>
5:13 pm - Monday April 18, 0214

የእውነት ጠበቃው ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ በሽብር ክስ ተከሰሱ...!!! (ገበየሁ ደመላሽ)

የእውነት ጠበቃው  ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ በሽብር ክስ ተከሰሱ…!!!

ለግንቦት 13 ተቀጥረዋል
ገበየሁ ደመላሽ

አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ፀሐፊ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ ‘ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በሃይል በመናድ’ ብሎም ከመንግሥት ግልበጣ ጋር በተያያዙ መንግሥታዊ የሀሰት ውንጀላዎች ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸዋል። ጋሽ ታዲዮስ ባለፈው ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፤ የድል ሀውልት ስር ተገኝተው የአርበኞችን የድል በዓልን ከአከበሩ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። በታገቱበት ጊዜ የፍርድ ቤት መጥሪያ እንዳልደረሳቸውና የእስሩ ምክንያትም እንዳልተነገራቸው ጠበቃቸው አቶ እንደገና ግዛው ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።
የህሊና እስረኛው በአሁኑ ጊዜ ከባለቤታቸውና ጠበቃቸው ውጭ ሌላ ሰው እንዳይጠይቃቸው ተከልክለው በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ  ክፍል ውስጥ ይገኛሉ።
ባለፈው አርብ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል። በዚህም “ከውጭ አካላት ጋር በአንድ ላይ በመሆንና በህቡዕ በመደራጀት ‘የአማራ ደም የእኔም ደም ነው’ በሚል ተንቀሳቅሰዋል።” የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም “የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት እየተደራጃችሁ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል ከፍተኛ እቅድ አውጥታችሁ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው።” በሚል ተጠርጥረዋል።
ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ ለመጭው ግንቦት 13 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
ታዲዮስ ታንቱ በነፃው ፕሬስ ውስጥ በሀቀኛ  ጋዜጠኝነታቸው ይታወቃሉ። በተለይም ‘ወግድ ይሁዳ’ በሚል ርዕስ ያቀርቡት በነበረው ተከታታይ የፖለቲካ ትንታኔያቸው ይታወቃሉ። “ደመላሽ፣ የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ እና ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኛ” የተሰኙ መፅሐፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን ሁለት ተጨማሪ አዲስ መፅሐፍትንም በተመሳሳይ ጊዜ ለማሳተም በዝግጅት ላይ እያሉ ነው የታሰሩት።
Filed in: Amharic