>

እኔ የማዝነው...?!? (ጌታቸው ሽፈራው)

እኔ የማዝነው…?!?

ጌታቸው ሽፈራው

*…. ለሀገር መፍረስ የመጀመርያዎቹ ተጠያቂዎች ሀገር ሊያድኑ የሚችሉ፣ ሴራ የሚያከሽፉ፣ ስጋት የሚቀንሱ፣ ሰላም የሚያሰፍኑ፣ ወንጀል የሚከላከሉ ተቋማት ላይ ተደላድለው ተቀምጠው፣ የሚታይ ስጋት እያለ የሌለ፣ የሀሰት ስጋት ላይ ተጎልተው ሲውሉ ነው።
ሀገርን  የሚያፈርሰው ጫካ ያለ ወንበዴ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ለሀገር መፍረስ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ተቋማት ላይ ተደላድሎ ኃላፊነቱን መወጣት ሲገባው ሌላ፣ የሀገርን ስጋት መቅረፍ ሲኖርበት ሌላ የተጓደኛ የሌለ ያልተጨበጠ ጉዳይ ላይ ጊዜውን የሚጨርስ ኃይል ነው።
እስኪ አሁን በምን ስሌት ታዲዮስ ታንቱ በፖለቲካ ይታሰራሉ? ያውም የተደራጀና የዕቡዕ ፖለቲካ እየተጠቀሰ። አቶ ታዲዮስ ታንቱ ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለፅ ችግር የለባቸውም።  ነገር ግን ከማንም ጋር ሆነው ፖለቲካ ሊሰሩ የሚችሉ ሰው አይደሉም። ይህን አሳፋሪ ክስ ይዛችሁ ስትመጡ  የሚያውቃቸው ሰው ሁሉ ያፍርባችኋል። “አቶ ታዲዮስ ተቸግረዋል” ተብሎኮ ብዙ ጊዜ ፌስቡክ ላይ የባንክ አካውንታቸው ተለጥፏል። ታምመው አካውንታቸው ፌስቡክ ላይ ተለጥፏል። ገንዘብ ተላከላቸው ብሎ አቶ ታዲዮስን በሕቡዕ ምናምን ሰበብ ማሰር እጅግ አሳፋሪ ነው።
እኔ የማዝነው ስለ ግለሰቡ ታዲዮስ ታንቱ አይደለም። የሚያሳዝነኝ የሀገር እጣ ፈንታ ነው። ሙሉ ከተማ የሚያወድም ሴራ ሲሰራ ዝም ብሎ የሚያይ በርካታ ተቋም ነው ይህን የሀሰት ክስ ሰበብ እያደረገ አንድ ሽማግሌ እያሰረ ያለው። አቶ ታዲዮስ ላይ ሀሰት ደርድሮ እስር ቤት በሚያቆይበት ሰዓት ስንት የሀገር ጠንቅ የሆነ ሴራ ማክሸፍ ይችል ነበር።
የሚያሳስበኝ የአቶ ታዲዮስ ጉዳይ አይደለም። አቶ ታዲዮስ ሽማግሌ ናቸው። አብዛኛው ሕይወታቸውን ኑረውታል። የማዝነው ለቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያ ነው። በአዛውንቶች ላይ ሀሰት ሲደረድር የሚውል መንግስት ህፃናትን ከገዳዮች ማዳን የሚችልበትን እንቁ ጊዜ  ማንም ጋር ፖለቲካ ለመስራት ፍላጎት የሌላቸው ሽማግሌ ላይ ሰበብ ሲቆፍር እየዋለ ጊዜ  እያጠፋ ነው። ነፍሰ ጥሩዎችን የሚታደግበትን፣ የወጣቶች ህይወትን የሚታደግበትን፣ የቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያን ስጋት የሚያቃልልበትን ጊዜ ባለፈው ትውልድ አንድ ምስኪን አዛውንት ላይ ድሪቶ ክስ አምጥቶ ጊዜውን ያጠፋል። አቶ ታዲዮስን በሀሰት እስር ቤት ለማቆየት ላይ ታች ሲሮጡ የቀጣዩ ትውልድ፣ የህፃናት፣ የነፍሰ ጥሩዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ አሸባሪን ሴራ ማክሸፍ ይችሉ ነበር። ግን የማይሆነው፣ የማይጠቅመው ላይ ተሰማሩ። የገጠመንን ችግር ትተው የልብ ወለድ ክስ እያመጡ ጊዜያቸውን ያባክናሉ።
እኔ የማዝነው አቶ ታዲዮስ በዚህ እድሜያቸው በመታሰራቸው ብቻ አይደለም። እጅግ የሚያሳዝነው የሀሰት ክስ፣ ሰበብ፣ ከምንም የተጋገረ ክስ እንደ ስርዓት መለመዱ ነው። የእውነት የሚያጠቁን ጠላቶች በየአይነቱ ተደርድረው ተቋማቱን የያዙት ግን የሀሰት ወንጀል፣ የፈጠራ ክስ ሲመሰርቱ ይውላሉ። ኢትዮጵያ የእውነት፣ ያፈጠጠ ስጋት መጥቶባት በሀሰት የሚጠሉትን በመክሰስ አትተርፍም። ኢትዮጵያን የሚያፈርሳት፣ እያፈረሳት ያለው እውነተኛውን ስጋት መግታት ሲችል፣ እውነተኛውን ስጋት በሚገታበት  የማይተካ ጊዜ፣ የሀሰት ክስ ሲቀምር የሚውለው ባለ ጊዜ ነው።
ለሀገር መፍረስ የመጀመርያዎቹ ተጠያቂዎች ሀገር ሊያድኑ የሚችሉ፣ ሴራ የሚያከሽፉ፣ ስጋት የሚቀንሱ፣ ሰላም የሚያሰፍኑ፣ ወንጀል የሚከላከሉ ተቋማት ላይ ተደላድለው ተቀምጠው፣ የሚታይ ስጋት እያለ የሌለ፣ የሀሰት ስጋት ላይ ተጎልተው ሲውሉ ነው።
እስኪ አንድ፣ እንዲያው አንድ ሰው ከአቶ ታዲዮስ ጋር ቁጭ ብሎ የሴራ ፖለቲካ አወራሁ የሚል ሰው ፈልጋችሁ አግኙ። እስኪ የሚያውቋቸው ፈልጋችሁ ጠይቁ። በምን ተአምር አቶ ታዲዮስ የሴራ፣ ያውም የሕቡዕ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ሊሰሩ ይችላሉ? በምን ተአምር አቶ ታዲዮስ በመሰል ፖለቲካ ተስማምተው ይሰራሉ?
Filed in: Amharic