ ባታውቁትም በኅያው እግዚአብሔር ይሁንባችሁ፡፡ ብታውቁትማ በቃሉ ትኖሩ ነበር፡፡ ሰዎች ግራ ሲገባቸውና አእምሯቸው ሲያስጨንቃቸው መፍትሔ ያገኙ እየመሰላቸው ሃይማኖታቸውን የሚቀይሩትና ከሃይማኖትም ከናካቴው የሚወጡት ለምን እንደሆነ አሁን አሁን ይበልጥ ግልጽ እየሆነልኝ ነው፡፡ ቢሆንም ሰው አይተንና በሰዎች ተመርተን ከምናምንበት ጎዳና አንውጣ፡፡ ሁሉም የሚሰፈርለት በራሱ ሥራና እምነት እንጂ በሌላው አይደለምና ለአብነት አንተ የምትገኝበት የመቶ ሰዎች ቡድን ውስጥ አንተ ብቻ ትክክል ሌላው ግን ስህተት መስሎ ቢሰማህም እንኳን ያን ቡድን ቢቻልህ ለመለወጥና እውነትህ የሌሎችም እውነት እንዲሆን መሞከር እንጂ በብስጭት ጥለህ አትሂድ፤ ነጻ የምታወጣህ እውነትህ እንጂ የመንጋ አስተሳሰብ አለመሆኑን ተገንዘብ፤ እርግጠኛ መሆን የሚገባህ ስለእውነትህ እውነተነት ብቻ ይሁን፡፡ የፓትርያርክና የዲያቆን ነፍስ በአንድዬ ፊት እኩል ናቸው፡፡ በጌታ የፍርድ ሚዛን ተመዝነው ባንተ ምድራዊ ሚዛን ትልቅ የመሰለህ ወደሲዖል ትንሽ የመሰለህ ደግሞ ወደገነት ሊገቡ እንደሚችሉ ካልተረዳህ ሃይማኖት ምን እንደሆነ ገና አልገባህም፡፡ በፈጣሪ ፊት የዶክተር ብፁዕ አቡነ እንቆንቆሳስዮስና የኔ ነፍስ እኩል ናቸው – የሚያለያየን የነፍስ ስንቅ የሚሆነን ቋጥረነው የምንሄደው ሥራችን ነው፤ ሰው እንደሰውኛ ይፈርዳል፤ እግዜሩ ግን እንደመንፈሣዊ አባት ሙላችንን በፍትኅ ይዳኛል፡፡ የሰማዩን ፍርድ ከምድሩ እያቀላቀልነው የምንቸገር ሰዎች እንዳለን እረዳለሁ – አዲስ ነገር እንዳልተናገርኩ(ም) አውቃለሁ፡፡ ማጥፋት ሰውኛ ነውና ባጠፋሁ ይቅርታ፡፡

Filed in: Amharic