“ከገባንበት የፖለቲካ ማጥ ለመውጣት፣ከስሜት የፖለቲካ ደጋፊነት መውጣት ብንችል….?
ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
መግቢያ
(ይህ ዘገባ ያዘጋጀሁት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር አዛምጄ ለአንባቢዎቼ ሃሳቤን ለማካፈል ነው፡፡ )
የዛሬ አርባ አመት ግድም ( ያንዬ የ10 አመት እምቦቀቅላ ህጻን ነበርኩ)፣ ስጋ ከማይመገቡ ሰፈር የነበሩ ሻለቃ የኔነህ የሚባሉ ጎረቤታችን ነበሩ፡፡ ሻለቃ ከአትክልትና ቅጠላቅጠል በቀር ስጋ ያለበት ድርሽ አይሉም፡፡ የአራት ኪሎ አድባሮች ለነበሩት ስጋቤቶች በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ደጃች ውቤ ሰፈር ነዋሪ ቢሆኑም ሻለቃ ለቁርጥ ስጋ የሚከፈት አፒታይት አልነበራቸውም፡፡ ሻለቃ በልጅነት አይምሮዬ የቀረጹብኝ ይህ ጸባያቸው እኔም በአብዛኛው ወደ ቅጠላቅጠሉ እንዳዘነብል ሳይረዳኝ አይቀርም፡፡ “ዛሬ እኔ የምወደውን ሰላጣ በተገኘው አጋጣሚ ለመመገብ እሞክራለሁ፡፡ ቁምነገር የሰራሁ መስሎኝ አንዲት የውጭ ሀገር ዜጋ ትንሿ ለምግብ ማዘጋጃ፣ ለመኝታና ለእንግዳም ማስተናገጃም ጭምር እምጠቀምባት አንዲት ክፍሌ ጋበዝኳት፡፡ የቃርያው ማቃጠል ብቻ ሳይሆን ሎሚውንና ጨውን አበዛሁት መሰለኝ ወሃ በብርጭቆ አምጥታ ፉት እያለች በእጇ ምላሷን ለማቀዝቀዝ እያራገበች፣ “ሰላጣውን ለምን ደበከው?” አለችኝ፡፡ የቆራረጥኩትን ዳቦና ሰላጣውን ወደ እሷ ገፋ አድርጌ “ምናልባት መነጽርሽን ማስመርመር ሊኖርብሽ ነው” ስላት፣ ትኩር ብላ አይታኝ “ከመነጽሬ አይደለም ከጆሮዬ መሰለኝ ሰላጣ እወዳለሁ እንጂ እንዲህ እንደምትጠላ የነገርከኝን አላስታውስም”ብላ አሳቀቺኝ፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን ስጋ ወይንስ አጅቦት ለሚመጣው ቅመማቅመም ነው ትኩረት የሚሰጡት ?
በተለምዶ አነጋገር ኢትዮጵያውያኖች ስጋ እንደምንወድ ተደርጎ ለረዥም ጊዜ ሲነገር መስማት የተለመደ ነው፡፡ እኔም ይህን እንደወረደ ተቀብዬ እስከተወሰነ ጊዜ ባምንበትም በሂደት አስተያየቴ ተቀይሯል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያኖች ስጋ መልኩን፣ ሽታውን፣ ወይ አጅቦት የሚመጣውን ቅመማ ቅመም እንጂ፣ የስጋ ጣእም ያለው ነገር ብዙዎቻችን በፍጹም አንወድም የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ለዚህ ድፍረት ለተሞላበት የግል አስተያየት በጥናት የተደገፈ ጽሁፍ አግኝቼ ለማንበብ አልቻልኩም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለረዥም ዓመታት የተለያየ የኢትዮጵያኖች የባህል ምግብ ንግድ ቤቶች ባለቤቶችን ወይም ባለሙያዎችን ስላነጋገርኩ፣ በመጠኑ ስለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቼ እንዳስብበት ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩኝ፡፡
ብዙዎቻችን ከስጋው የበለጠ በፍቅር የምናጣጥመው አብሮት ያለውን ቅቤ፣ ሚጥሚጣ፣ ጨው፣ ኮረሪማ፣ ኮሰረት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል.…ወዘተን እንጂ ስጋውን አይደለም የሚሉ በርካታ ግለሰቦች አጋጥመውኛል፡፡ እንዲያውም ያን የመሰለ ሽንጥ፣ ሻኛ፣ ፍርምባና የክትፎ ጣእም ላለመቅመስ በጨው የተፈጨው ሚጥሚጣ መፋጀት ሳያንስ፣ በላዩ ላይ ሌላ ጨውና ሰርን በሚበጥስ ሰናፍጭ፣ ሎሚና መጠኑ የበዛ አልኮል በርበሬ በገፍ ሲገባበት፣ ስጋው ቅመም፣ ቅመሙ ስጋ ሆኖ ቦታቸውን ይቀያየራሉ፡፡ አዋዜ፣ ቆጭቆጫ/ዳጣ የመሳሰሉት ከሚያቃጥሉና ከሚጎመዝዙ ነገሮች ተቆነጥጣጥረው እንደ መድሃኒት በጥንቃቄ ሲቀምሙት፣ ስጋው ውስጥ ሳይሞት አምልጦ የተረፈውን ነብስ ለመጨረስ የሚደረግ ዳግማዊ ዘመቻ ነው የሚመስለው፡፡
እንደዚህ ተገደን ወይም ስለት ተስለን የምንበላ የሚመስለው ዋናው ምክንያት ግን፣ ጥሬ ስጋ፣ ክትፎ፣ ጥብስ፣ ቅቅል፣ ወጥ ውስጥ ያለውን የስጋ ጣእም ላለመቅመስ ወይም ለመሸሽ ብቻ ነው፡፡ ስጋውን ከምንቀምስ ምላሳችንን ብናቃጥል፣ ጨጓራችንን ብንልጥ፣ መጸዳጃችንን ብንጎዳ እንመርጣለን፡፡
እራሳችንን ግን ስጋ በጣም እንደምንወድ አድርገን፣ ሲያወሩ የሰማነውንና በደመነብስ የተላለፈልንን ተቀብለን አምነን እያስተጋባን እስካሁን ኖረናል፡፡ ከዚህ የምናስተውለው ሃቅ ብዙዎቻችን እንወደዋለን የምንለውንና በተግባር የምንሰራውን ምን ያህል እንደሚራራቅ አስበንበት እንደማናውቅ ነው፡፡
እኛ እና ፖለቲካ ምንና ምን ?
ከላይ ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት ብዙዎቻችን በብዙ ነገሮች፣በየእለት፣ተእለት የህይወት እንቅስቃሴአችን ወዘተ ከስሜት ወይም ከደመነፍስ እንቅስቃሴ ራሳችንን ለመግታት የምናደርገው ጥረት እምብዛም ነው፡፡ ይህን የደመነፍስ ባህሪያችንን ለማየት የፈለገ ሰው በአንድ ሚኒባስ ውስጥ ገብቶ ትራጄዲክ ድራማውን ማረጋገጥ ይቻለዋል፡፡( ሁላችንንም አላልኩም፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በደምሳሳው የምወቅስ ተላላ ሰው አይደለሁም፡፡ ለዚች ሀገር ታላቅ ቁም ነገር ሰርተው ያለፉ፣ዛሬም በህይወት ያሉ፣ከስሜት ፖለቲካ የራቁ ጎምቱ ኢትዮጵያውያን ሞልተው ተርፈዋል፡፡) በነገራችን ላይ እንደው ዝም ብሎ በስሜት አንድን ነገር ገቢራዊ ለማድረግ መሞከር እርባና የለውም፡፡ ስሜት ብቻውን ምክንያታዊ ሊያደርገን አይቻለውም፡፡ አስበን አመዛዝን የምንደግፈውን መደገፍ ፣ የምንቃወመውንም በሰውነት ደረጃ ላይ ቆመን ፣ በምክንያት ቢኮን መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ለማናቸውም በፖለቲካውም እንዲሁ ነን፣ “ኢትዮጵያችንን፣ ሕዝባችንን፣ ባሕላችንን፣ ቋንቋችንን፣ ኃይማኖታችንን፣ ነገዳቸውን” ከልብ የሚወዱ የሚመስላችው ጥቂት የማይባሉ በሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ “ሰዎች” መውደዳቸውና ፍቅራቸው በተግባር ከሚሰሩት ጋር ሲነጻጸር እንደ “የጥሬ ስጋው ፍቅር” የተገላቢጦሽ ነው፡፡
ለብዙዎች የፍቅርና የጥላቻ ቦታውን ቀያይረው ሲጠቀሙበት ስለኖሩ፣ የሚወዱትን “በፍቅር” ለጥቃት ሲያጋልጡትና ሲጎዱት እንዳያስተውሉ አፍዝ አደንግዝ የተደገመባቸው ይመስላሉ፡፡ በደመ-ነብስና በስሜት ብቻ ዓይናችንን ጨፍነን የተከተልነው መንገድ ወዴት ሊያደርሰን፣ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለማሰብና ለመመርመር ልማዱም ሆነ ትግስቱ ስለሌለን ውጤቱ የት አንዳደረሰን አሁን ማየት ይቻላል፡፡
አለማወቅን እንደ ወንጀል፣ መጠየቅን እንደ ድክመት ስለምንወስድ ማስመሰል ወይም አድርባይነት ጌጣችን ሆኖ ኖርዋል፣ ቀጥሏልም፡፡ በወጣትነታችን ዘመን ከቤተሰብ፣ ከአካባቢያችን፣ ከማኅበረሰባችንና ባጠቃላይ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር ጭምር ከሁሉም እያጣቀስን፣ የሚጎዳንንና የማይጠቅመውን ሳናስወግድ፣ እንደወረደ ሁሉንም ሰብስበን በአዕምሮዋችን በላይ በላዩ የጠቀጠቅናቸው ተደበላልቀውብን ያስከተለው የቀውስ ውጤት ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡
“የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ …” የሚለውን ቀረርቶ እየሰማን አድገን፣ ባናቱ ላይ ማሞ ቂሎን፣ ተንኮለኛው ከበደንና ለማ በገበያን ያነበበው የኔ ትውልድ፣ አድገን ፖለቲካውም ላይ በተወሰነ ደረጃ የማሞን ባህሪ አላንጸባረቅንም ማለት አይቻልም፡፡ ሀሰት የምትሉ ካላችሁ በሃሳብ መሞገት ይቻላል፡፡
“ባሌ ቀንቶ ካልደበደበኝ የሚወደኝ አይመስለኝም” ብላ ከምታምን እናት ተወልዶ ያደገ ወጣት፣ ምናልባት በራሱና ባካባቢው ተጽእኖ ከዚህ አስተሳሰብ ካላመለጠ? የሚወደውን ከመንከባከብና ከማሽሞንሞን ይልቅ በመጉዳትና በማበላሸት ነው ፍቅሩን የሚገልጸው ብል ማጋነን አይመስለኝም፡፡
“ጥራኝ ዱሩ፣ ጥራኝ ደኑ…” ወዘተ ቀረርቶ እየሰማ ላደገ ወጣት በቡጢ እየጠለዘህ “ቻለውን” እንጂ፣ ስለ መቻቻልና የጋራ ብሔራዊ ጥቅም ለማስረዳት በተለይ በዚህ ጊዜ፣ ጉንጭ ማልፋትና ጨጓራን መላጥ ነው ትርፉ፡፡ (እንደዛ አይነት ግጥም በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ባህሎችና ቋንቋዎቻችን ውስጥ አሉ)፡፡
በግትርነት እና በጽናት መሃከል ያለውን ልዩነት እንደ ጥሬ ስጋው ፍቅር ተምታቶብን ስለቀያየርነው፣ አንዴ ሳናውቅ ገብተን ከጀመርነው አፍራሽ ተልኮ ማፈግፈግ መርህን መጣስ አድርገን እንድናይ አፍዝ አደንግዝ የተደገመብን ይመስላል፡፡ በመሪዎቻችን ላይ የምናየውን ስህተት እርምት እንዲያደርጉ መውቀስ ማህተብን እንደመበጠስ፣ ወይም እራስን ከተሳሳተ አቋም ለማረም መሞከር የቁርባን ጋብቻን እንደማፍረስ ያህል ነው የምንቆጥረው፡፡
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው፣ ያሉብን ድክመቶች ሳያንሱ፣ የፖለቲካው ሰፈር ለመተዳደርያ የገቢ ምንጭም ሊሆን እንደሚችል ቀድመው የተገለጸላቸው አጭበርባሪ የግጭት ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ፖለቲካም እንደ ሸቀጥ “በአትራፊነቱም” የነጋዴውን ማኅብረሰብ ማስናቁና ባጭር ጊዜ ወደ ከፍተኛ የስልጣን ማማ ጭምር ማድረሱ በጎሰኛ ምሁሮች እይታ ውስጥ ስለገባ፣ “አንቱ የተባሉ” ቱባ ቱባ ጎጠኞች ከየማኅበረሰቡ እንደ እንጉዳይ መፍላትና፣ የባቢሎንን ሕንጻ ገንቢዎችን የሚያስንቁ ወዶ ገብ የተትረፈረፉ ጭፍን ተከታዮች ማግተልተል መቻላቸው ሁኔታውን የከፋ አድርጎታል፡፡
እነዚህ በተለያዩ ስፍራዎች አሸምቀው ያሉ የግጭትና የጎሳ ፖለቲካ ነጋዴዎች፣ በጸረ ኢትዮጵያዊነት ላይ ተመሳሳይ አቋም ስላላቸው ለጊዜው በጥቅም እስከሚጋጩ ይተባበራሉ፡፡ ይህንንም በተጨባጭ እየተመለከትን ነው፡፡ሁሉም ትርምስ ቀውስና ጦርነት ሲኖር ነው ገበያቸው የሚደራው፡፡ ሁሉም ልዩነትን እያራገቡ ችግሩን የሚያባብሱና “ቆመንለታል” “እንወደዋለን” የሚሉትን ሕዝብ፣ ለአራጆች እያመቻቹ በማስጨረስ ለራሳቸው መተዳደሪያ ገቢ የሚፈጥሩ ከእብድ ውሻ የከፉ ጨካኞች ናቸው፡፡
ህብረት፣ መቀራረብ፣ መተጋገዝ ሲጀመር የነሱን ተፈላጊነት ስለሚያሳንስ ብርክ ይይዛቸዋል፡፡ የትብብርና የአብሮነትን መንፈስ ይዘው ገና ብቅ የሚሉትን አናት አናታቸውን በመቀጥቀጥና በማሸማቀቅ የተካኑ ናቸው፡፡ ሴራ በመጎንጎንና እርስ በእርስ የማጋጨት “ተፈጥሮዋቸው ያደላቸውን” ተንኮል በመጠቀም ሁሌ ህብረትን የመበተን ችሎታ አላቸው፡፡ የዘር ፖለቲካ፣ የዕምነት ስፍራዎች፣ የመረዳጃ ማኅበራት ብቻ ሳይሆኑ፣ ቴክኒዮሎጂ የፈጠረው፣ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ዙም፣ ፓልቶክና ማኅበራዊ ድኅረገፆች ዋና መደበቂያ ዋሻዎቻቸው ናቸው፡፡
እንዚህ በየማህበረሰቡ ያሉ ተንኮለኛ የቀውስ ነጋዴ ዘረኞች፣ በተለይ በውጪው ዓለም የሚኖሩት፣ ተምረው ትልቅ ደረጃ መድረስ ወይም ሰርተው እራሳቸውን ማሻሻል የሚችሉበት እድል ያለበት ሀገር ለብዙ ዓመታት እየኖሩ በራሳቸውም ስንፍና ጭምር የግል ሕይወታቸውን እንኳን መምራት የደከማቸው፣ አተራምሶና አጋጭቶ መጠቀምን እንደ ሙያ ሌላውን ማንነታቸውን የገነቡ አምታቾች (ቁጭበሉዎች)፣ የአንድ መቶ አስር ሚሊዮንን ሕዝብ ችግር የሞቀ ቤታቸው ቁጭ ብለው በየሶሺያል ሚዲያውና በዩቲዩብ ባገኙት የተሳታፊዎችና የላይክ ቁጥር ብዛት አሳድጎ የሸቀጥ ማስታወቂያ ሳንቲም ለመሰብሰብ ነው፡፡
ትንሽ የሆነውንና ያልሆነውን እየደበላለለቁ፣ የተጋነነና የውሸት ቆርጦ ቀጥል “ሰበር ዜና” እየፈበረኩ ኅብረታችንን ለማደፍረስ ለጠላት አድረው አማራ መስለው ኦሮሞውን፣ ኦሮሞ መስለው አማራውን የጠቀሙ እያስመሰሉ በመሳደብና ማኅበረሰቦቻችንን በመጋጨት ለጠላት እቅድ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ሀገራችንን ወደ ሲኦል ለመቀየር እየሞከሩ ላሉት አክራሪ ብሔረተኞችና የአካባቢያችን እስትራቴጂክያዊ ጠላቶች በሎሌነት እያገለገሉ እንዳሉ ኅሊና ያለውና የዘር ጎራ ያልመረጠው ማስተዋል አይሳነውም፡፡ በነገራችን ላይ ሱዳንን የመሰለ ታሪካዊ ጠላት ድንበር ተጋሪ ያላት ሀገር ዜጎች፣አርስበርስ መናቆር ሲስተዋል በእውነቱ ለመናገር የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ሱዳን በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ተኝታ አታውቅም፡፡ሱዳን ክፉ ጎረቤት፣ምቀኛ የድንበር ተጋሪያችን ሀገር ናት፡፡
እውቀትን ለተሳሳተ ዓላማ የሚጠቀሙበት የጎሳ ልሂቃንም፣ “የኛ” የሚሉትን ማኅበረሰብ ከጎናቸው ለማሰለፍ፣ በዓለም ላይ ከተካሄዱ የፋሽስት/ናዚ ድርጅት እንቅስቃሴዎች፣ ፋሽስት መሪዎቹ እንዴት ሕዝባቸውን አሳስተውና አነሳስተው ከጎናቸው ማሰለፍ እንደቻሉና፣ የሕዝብን ስነ ልቦና ለመስለብ የቱ ቦታ ደካማ ስሜቱን ኮርኩረው ለማነሳሳት እንደተጠቀሙበት፣ ከውጭው ዓለም ከታሪክ መጽሃፍት ሥራችን ብለው በመመርመርና በማጥናት፣ ይህንን ፋሽስታዊ መርዝ ጽንሰ ሃሳባቸውን ቀምመውና ጠንስሰው ከሀገራችን ሁኔታ ጋር አዳቅለው በሕዝባችን ውስጥ በማሰራጨት ወገኖቻችንን እርስ በእርስ እያጫረሱ እንዳሉ በተጨባጭ የስራቸውን ውጤት በየስፍራው የሚደርሰውን አደጋ ማየት ይቻላል፡፡
ጤነኛ ሰው ከመጽሃፍ ዓለም ታሪክንና ጠቃሚ ተመክሮዎችን ተምሮ፣ ከራሱ አልፎ ሀገሩንና ወገኑን በመርዳት ቁምነገር ይሰራበታል እንጂ፣ ለስልጣንና ለጥቅም ብሎ “እወደዋለሁ”፣ “ለሱ ቆሚያለሁ” የሚለውን ሕዝብ “እንደ ቁርጥ ስጋው ፍቅር” ለመጉዳት አይጠቀምበትም፡፡
ከችግሩ እርቀው ሠላም ያለበት ሀገርና የሞቀ ቤታቸው ቁጭ ብለው፣ ቆመንለታል ለሚሉት ማህበረሰብ ስም፣ አብሮት በሰላም የሚኖረውን ወገኑን እየተሳደቡ በማዋረድ፣ ለራሳቸው የቂምና የጥላቻቸውን ጥማት እየተወጡ፣ “ለሚወዱት ሕዝብ” ጠላት እየገዙለትና እንዲጠቁ ምክንያት እያመቻቹላቸው በሌሎች የነሱ ቢጤ ጨካኞች ያሳርዱትና፣ እንደገና በተከተለው አሰቃቂ በደል ለሌላ የቀውስ አዙሪት ሙሾ እያወረዱ፣ ለሌላ ዙር ጥቃት ሁኔታውን ሲነግዱበት ማየትና መስማት፣ ምን ያህል “እንወደዋለን የሚሉትን ሕዝብ” ጠላት ከሚሉት ባላነሰ መንገድ እንደሚጎዱትና ለአደጋ እንደሚያጋልጡት የማንሰማበት ቀን የለም፡፡
ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደሚሰማው በባእድ ሀገር የሚንከራተተውን ኢትዮጵያዊ በየጊዜው ማታለላቸው አሳዛኝ ዜና ነው፡፡በዚህ ቀውስ መሃል የጽንፈኞቹ እይታ የሚያነጣጥረው የዋሁ ተከታዮቻቸውን ኪስ በጎፈንድ.. እያራቆቱ በሕዝብ ስም በወገን ደም መክበርን ነው፡፡ (በእርግጥ በአንጻሩ ብዙ ችግር ላይ ያሉ ወገኖቻችንን በጎፈንድሚ… በመርዳቱ በጎ ተግባር የሚደክሙት ሃቀኛ ወገኖች እንዳሉ ሳይዘነጋ! ለአብነት ያህል ኢትዮጵያዊው አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጋሼ ታማኝ በየነና አብረውት የሚሰሩት ኢትዮጵያውያን፣ ሌሎችም በርካታ የሰብዓዊ እርዳታ ሀገር ቤት ለሚገኙ ተጎጂ ወገኖቻችን የሚያርቡ ኢትዮጵያውያን ስማቸው ከመቃብር በላይ በወርቅ ቀለም የሚጻፍ ነው፡፡)፡፡
በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ዘረኞች ስሜታቸውን መቆጣጠር እስከሚያቅታቸው በደም ፍላት እና በእልህ በየማኅበራዊ መገናኛው የሚወረውሯቸው በነውር የታጀሉ አጸያፊ ተንኳሽ ቃላቶች በስሙ የሚሳደቡለትን ሕዝብ፣ ድርጅት፣ ዕምነት፣ ሀገር ውስጥ ምን ያህል ሕዝብን ሊጎዳ እንደሚችልና፣ ችግሩ ከቀጠለ ሀገርን እንደሚያፈራርስ የጎጥ መሪዎቹ በደንብ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን የእነሱ ስግብግብ የሥልጣንና የንዋይ ፍላጎት ካልትሟላ ኢትዮጵያ ብትፈራርስ ደንታ የላቸውም፡፡ ሲያስመስሉ ግን ለወገን ፍቅር ነው የሚታገሉት፡፡ የዋህ ተከታዮቻቸው በቅንነትና በስሜት ከላይ የሚነገራቸውን እንጂ የመሪዎቹን ድርብ ሁለተኛውን አጀንዳ አያውቁትም፡፡
በመላው ዓለም ያሉ አክራሪ ብሔርተኞች እስከሚበጠሱ የሚያከሩት፣ በጨቅላ እድሜያቸው እቤት ውስጥ “እሳት ዳር” ወይም ምድጃ ዙርያ ከወላጆቻቸው ሲሰሙ የተተከለ የዘረኝነት ችግኝ ወይም የተሳሳተ ያለፈ ዘመን ትርክት…እንደ ተረት ተረት እየሰሙ በማደጋቸው እንጂ አብሮዋቸው ተወልዶ ያደገ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ማኅበረሰብም ይሁን ቡድን በሚደርስባቸው ጥቃትና በደል እራስን ለመከላከል እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ነው ጤነኛ የነበረው የትግሉ ዓላማም ሆነ የእንቅስቃሴው ይዘት፣ በአክራሪ ጎጠኛ ምሁሮች ተጠልፎ አቅጣጫውን የሚስተው፡፡
እንደዚህ አይነት ጥቃትና በደል በሕዝብ ላይ ሲደርስ የአክራሪዎቹን የጥላቻ ችግኝ ለመዝራትና ለመትከል እንደለሰለሰ መሬት ስለሚመቻቸው እንቅስቃሴውን ወዲያው ይቆጣጠሩታል፡፡
መጀመርያ የሚያስተምሯቸው የራስን ብሔር መውደድ ብቻ ሳይሆን፣ በስሜት የደለበ ወደ አክራሪ የዕምነት ወይም (የሴክት) አይነት አደረጃጀት በመከተል በመዝሙሩም፣ በዘፈኑም፣ በሽለላውም፣ በመንዙማውም…ወዘተ እነሱ ብቻ ለዛ ወገን ተቆርቋሪ የመሆን ስሜት እንዲያድርባቸው ይቀሰቅሷቸዋል፡፡ በአንጻሩ ከዛ ውጪ ያለውን ማኅበረሰብ እንዲጠሉ፣ እንዲፈሩ፣ እንዲጠየፉ፣ እንዲወጉና ከምድረገጽ እንዲደመሰሱ ጭምር አስተምረው አቋም የማስያዝ ችሎታ አላቸው፡፡ ዲሞክራሲ፣ ምርጫ፣ የግለሰብ ነፃነት የሚባለውን፣ ህብረ-ብሔራዊ አመለካከት፣ ሀገራዊ ራዕይ፣ ሀገራዊ ጥቅም …አለርጂኮቻቸው ናቸው፡፡ የግለሰብ መብት መከበር ለአጠቃላዩ ዲሞክራሲ መሠረትና ለቡድንም መብት መከበር ዋስትና መሆኑን አይቀበሉም፡፡
በጣም የሚያስገርመው ወይም የሚያስደነግጠው፣ በሌላው ማህበረሰብ ውስጥ ስለሚያዩት አክራሪነት እንጂ፣ የሚያወግዙትን ተመሳሳይ ነገር በግልባጩ እራሳቸው ሲፈጽሙት ትክክል እንደሆኑ ይሰማቸዋል፡፡ በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ አክራሪ ብሄርተኞች እንዳሉ መቀበል አይዋጥላቸውም፡፡ ወይም እነሱ ቆመንለታል የሚሉት ማህበረሰብ ከአክራሪነት የነፃ፣ ወይም እነሱ ሲያደርጉት ትክክል ሕጋዊ እንደሆነ አድርገው ሊያሳምኑ ይሞክራሉ፡፡
አክራሪ ብሔረተኞች የራሳቸውን ጠባብ አጀንዳ ለማሰፈጸም ከማንኛውም የሀገር ጠላቶች ጋር እስከመተባበር ድረስ እርቀው እንደሚሄዱ እየተካሄደ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ እያየን ነው፡፡ በሀገራችን ባሰለፍነው ፣ አንዳንድ አክራሪ ብሔርተኛ ቡድኖች ከሱዳንና ከግብጽ፣ ….ወዘተ ሲሞዳሞዱ የታዩትን ብዙ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በተረፈ ሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ዘር ተኮር ግድያና መፈናቀል ምክንያት የደረስንበት ቀውስ ጠላቶቻችን የሚፈልጉት መንገድ እየተሳካላቸው ይመስላል፡፡ ለስልጣንና ለጥቅም “ዓይናቸውን በጨው ያጠቡት”፣ በየወቅቱ ከሚፈጠረው ቀውስ ለማትረፍ እየተወራጩ ነው፡፡ ጥቂት የማይብሉ የዘርና የፖለቲካ ድርጅቶች ተከታዮቻቸው እምነታቸውን ለመሪዎቻችው ሰጥተው አንዳንዴ ሳያውቁት አብረው በማፍረሱም ሂደት ላይ ተሰማርተዋል፡፡
መንግሥት በየቦታው በጊዜ ሊያርማቸው፣ ሕዝባችንን ከአደጋ ሊከላከል፣ አቅመ ደካሞችን ሊረዳቸውና ሊደግፋቸው የሚገቡ ነገሮችን በፍጥነት ማድረግ አለበት ፡፡ በሰለጠነ መንገድ የምንወቅሰውና የምንገስጸው ብቻ ሳይሆን ፣ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ ወይም የሰውነት ባህሪ ነው፡፡ በየስፍራው ከሚገደለው ኢትዮጵያ ዜጋ፣ ከሚፈናቀለው ሕዝብ ጎን መቆምና መቃወም ብቻ ሳይሆን ለችግሩም ፈጥነን ለመድረስ መሞከር ከምንም ነገር በፊት የምንወስደው ወገናዊ ሆነ የዜግነት ግዴታችንም ነው፡፡
በተለይ በቅርብ ግዜ ውስጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ተቃውሞ በአደባባይ ለማሰማት በተከታታይ በተለይ የመጀመርያዎቹ ሁለት ቀናት በተለያየ ስፍራ እንደታየው አይነት ሥነ-ሥርዓትና፣ በጨዋነት አንድም ችግር ሳይደርስ እንደተጠናቀቀው ተቃውሞ ሰልፈኞቹና አስተባባሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሕግ አስከባሪ ሆነው የተመደቡት ወታደሮቹም ጭምር ተደናግጠው ሳይረበሹና አንዲት የጥይት ድምጽ ሳያሰሙ በሰላም መጠናቀቁ፣ የሰልፍ አዘጋጆቹንም ሆነ የጸጥታ አስተናጋጆቹም ጣልቃ ባለመግባታቸው፣ አስተዳደሩን ጨምሮ ሁሉንም በጋራ ተቻችለው ለተወጡት ሃላፊነት ምስጋና ልንቸራቸው ይገባል፡፡
ስንደግፍም ሆነ ስንቃወም ከግል ጥላቻ ጋር በመደባለቅ የትግሉንና የመስዋእትነቱን ዋጋ አናሳንሰው፡፡ በተለይ በአሁኑ ሀገራችን ባለችበት አስጊና አደገኛ የታሪክ መታጠፊያ ጎዳና ላይ ባለችበት ወቅት፣ ሰላማዊ ተቃውሞን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ትናንሽ የውስጥ ልዩነቶቻችንን የሀገራችን ጠላቶች ለራሳቸው የግል ዓላማ ጋር አዛምደው በውስጥ አርበኞቻቸው አማካይነት አስጠልፈው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ፣ በገንዘብም ሆነ በዓለም አቀፍ ሃያላን ድጋፍ የፈረጠሙ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ግብጽና ሱዳን ምን እየሞከሩ እንደሆነ የማያይ ካለ “ኮማ” ውስጥ ተቀርቅሯል፡፡
በውስጥ ትርምስ ተይዘን ግድባችን በሠላም እንዳይሞላ፣ እየቀረበ ያለው ምርጫ በሠላም እንዳይካሄድ፣ አይሆንላቸውም እንጂ ከቻሉ በኢትዮጵያውያን መሃከል( በተለይም በሁለቱ ታላላቅ ብሔሮች መሃከል) የእርስ በእርስ ጦርነት ቶሎ እንዲጀመር የመጀመርያው የሱዳንና የግብጽ እቅድ ሲሆን፣ ወደ ድሮ ስልጣኑ ለመመለስ የሚፈልገውም ትህነግም እየተንደፋደፈ ሊጀምር የሚፈልገውን የትጥቅ ትግል ጊዜ ገዝቶ ለመጠናከር፣ ጦርነቱን በየአቅጣጫው በመወጠርና፣ በማስፋት በየማህበረሰቡ ውስጥ እየገዛ ባዘጋጃቸው ቅጥረኛ አክራሪ ብሔርተኞች ጉዳይ አስፈጻሚነት ሀገራችንን እየተፈታተኗት ነውና ወገኔ ዓይንህን ብቻ ሳይሆን አዕምሮህንም ክፈት፡፡
ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆነው ፈራርሰን እንድንበታተን ለሚፈልጉት የሀገራችን ጠላቶች ልዩነቶቻችንን እንዲጠቀሙበት መንገድ መክፈት የለብንም፡፡ ከመንግስት አኳያ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ሲፈጸም ለመንግስት ጥያቄ ስናቀርብ በተለይ የሀገራችንን ጠላቶች ሊጠቀሙበት በማይችሉት በራሳችን መንገድ፣ መሠረታዊ የሀገራችንን ዘላቂ ጥቅም ምንግዜም ሳንዘነጋ ሊሆን ይገባል፡፡ በእልህ ተነሳስተን “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ…” ትግሉን ያዳከመና ሕዝባዊ እንቅስቃሴውን የጎተተ መንገድ እስካሁን አልሰራም ወደፊትም አይሰራም፡፡
በተለይ አንዳንድ የ1960ዎቹ መርኅ-አልባ ፖለቲከኞች፣ ሁሌ መንግሥትን መቃወም እንደ ተራማጅነት የማየት ስር የሰደደ የማይለወጥና የማይሻሻል ቋሚ አመለካከታቸው “እኔ ካልበላሁት ጭሬ አፈሰዋለሁ” አይነት የዶሮዋን አካሄድ ዛሬም ሲገፉ ይታያሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሁሉም ማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉ አክራሪ ብሔረተኞችና ያኮረፉ የስልጣን ሱሰኞች፣ የወጣቱን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ጠልፈው ወደየእራሳቸው አጀንዳ ሊቀይሩት እየተቅበዘበዙ እንዳሉ አንዘንጋ፡፡ እጅግ የማከብራቸው ስመጥሩው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ በአንድ ንግግራቸው ላይ ታሪካዊ ምክር ሰጥተውን ነበር፡፡ ከተጠቀምንበት ማለቴ ነው፡፡
እጠቅሰዋለሁ “ስለተጠማን መርዝ አንጠጣም!” እንዳሉት ሁሉ፣ በደል ሲደርስ መቃወምና ከወገናችን ጎን መቆም ትክክል ሆኖ፣ ስርዓትና ሕግን ግን መጣስ የለብንም፡፡ ሠላም በመሬቱ ላይ ለሚኖረው ሕዝብ የህልውና ጥያቄ ነው፡፡፡ መንግሥትም እየተወላገደም ቢሆን የጀመረውን መጨረስ መቻል አለበት፡፡ መንግሥት ስለተሳሳተ ሀገር መፍረስ የለበትም!፡፡ በስርዓትና በሕግ መንግስትን ካልቀየርን የሚከተለው ቀውስ ምን ሊሆን እንደሚችል በዙርያችንና በራሳችን የእድሜ ክልል የምናውቀውንና የምናየውን ሁሉን ከመዘርዘር ለአንባቢ ልተው፡፡
ለተበደለ ድምጻችንን ማሰማት፣ በዳዮች በሕግ እንዲዳኙ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለችግራቸው የሚረዳ ተጨባጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ግብረሰናይ ድርጅቶችም ሆነ መንግስታዊም ሆኑ ግላዊ ተቋማት ጋር መተባበር ያስፈልጋል፡፡
መንግሥትን ስንቃወም በምክንያት እንደመሆኑ፣ መንግስትንም የሚደግፉት የራሳቸው ምክንያት እንዳላቸው አንዘንጋ፡፡ አማራጭ አቅርቦ ውሳኔውን ለሕዝብ እንጂ፣ እራሳችን ከሳሽ፣ ምስክርና ዳኛ ለመሆን መሞከር ከምንኮንነው መንግሥት በላይ አጥፊዎች ያደርገናል፡፡ ከሴራና የአድማ ፖለቲካ ወጥተን ልዩነትን ተቀራርቦ በመወያየት ለመፍታት እንሞክር፡፡
እንዲሆንልን እየተመኘን የምንታገለው፣ አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት ያለው ማኅበረሰብ ለመገንባት ሳይሆን፣ የሁላችንንም የተለያየ የፖለቲካ፣ የዕምነት፣ ባህል.…ወዘተ ተከብሮልን በጋራና በነጻነት፣ ደንብና ሕግ አክብረን በጋራ የምንኖርባት ለሁላችንም እኩል የሆነች ሀገር እንድትኖረን ነው፡፡
ሁሉን ነገር የመንግሥት ስህተት ብቻ ነው ብሎ ጭፍንተኛ ተቃዋሚ መሆንም ሆነ፣ በአንጻሩ አስተዳደሩ አይሳሳቱም አትውቀሱ አትቃወሙ የሚሉት፣ ሁለቱም አውቀውም ሆነ ሳያውቁት ለሀገራችን ጠላቶች እያገለገሉ ነው፡፡ ሁለቱም ስለ መብትና ግዴታ ልዩነት ማወቃቸው ያጠራጥራል፡፡ ሁለቱም ስለ ዲሞክራሲያ ጽንሰ ሃሳብ ገብቷቸዋል ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡
ለመቃወም የግድ መዋሸትና ማጋነን ሳያስፈልገን፣ በተጨባጭ ከሚደርሰውና ከሚታየው ጥፋት ተነስተን መንግስትና የፖለቲካ ድርጅቶችን መውቀስ ይሻላል፡፡ አሊያ ትግሉንና እየተካሄደ ያለውን መስዋእትነት ያሳንሰዋል፡፡ የሚታዘብና የሚያመዛዝን ሕዝብ እንዳለ አንዘንጋ፡፡
“መንግስትን ይደግፋሉ ተብለን እንዳንታማ፣ በዘሬ እፈረጃለሁ፣ ቡና አጣጭ አጣለሁ፣ ወይም ከማኅበራዊ ሕይወት ላለመገለል ሲባል እውነትን መሸሽ ከራስ የኅሊና ወቀሳ ስለማያስመልጥ፣ ቢያንስ እውነትን ተናግሮ ከሕዝብ ጥቅም ጎን በመቆም፣ በሠማንያ ሰባቱ ማኅበረ-ሰብ አክራሪ ብሔረተኞች ነቀፋ መጠመዱ ይሻላል፡፡
መንግሥትም ቢሆን ለዚህ ውድቀት ያደረሱንን የትህነግን የከፋፍለህ ግዛ ሕጎች በሕገመንግስቱ እንዲሻሻል ከሕዝብ በየጊዜው የሚቀርበውን አቤቱታ ቢያንስ ለፓርላማ አባላት ቀርቦ የሁሉም አካባቢ ወኪሉች ሃሳብ እንዳይሰጡበት ለውይይት እንኳን ለምን በሩን ዘጋው?፡፡ በዓለማችን የእምነት መጻህፍት እንኳን ከጊዜው ጋር ሳይሄዱ ሲቀሩ አንዳንድ ሕጎችን የዕምነት አባቶች ተወያይተው ያሻሻላሉ፡፡ ያውም ሕገመንግሥቱን የፈጠሩት ወያኔዎች የማያከብሩት ሕግ፡፡
ሠላምን ለማስፈን፣ በሕዝቦች መሃከል የሚነሳን ጦርነት ለማስቀረትና፣ መኅበረሰቡን ለማቀራረብ ከሆነ የሚቀየረው ወይም የሚሻሻለው፣ በዚህ የሚያኮርፉ ክፍሎች ቢኖሩ፣ ወያኔ የጥቅም ተካፋይ ሸሪክ አድርጎ በየመህበረሰቡ አናት ላይ በአንባሳደርነት ያስቀመጣቸው “የጎሳ አምበሎች” ዛሬ የወያኔ ሸሪኮች እንጂ፣ ተራው ዜጋችን ከለውጡ ተጠቅሞ ያተርፋል እንጂ አይጎዳም፡፡
ይህንን ጥያቄ አሽዋፊ አክራሪ ብሔርተኞች፣ እውነቱን እያወቁ በተሳሳተ መንገድ አጣመው በማቅረብ፣ አሃዳዊ መንግሥት እንደተጠየቀ፣ የተለያዩ ማህበረሰቦች የራሳቸውን ቋንቋና ባህል እንዳይጠቀሙ የቀረበ ጥያቄ ተደርጎ እንዲታይ ሕዝብን የሚያሳስቱበትን መንገድ ትክክል እንዳልሆነ በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
ለማጠቃለል፣> የሚቀጥለው ምርጫ ርትአዊ፣ፍትሃዊ፣ሰላማዊ እና አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን መንግስት በብዙ መልኩ መስራት አለበት የሚለው መልእክቴ ነው፡፡
ሞኞች ሆነን ጠላትን ተባብረን መመከት በሚገባን ሰአት እርስ በርሳችን እየተጋጨን ለየብቻና በየተራ በጠላት እንዳንጠቃ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አንዴ ከፋፍለውና አዳክመው ከበታተኑን ቦኋላ እንደገና መነሳት አቸጋሪ ነው፡፡ ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ………..የሚለው የአባቶቻችን ብሂል እንዳይደርስብን እንጠነቀቅ፡፤
በተረፈ የፋሲካ በዓል ቢያልፍም፣ ለዳግማዊ ትንሳኤ ጤናችን እንዳይታወክ፣ ከአትክልቱ በዛ፣ ከስጋው ቀነስ፣ ለምግቡም ሆነ ለፖለቲካው ተፈጥሮ የቸረውን “ንጥረ-ነገሩን” ሳናደበዝዝ እንደ ስጋውና ፖለቲካው፣ የኢትዮጵያን ወግና ባህል ሳናበላሽ፣ የሠላም የመቻቻልና የአብሮነት መንፈስ የሚዳብርበት ጊዜም እንዲሆንልን ለሁላችንም እመኛለሁ፡፡
እንደ መደምደሚያ
የዛሬውን ጽሁፌን የምቋጨው በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት እውቅ የጦር ሰው በነበሩት ሌ/ጀነራል ዐብይ አበበ ምክረ ሀሳብ ይሆናል፡፡
‹‹ ጥንታዊቷንም፣የዛሬይቷን ኢትዮጵያችንን የወደፊትም እንድትሆን ካስፈለገ በቅን መንፈስ በፍቅርና በመተባበር ደግፈን እናዘልቃለን ብለን ካልተነሳንበቀር በአሉባልታና በመነቃቀፍ በሐሰት በመነዳና በወሬ በመሰልጠን በንጹሑና በተባረከውም ሕዝቧ ተንኮል በመዝራት እንዲሁም በሰው ሀገር ጉዳይ ውስጥ እየገቡ አሳቢ በመምሰል የሕዝቧን መነጣጠል ለሚገፋፉ ባእዶች ደጋፊና ተባባሪ ሆኖ በመገኘት ጥቅም ይገኛል ብሎ የሚያስብ ቢኖር የተሳሳተ መንገድ መሄዱን ይረዳው፡፡ ከእንደዚህ ያሉም ሰባኪያን መራቅ የማንኛውም ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ሰው ጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡
‹‹ አውቀን እንታረም ገጽ 16-17 ሌ/ጀነራል ዐብይ አበበ››
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት፡፡
ለእኛም ማመዛዘኛ ልቦና ይስጠን፡፡