>

ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ ናት!!! (ማኅበረ ቅዱሳን)

ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ ናት!!!

ማኅበረ ቅዱሳን

*… በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ!
 
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ ውጊያ ሲደረግባት ቆይaል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ውጊያ በጊዜ ሂደት መዋቅራዊ ወደመሆን እያደገ ሄዶ አሁን ያለንበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ በነዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ ሲካሄድ የቆየውን ጥቃት ማሳያ የሆኑ በርካታ ክስተቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለምሳሌ ባለፉት ዓመታት በየአካባቢው የሚደረጉ የክርስቲያኖች በክርስቲያንነታቸው ተለይተው መገደል መሰደድ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና የምእመናን ሀብትና ንብረት መዘረፍ አንዱ ሲሆን የማንነትዋ መገለጫ የሆኑት ሀብቶችዋን ከዳር እስከ መሀል የመቀማትና የማጥፋት ብሎም ለሌሎች አካላትና አገልግሎቶች እንዲውሉ መደረጉ ደግሞ ሌላኛው ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
በተለይም ባለንበት ዘመን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረገውን ጥቃት ለየት የሚያደርገው ነጻነት፤ እኩልነት መቻቻልና እና አብሮ መኖር የሚሉ ቃላትን ሽፋን ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ ነጻነት፤ እኩልነት እና ሌሎችን እንደራስ አድርጎ መውደድ መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮ እንደመሆኑ መጠን ክርስቲያኑ ይህንን ባህል አድርጎ ሲኖረው ቆይaል፡፡ በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ እስከ አሁን ያለውን መከራና ጥቃት የሀገርን ሰላምና አንድነት በማስቀደምና በአርቆ አሳቢነት እንዲሁም ነገሮች ሊለወጡና ሊሻሻሉ ይችላሉ በሚል ተስፋ  በትዕግሥት ሲያልፍ ቆይቶዋል፡፡ ሆኖም ግን ጉዳዩ ከመሻሻል ይልቅ በየቦታው ሲደረግ የነበረው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማንነትዋ መገለጫ የሆኑ የእምነት ቦታዎች መነጠቅ እየባሰ መጥaል፡፡ ከዚህም የተነሳ በገጠር የተጀመረው ቅድስት ቤተከርስቲያን ለአደባባይ በዓላት የምትጠቀምባቸውን የአምልኮ ቦታዎች መቀማትና ለሌላ አገልግሎት መስጠት እያደገ መጥቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓል የምታከብርበትን የመስቀል በዓል ማክበሪያ ቦታ ለሌላ አገልግሎት የማዋልና አሳልፎ ለመስጠት ሙከራዎች ማየት ደረጃ ላይ መድረሳችን ጥቃቱ ከፍተኛ ደረጃ ለመድረሱ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ ጋር ይዘቱ ምንም ይሁን ምን ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደ ሰው የሚሰማቸውን ስሜትና ሀሳባቸውን መግለጽ መቻላቸው ተፈጥሮአዊ መብት ሆኖ እያለ የእርሳቸውን ንግግር ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት እንደ ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ሲኖዶሱን ለመከፋፈልና ለማዳከም ብሎም ተÌማዊ አንድነትዋን ለማናጋት የሚደረገው ርብርብ በእጅጉ የሚያሳዝን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በተጨማሪም ለዚህ ቤተ ክርስቲያንን የማሳደድ ተግባር የራስዋን አካላት ለጉዳዩ መጠቀሚያ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት ጉዳዩን በእጅጉ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
እነዚህን ሁሉ በአንድ ላይ ስናያቸው ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና ለሌሎች አካላት ቀርቶ ለሁሉም ክርስቲያኖች እኩል ግልጽ ባልሆነ መንገድ ቤተ ክርስቲያን በስደት ላይ መሆንዋን ያሳያል፡፡
ስለዚህ:-
1ኛ፡ ሁላችንም ሕዝበ ክርስቲያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በስደት ላይ መሆንዋን ተረድተን እንደ ቀደምት አባቶቻችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ስደት በተቀበሉበት መንገድ ለመቀበል መዘጋጀት አለብን፡፡
2ኛ፡ የቤተ ክርቲያን አካላት ሆናችሁ ነገር ግን ይህንን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ስልታዊ እና የረቀቀ ጥቃት ባለመረዳት በተለያየ ደረጃ የችግሩ አካል በመሆን ላይ ያላችሁ ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እናሳስባለን፡፡
3ኛ፡ በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጣችሁ የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅና ምእመናንን ለመጠበቅ የተሰጣችሁን አደራ ለጊዜያዊ ጥቅምና የፖለቲካ ፍላጎት መጠቀሚያ ያደረጋችሁ አካላት ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በተያያዘ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅናና መመሪያ ውጭ እና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ባልተከተለ መልኩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
4ኛ፡ ሀገር እና ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ይህንን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተደረገ ያለውን የተቀናጀና የተደራጀ መገፋትና ስደት በመረዳት ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንዲቆሙ እና ችግሮቹን ለማስወገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡፡
5ኛ፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የመንግሥት መዋቅርን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያናችንን በልዩ ልዩ መንገድ ሲያጠቁ ክርስቲያኖችን ሲገድሉና ሲያሳድዱ ሲያፈናቅሉ እንደነበር መንግሥት ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም መንግሥት አንድም ጊዜ በይፋ ይቅርታ ጠይቆ አያውቅም፡፡ በአንጻሩ ሌሎች አካላት በቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታዎች ላይ ያለአግባብ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ለመስጠት በሚያደርገው ሂደት ረጅም ርቀት በመሄድ ይቅርታ ሲጠይቅ ይታያል፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ስደት በመንግሥት የሚፈጸም ጥቃት ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል፡፡ ስለዚህም መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው ስደት እንዲቆም የማድረግ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
6ኛ፡ መንግሥት ውሳኔዎችን ሲወስን አሁን እየታየ ባለው መልኩ በጩኸትና የቤተ ክርስቲያንን መብት በመግፋት ፍትሕ እያዛባ የሚሄድና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ስደት እንዲቆም የማድረግ ድርሻውን የማይወጣ ከሆነ ለሚደርሰው ሰላም ማጣትና ችግር ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
7ኛ፡ በመጨረሻም ምእመናንን ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚኖሩ ቀጣይ ሁነቶችን እየተከታተልን የምንገልጽ መሆኑን ተረድተው በንቃት እንዲከታተሉ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
ማኅበረ ቅዱሳን
Filed in: Amharic