>
5:13 pm - Monday April 19, 7943

የሕዝብን ሀብትና የመንግሥትን መዋቅር ለ‹‹ምርጫ›› የመጠቀም ንቅዘት!

የሕዝብን ሀብትና የመንግሥትን መዋቅር ለ‹‹ምርጫ›› የመጠቀም ንቅዘት!

ከይኄይስ እውነቱ


ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ባጠቃላይ፣ በቅርቡ ሦስት ዓመታት ደግሞ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊነት የለም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ሕገ መንግሥት የአንድ አገር ሕዝብ የሚተዳደርበት እና እንዲያስተዳድረው የሚሰይመውን መንግሥት የተባለ አካል ፈቃድ የሚሰጥበት÷ ከሌሎች ሕግጋት ሁሉ የበላይ የሆነ የፖለቲካና የሕግ ሰነድ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥታዊነት (constitutionalism) ግን ጠቅለል ባለ አነጋገር በሕገ መንግሥት መሠረት የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠበትን እና የመንግሥት ሥልጣን ገደብ የሚበጅበትን ሥርዓትና መርህ ይመለከታል፡፡

ወያኔ ሕወሓት እና ኦነግ የጐሣ ሥርዓትና ‹ክልል› የሚባል ‹ጋጣ› የተከሉበትን ‹ሕገ አራዊት› ዘንግቼው አይደለም፡፡ ሕዝብ መከፋፈያ÷ አንድነት ማጥፊያ÷ አገር መበተኛ የ‹ዕዳ ደብዳቤ› መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት የለም የሚለው እምነቴ፣ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ከሚታየው ጽድቅ (እውነት) አኳይ እምነት ብቻ ሳይሆን እውነት እንደሆነ ከበቂ በላይ መገለጫዎችና ማስረጃዎች አሉ፡፡ እውነት የምንለው በአእምሮአችን የሚመላለሰው÷ በልባችን የያዝነውና የተቀበልነው ሃሳብ ከነባራዊው ዓለም ጋር አንድነት ወይም ሥምረት ሲኖረው ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በአገዛዝነት የተሰየመው ቡድንም ሆነ ግለሰብ ኢትዮጵያን እንደ ጠላት ወረዳ ቆጥሮ እገዛዋለሁ የሚለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽብርተኞችን በማሰማራት ያለተጠያቂነት መጨፍጨፍ፣ ማሰር፣ በገፍ ማፈናቀል፣ ሀብት ንብረቱን መዝረፍ ማውደም፣ ማንገላታት፣ ማዋከብ የዕለት ተዕለት መደበኛ ሥራው አድርጎታል፡፡ ባለንበት 21ኛ ክፍለ ዘመን ሌላ የሚያሰብው አገርና ሕዝብ ከሌለ በቀር ማናቸውም መንግሥታት (አምባገነኖቹን ጨምሮ) በገዛ አገሩና ሕዝቡ ላይ ይህንን ነውር የሚፈጽም ያለ አይመስለኝም፡፡

ነፃ ሕግ ተርጓሚ አካል አለ? ሕገ መንግሥታዊነትን የሚያረጋግጥ ነፃ የዳኝነት አካል አለ? በእውነት ሕዝብን የሚወክል እና ሕግ አስፈጻሚውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ሕግ አውጪ ምክር ቤት አለ? ሥልጣኑን እና ገደቡን ዐውቆ የሚሠራ የሕግ አስፈጻሚ አካል አለ? (በሚሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም በእርዳታ አግኝቶ እንደ ግሉ ሀብት ከየትም ላምጣው ለፈለግኩት ጉዳይ ላውለው ማንም ሊጠይቀኝ አይገባም የሚል ጨቅላነትን ከባዶ ድፍረት ጋር በያዘ ግለሰብ እጅ የወደቀች አገር ውስጥ መኖራችንን አንዘንጋ)፤ በነዚህ ሦስት የመንግሥት አካላት መካከል የሥልጣን ክፍፍል፣ የርስ በርስ ቊጥጥርና ምዝዝን ሥርዓት አለ? ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥታዊ ሥልጣን ላይ ገደብ እና ተጠያቂነት አለ? በሕጉ ገጸ-ንባብና መንፈስ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሳችን አሉታ ከሆነ ስለ ሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊነት ማንሳት አንችልም፡፡ 

ከዚህ በላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ሕገ መንግሥታዊነት ላለመኖሩ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን ለአብነት ያህል አነሣለሁ፤

  • የአማራውን ሕዝብ እና የርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣ በአገዛዙ ሙሉ ተሳትፎ ያለ ምንም ተጠያቂነት በሚዘገንን ሁናቴ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመባቸው መሆኑ፤
  • በትግራይ ወገኖቻችን ላይ በአገዛዙ እና በሻእቢያ አረመኔ ኃይል እየተፈጸመ ያለው እልቂት፣ በእናትና እኅቶቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለ አስገድዶ መድፈር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ረሃብ፣ በመቶ ሺዎች መፈናቀል፣ ባጠቃላይ የሚታየው ሰብአዊ ቀውስ፤
  • በኮንሶ፣ በአማሮ፣ በጅማ፣ በወላይታ፣ በጉራጌ፣ በጋሞ ወዘተ. በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸሙና እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች፣ አፈናዎችና ማፈናቀሎች፤
  • የዱርዬ አገዛዝ መገለጫ የሆኑ የፖለቲካ ግድያዎች መበራከት፤
  • አገዛዙ ባሠማራቸው መደበኛ እና ኢ-መደበኛ (ሕገ ወጥ/ ሽብርተኞች) ኃይሎች በጠራራ ፀሐይ ከሚፈጸም ግድያ በተጨማሪ ከተማን የማቃጠል፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩትን ሀብትና ንብረት የማውደም የውንብድና ተግባራት መፈጸም፤
  • ባንድ በኩል በማዕከልና በክፍላተ ሀገሩ መካከል ያለው ግንኙነት ኢትዮጵያ የምትባል አንድ ሉዐላዊ አገርና ኢትዮጵያዊ የሚባል አንድ ሉዐላዊ ሕዝብ የሚያስተዳደርና ለጋራ ጥቅም የሚሠራ ሳይሆን ራሳቸውን በቻሉ ሉዐላዊ መንግሥታት መካከል ያለ ግንኙነት መምሰል፣ በዚህም ሥርዓተ አልበኝነት መንገሥ፤ በሌላ ወገን የማዕከሉ አገዛዝ ባሻው ጊዜ በክፍላተ ሀገራቱ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ በመግባትና ኃይል በመጠቀም ሰላማዊ ዜጎችን መግደል፣ ማሰር፣ ማንገላታት፤ የራሱን ሎሌዎች መሾምና መሻር፤ ሲያሰኘውም ለድብቅ ተልእኮ ያለ ሕግ የአስቸኳይ ጊዜ በማዋጅ ጥቂት በማይባሉ የአገራችን ክፍሎች ወታደራዊ አገዛዝ ማስፈን፤ 
  • የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ (ፍርድ ቤት፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ወኅኒ ቤት፣ ፖሊስ) ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መሽመድመድ (dysfunctional መሆን)፤ በዚህም ዳኝነት ብሎም የሕግ የበላይነት አለመኖር፤
  • ነባር ብሔራዊ ተቋማትን – የመንግሥት፣ የሃይማኖት እና የማኅበረሰብ –  ሥልጣን (mandate) ሳይኖረው በጐሣ ተረኞች ሥር በማድረግ ማሽመድመድ፤ አገዛዙ ለሚያራምደው አገር-አፍራሽ ዓላማ ማዋል፤ ብሔራዊ ምልክት የሆኑ የልማት ተቋማትን ያለ ጥናትና ሕዝብ ፈቃድ ባለቤትነት የማዛወር ሂደት መጀመር፤ 
  • ብሔራዊ ታሪክና ቅርሶችን ሆን ብሎ ማጥፋት ወይም መቀየር፤ ለታይታ የሚሆኑ ‹ፓርኮችን› በሽፋንነት እየሠሩ ነባርና ጥብቅ ደኖችን ማጥፋት፣ አደጋ ሲደርስባቸውም እንደ ጠላት ሀብት ዝም ብሎ መመልከት፣ በዚህም ምክንያት የአካባቢ ጥበቃና የብዝኃ-ሕይወት መናጋትና መመናመን እንዲሁም የአየር ንብረት መዛባት፤
  • መንግሥታዊ ንቅዘት (rampant and deep-rooted government corruption) በመንሰራፋቱና ሥር በመስደዱ  ቢሮክራሲውም ሆነ የመንግሥት የተባሉት ‹የልማት ድርጅቶች› በሥልጣን ካባ በተሸፈኑ ሌቦች የሕዝብ ሀብት ለጥቂት ተረኞች መጫወቻ መሆን፤
  • በአመዛኙ ሥርዓት-ወለድ የሆነውና በጥቂት ዘረኞችና አድርባይ ስግብግብ ነጋዴዎች መሠሪነት የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቶ ገበሬው በመፈናቀል፣ ከተሜው ደግሞ በሥራ አጥነትና አቅም እጦት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለረሃብ መዳረግ፤
  • የሀገር መከላከያን፣ የሕዝብ ደኅንነት እና ሌሎች የጸጥታ ተቋማትን ራሱን በአገዛዝነት ለሰየመው የጐሣ ፓርቲ ፍላጎት፣ ዓላማና ጥቅም በማስገዛት ኢትዮጵያ ብሔራዊ የምትለውና ሕዝቧን ከውጭ ጠላት የሚታደግ ለሰንደቅ ዓላማዋ የሚቆም የመከላከያ ኃይል እንዳይኖራት ማድረግ፤ በዚህም ምክንያት የአገር ዳር ድንበር ተደፍሮና ሉዐላዊነት ተገስሶ በታሪካችን ወራሪ ጠላት ግዛታችን ውስጥ (በአገዛዙ ፈቃድ) ዘልቆ ገብቶ ዜጎችን እየገደለ፣ ሀብትና ንብረታቸውን እያወደመ ተንሠራፍቶ የተቀመጠበት አልፎ ተርፎም አንድ ክፍለ ሀገር በሙሉ ይገባኛል የሚል የድፍረት ጥያቄ ይዞ የተነሣበት ሁናቴ መኖር፤
  • ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጉዳይ ረገድ አገርና ሕዝብን ማስተዳደር ተስኖት በእውር ድንብር የአገራችንን ህልውና ከመቼውም ጊዜ ተወዳዳሪ በሌለው ሁናቴ አደጋ ውስጥ በመክተት መክሸፉን/መጨንገፉን በተግባር አስመስክሯል፡፡ 

እንዲህ ዓይነቱን የወደቀ የዱርዬ አገዛዝ ተሸክሞ የራሱንና የአገሩን ህልውና ሰማያዊ ኃይል በተአምር እንዲታደግለት የሚጠባበቅ ሕዝብ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ውጭ ከቶ የት ይገኝ ይሆን?

እንግዲህ ይህ የከሸፈ የዐቢይ አገዛዝ/‹መንግሥት› ነው በከሸፉ ተቋማቱ፣ እስከ አጥንቱ ድረስ በበሰበሰ ኦሕዴድ/ኢሕአዴጋዊ መዋቅር እና ኢትዮጵያዊነታቸውንና ኅሊናቸውን ለሥልጠንና ጥቅም በሸጡ በሽተኛ ባለሥልጠናትና ድኩማን ካድሬዎች ታጅቦ ‹ምርጫ› እናደርጋለን በማለት አገር እያመሰ የሚገኘው፡፡

ከርእሴ ጋር በተቈራኘ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት እንግዳ ያልሆነ አንድ ትዝብቴን ላንሳና ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡

ከደርግ ዘመነ አገዛዝ ጀምሮ የተተከለው ዝቅተኛ የፖለቲካ አስተዳደር አሀድ ቀበሌ ነው፡፡ በደርግም ሆነ በተከታዮቹ የኢሕአዴግ አገዛዞች ለፖለቲካ ሥልጣን ማስጠበቂያና ሕዝብን መቆጣጠሪያ መሣሪያነት ከመጠለፉ በፊት ቀበሌ ከውጥኑ ለምን ታስቦ በአስተዳደር መዋቅርነት እንደተደራጀ ከዚህ ቀደም ባቀረብኩት አነስተኛ መጣጥፍ ለማንሳት ሞክሬአለሁ፡፡ 

ቀበሌ (በአሁኑ አደረጃጀት ወረዳ) እና ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚሠሩ ቋሚ ሠራተኞች (በየደረጃው ካሉ ምክር ቤቶች አባላትና ተሿሚዎች በስተቀር) የመንግሥት አስተዳደር ሠራተኞች ናቸው፡፡ በተግባር ግን አብዛኛዎቹ የገዢው ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በመሠረቱ በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደር አካላት የመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮች እንጂ የፓርቲ መዋቅሮች አይደሉም፡፡ መሆንም የለባቸውም፡፡ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ግን በተግባር የፓርቲ ዓላማ ማስፈጸሚያ መዋቅሮች ሆነው እያገለገሉ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲና መንግሥት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆን በመለስ የሚመራውና አሁን ደግሞ በወራሹ አረመኔው ዐቢይ የሚመራው ኢሕአዴግ የተባለ የኢትዮጵያ ጠንቅ የተከሉት የአገዛዝ ሥርዓት መርህና የአገዛዛቸው ንቅዘት ዋና መለያ ነው፡፡ 

አረመኔው ዐቢይም ጥርሱን የነቀለበትን ይህን የነቀዘ አስተሳሰብ በመያዝ አሁን እየተወነ ያለውን የማስመሰያ ‹ምርጫ› ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው የመንግሥት መዋቅሮች ወይም የሕዝብ ሀብት እነዚህ የከተማ አስተዳደሮችን ነው፡፡ ለዚህም ነው የአራዳ ክፍለ ከተማ፣ የቂርቆስ ክ/ከተማ፣ የቦሌ ክ/ከተማ ወዘተ ወረዳ …. የብል(ጽ)ግና ምርጫ አስተባባሪ ወዘተ. እየተባለ ለፓለቲካ ፓርቲ ዘመቻ ማካሄጃ ማዕከላት የሆኑት፡፡ ቢያንስ ከሃምሳ በላይ ‹ተቃዋሚ› የሚባሉ የ‹የፖለቲካ ፓርቲዎች› እንዳሉ ይነገራል፡፡ ቅርፃቸውም ሆነ ይዘታቸው የፈለገው ይሁን በጉልበት የተሰየመው ገዢ ፓርቲ የጠቀስናቸው የመንግሥት አካላትን ተጠቅመው የምርጫ ዘመቻቸውን ማካሄድ ይችላሉ? ለምሳሌ የኮልፌ-ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ…. ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በሚል የክ/ከተማውንና የወረዳውን ሀብት ተጠቅሞ ቅስቀሳ ማድረግ ይችላል? ከአድልዎ የነፃ (ሚዛናዊ) እንሁን ከተባለ፤ እውነተኛ ነፃ፣ ፍትሐዊና አሳታፊ ምርጫ ለማድረግ ከተፈለገ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ሀብት እኩል ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን በሕግ መሠረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚፈቀድላቸው የሕዝብ/መንግሥት ሀብት በስተቀር ማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ለምርጫ ውድድር የሚቀርበውና ቅስቀሳ የሚያደርገው ከአባላቱ እና የምርጫ መሠረቴ ነው ከሚለው ሕዝብና አካባቢ ከሚያገኘው ድጋፍ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በወያኔ ወ ኦሕዴድ ኢትዮጵያ ግን የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር (ቢሮክራሲውን ጨምሮ) ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥት/የሕዝብ ሜዲያዎች፣ የ‹አገር መከላከያው›፣ የጸጥታው መዋቅር፣ የፍትሕ አስተዳደር አካላት በሙሉ ለገዢው ፓርቲ ጥቅም በቊጥጥር ሥር ውለው የፓርቲውን ተልእኮ ያስፈጽማሉ፡፡ በዚህም ሳይወሰን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና በግሉ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰብ ባለሀብቶችን መንግሥታዊ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም (በማስገደድ/በተጽእኖ) የማይደግፉትን የፖለቲካ ድርጅት በፋይናንስና በማቴሪያል አለፍ ሲልም ካናቴራ በማስለበስና በማናገር ንቅዘት የተሞላበት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያስገድዳሉ፡፡ ይህ በምርጫ ስም ማፌዝ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ሲፈጸም የቆየና አሁንም የቀጠለ የብልግና አሠራር ነው፡፡ ብል()ግናም ከግብሩ ጋር የሚሰምረውን ድርጊት እየፈጸመ ነው፡፡  

ለማጠቃለል ኢትዮጵያ በምትገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ እንኳን የፌዝ እውነተኛም ምርጫ አያስፈልጋትም፡፡ ደጋግሜ እንደተናገርኹት በምርጫ የሚፈታ የኢትዮጵያ ችግር የለምና፡፡ የዜጎች እልቂት፣ መፈናቀል፣ እስርና እንግልት ባጠቃላይ የሽብር ተግባር መደበኛ የሕይወታችን አካል ሆኖ ሰላምና ደኅንነት በራቀበት አገር፣ የአገር ቀጣይነት አሳሳቢ በሆነበት አገር፣ ወጥቶ መግባት ብርቅ በሆነበት አገር ወዘተ. ምርጫ እያሉ ማቧለት ዕብደት ካልሆነ ምን ይሉታል? በማንነትና ዜጎች በሚከተሉት እምነት ምክንያት የሚፈጸመው ዘግናኝ ግፍ ሳያንስ፣ የሕዝብ ሀብትና የመንግሥት መዋቅሮችን ተቆጣጥረው ለማስመሰያ ምርጫው ማስፈጸሚያ ማዋሉ ሳያንስ፣ በገጠር በከተማ ለማጭበርበር የሰለጠኑ ደናቁርት ካድሬዎችና የሐሰት ትርክታቸው ሰለባ የሆኑ ወጣቶችን ማሰማራታቸው ሳያንስ፣ ፊደል የቈጠሩ ሆዳም አድርባዮችን ለእጩነት ማዘጋጀታቸውና ለሐሰት ፕሮፓጋንዳ በውጭ ያሉ ታማኝ ሜዲያዎችንና የሚመሯቸውን ወራዳ ግለሰቦች መግዛት ሳያንስ፣ በአ.አ. ወጣቶችን በቤት፣ በቦታና በገንዘብ ለመደለል የሚደረገው ወራዳ ተግባር ሳያንስ… የውሸት ምርጫ አድርጎ ግፍና ጭቆናን የበለጠ ለማጽናት አንድ የሆነውን የሰሜኑን ሕዝብ በማጋጨት ከፖለቲካ ጨዋታ ውጭ ለማድረግ በተግባር እየተተረጐመ ያለ ሸፍጥ፣ ለሺህ ዓመት በሰላምና በመከባበር የኖሩትንና ለቀረው ዓለም የአብሮነት ምሳሌ የሆኑትን የርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ለማጣላት ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የሚሸረበውን ሴራ ስናስተውል አገዛዙ እጅግ አረመኔ፣ ፈሪና ምንም የሕዝብ መሠረት እንደሌለው እንረዳለን፡፡ 

በውስጥም በውጭም የምትገኝ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ሆይ!!! ውጤቱ ከወዲሁ የታወቀው ይህ የሐሰት ‹ምርጫ› ቢደረግም ባይደረግም ከሰው በታች ያዋረደንን ቀድሞ በወያኔ ሕወሓት አሁን ደግሞ ኦሕዴድ በሚባል ዘረኞች ቡድን የገለማ ሥጋ ለብሶ የሚንከላወሰውን ኢሕአዴግ የሚባል ሰይጣናዊ ቡድን እስከነ መዋቅሩ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ከአካይስቶች ለመታደግ ወገባችንን አጥብቀን በኅብረት መነሣት ይኖርብናል፡፡

Filed in: Amharic