>
5:33 pm - Wednesday December 6, 1893

የአዞ ፖለቲካ (ጌጥዬ ያለው) 

የአዞ ፖለቲካ

   ጌጥዬ ያለው 

የ60ዎቹ የተማሪ ፖለቲከኞች ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ‹አዞዎቹ› (Crocodiles) የሚባል አደረጃጀት ነበራቸው፡፡ በወቅቱ ይደረጉ የነበሩ የተማሪዎችን የተቃውሞ ሰልፎች ሁሉ ይመሩ የነበሩት አዞዎቹ ናቸው፡፡ መሥራቾቹ ዛሬም በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለያዩ አሰላለፎች ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዳዶቹ  ኦሮሞነት ጉርሻ ሰጥቷቸው ቤተ መንግሥት ገብተዋል። ከአዞዎቹ መካከል እነ ብርሃኑ ነጋ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በግልፅ ባይገቡም እንደ ውሽማ አጥር ስር መሹለክሎካቸው አልቀረም።  እነ ሌንጮ ባቲማ በግልፅ ቆራሽ ቀዳሽ ሆነዋል።
 ኢትዮጵያን እንደ አዞ እየዋጠ ያለው የማንነት ፖለቲካ የተጠነሰሰውም ከዚህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአዞዎቹ  መስራቾች ‹‹በኮሚቴ ተዘጋጅቶ በዋለልኝ መኮንን መድረክ ላይ ተነበበ፤ በስሙ በ‹ስትራግል› ጋዜጣ ታተመ›› ያሉትን  ባለ አምስት ገፅ በእንግሊዝኛ የተፃፈ ከፋፋይ ፅሁፍ ላይ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ   በመወያየት ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ እንቅስቃሴያቸውን በድጋሜ አድሰዋል፡፡ መርሃ ግብሩ መንግሥታዊ ድጋፍ ተሰጥቶት በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን ዲማ ነግዎ፣ ሌንጮ ለታ፣ ሚሚ ስብሃቱ፣ ሰመሀል መለስ ዜናዊ፣ የመኢሶን አባሉ ታምራት ከበደ የተገኙበት ነበር፡፡ የማርታ ኩዌ ኩምሳ በዜማና ዝማሬ የታጀበ የመድረክ ላይ ቅስቀሳ ደግሞ አዞው ዛሬም እንደገና አፉን ስለመክፈቱ ያረጋግጣል፡፡ ይህ የአዞው ፖለቲካ አስተሳሰብ በሕወሓት ውስጥ ነግሶ ኢትዮጵያን ሲነክስ ኖሯል፡፡ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ደግሞ አዞው ጥርሱን ቀይሮ መጣ፡፡ የመለስ ዜናዊም ሆነ የአብይ አሕመድ አዞዎች የሚውጡት አንዲት ኢትዮጵያን ነው፡፡ ቅድሚያ የሚሠጡት ደግሞ ለኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሆኑ ሕብረ ብሔራዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን ሆኗል፡፡ በተለይም ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አዋሳ እና አዲስ አበባ ኢላማ ናቸው፡፡ የአብይ አዞ አዋሳን እየዋጣት ነው፡፡ ሐረርን 50/50/0 በሚል ቅርምት ማለትም ግማሹን የፖለቲካ ሥልጣን ለኦሮሞ፣ ገሚሱን ለሶማሌ በመስጠትና ሌሎች ነዋሪዎችን ውክልና በመንፈግ ቀጥሏል፡፡ በድሬዳዋም የ40/40/20 የሥልጣን ቅርምት እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዳውም አሁንማ በኦሮሙማ ጠቅላይነቶ 100/0 ሆኗል ነው ነገሩ፤ ኢሕአዴግ ስሙን ቀይሮ ቢመጣም የሥልጣን መዋቅሩ ግን አልተቀየረም፡፡ የአዲስ አበባው አዞ ጉሮሮ ላይ ነን፡፡
አዲስ አበባ በተለያዩ መንግሥታት
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ስሌት እስከ 1960 ድረስ ኢትዮጵያ 12 ጠቅላይ ግዛቶች ነበሯት፡፡ በ1960 ባሌ ከሐረር ጠቅላይ ግዛት ተገንጥሎ ራሱን የቻለ ጠቅላይ ግዛት ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1962 የኤርትራ ፌዴሬሽን ፈረሰ፡፡ ኤርትራም ሌላ ጠቅላይ ግዛት ሆነች፡፡ እስከ 1974  ድርስ 14 ጠቅላይ ግዛቶች ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት አዲስ አበባ የሸዋ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ ነበረች፡፡ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ሥልጣኑን እንደጨበጠ ደግሞ አዲስ አበባን ራሷን የቻለች ራስ ገዝ አድጓታል፡፡ ከስድስት ዓመታት በኋላ ጊዜያዊው ወታደራዊ የደርግ መንግሥት ወደ ሶሻሊስት ሪፐብሊክነት ራሱን ቀየረ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያን በ25 ክፍለ ሀገሮችና በ5 ራስ ገዝ አስተዳድሮች አዋቀረ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባ ከ25ቱ ክፍለ ሀገሮች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን እንደወጣ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ራሷን የቻለች ‹ክልል› ሆነች፤ ‹ክልል› 14፡፡ ቆይቶ ቻርተር ከተማ አደረጋት፡፡ እንደ ዘጠኙ ‹ክልሎች› ሁሉ የ‹ክልል› 14ነትን አወቃቀር ይዛ ቀጥላ ቢሆን ኖሮ የቆዳ ስፋቷ በድሮው ልክ ይሆን ነበር፡፡ ይህም እንደፈለገች ወደ ጎን የምትሰፋበትን እድል ይሰጣታል፡፡
የሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አዞ አዲስ አበባን በድጋሜ የነከሳት በድኀረ 97 ምርጫ ነው፡፡ በከተማዋ እጅግ በተጋነነ ውጤት በምርጫ የተሸነፈው ኢሕአዴግ የኦሮሚያ ‹ክልል›ን ዋና ከተማ ከናዝሬት ወደ አዲስ አበባ ሲያመጣ አዲስ አበባ ላይ ፍም እሳት በገለባ አዳፍኖ ነው ያለፈው፡፡ ዛሬ ከተማዋ ውስጥ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች አንዱ ምንጭ ይህ ነው፡፡ በኦሮሞ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች እጅ ሥር ወድቃለች፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቷ ሥልጣኑንን የተነጠቀባት ኦሕዴድ ከቀበሌ እስከ ከንቲባ የተቆጣጠራት ከተማ ሆናለች፡፡ በምክትል ከንቲባነት ማዕረግ የዋና ከንቲባነት ሥራ የሚሠራባትም ሹመቱ ሕጋዊነትን የጎደለው ስለመሆኑ አያሻማም፡፡ ከሰሞኑ ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአንድ የመዝናኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ቀርባ ነበር። የዝግጅቱ ባለቤት ሰይፉ ፋንታሁን “እርሶ ምክትል ከንቲባ ነዎት። ዋናው ማነው?” ሲል ጠየቃት። የኦሕዴዷ ሴት ምላሿ “ሕዝቡ ነው” የሚል ነበር። የአዲስ አበባን ሕዝብ ይሄን ያህል የፖለቲካ ድሀ አድርጋ ቆጥራዋለች።
አዲስ አበባ  ስትመሰረት የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከ20 ሚሊዮን ያነሰ እንደነበር ይገመታል፡፡ እንደ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ማዕከል ትንቢያ ዛሬ ይህ የሕዝብ ቁጥር ከ98 ሚሊዮን በላይ ሲሆን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደግሞ ወደ ሰባት ሚሊዮን ይጠጋሉ፡፡ መንግሥት ከሦስት ዓመታት በፊት ካወጣው ከዚህ ትንበያ በተለየ  ከፍ የሚያደርጉት አካላት አሉ፡፡ ከአመታት በፊት የተደረገው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ እንደሚያመለክተው፣ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል 57 ከመቶ ያህሉ የአማራው ሕዝብ ተወላጆች ናቸው፡፡ 19 ከመቶዎቹ ደግሞ የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ሲሆኑ ቀሪውን ቁጥር ሌሎች ነዋሪዎች ይይዛሉ፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍሉ ይህንን የነዋሪዎች ቁጥር ያገናዘበ አይደለም፡፡ ከከንቲባ እስከ ወረዳ ድረስ በአመዛኙ በኦሮሞ ተወላጆች ተይዟል፡፡ ብዙሃኑ በኅዳጣን እየተመራ ነው፡፡ በተገቢው የፖለቲካ ውክልና መሰረት ቢሆን ኖሮ ግን ቢያንስ ከንቲባው ከአማራ ተወላጆች፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ደግሞ ከኦሮሚያ መመረጥ ነበረባቸው፡፡
ከተማዋ በሕጎች፣ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መመራቷ ቀርቶ በግለሰቦች ፖለቲካዊ ውሳኔ ብቻ እየተመራች ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለአብነትም  ለከተማ አስተዳድሩ የነበረው የአዲስ አበባ ፖሊስ ተጠሪነት ከምርጫ 97 በኋላ መለስ ዜናዊ አንስቶ ለፌዴራል ፖሊስ ተጠሪ አደረገው፡፡ ታከለ ኡማ እንደመጣ ደግሞ ፖሊስ ኮሚሽኑ የሥራ ሪፖርት ያቀርብ የነበረው በሰላምና ደህንነት ቢሮው በኩል ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ማለት አዋጅ ማሻሻሉም ቀርቶ አንድ መግለጫ እንኳን ሳይነገር ተጠሪነቱ ከፌዴራል ወደ ከተማ አስተዳድሩ ተመልሷል ማለት ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ወደ አሮሚያ ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ አዳነች አበቤ ከአቶ ታክለ ተቀብላ የምታስፈፅመው ታላቁ ጉዳይ የአዲስ አበባ ተቋማትን ተጠሪነት ወደ ኦሮሚያ ማዘዋወርና ከተማዋን የኦሮሚያ አካል ማድረግ ነው፡፡ ከተቋማት ጋር ትስስር እየተፈጠረ እንደሆነም ተሰምቷል፡፡ ይህ በአዋጅ ተደንግጎ በግልፅ ባይፈፀምም ውስጥ ለውስጥ የተቋማቱ አሠራር ግን በዚሁ አይነት የሚቀጥል ነው፡፡ ውስጥ ለውስጥ በሚተላለፍ መመሪያ መሰረትም የትምህርት ዘርፉን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያን ለማጥፋትም ሆነ አፍርሶ እንደገና የአባ ገዳ ዱላ አስጨብጦ ለመሥራት የትምህርት ዘርፉን መቆጣጠር አዋጭ መንገድ ሆኗቸዋል፡፡ በመሆኑም በከተማ አስተዳድሩ ባሉ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሠሩ ርዕሳነ መምህራን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች እንዲሆኑ ታዝዟል፡፡
 የመምሕራን እሮሮ 
‹‹ትምህርት በኦሮምኛ ተቀናጅቶ በሚሰጥበት ካሉት ርዕሳነ መምህራን አንዱ የኦሮምኛ ቋንቋ መስማት፣ መናገር፣ ማንበብና መፃፍ የሚችልና መቻሉን በፈተና የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡›› ይላል የርዕሳነ መምህራን ድልድል መስፈርቱ፡፡ በዚህ መሰረት በእያንዳዱ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህሩ ወይም ምክትሉ ኦሮምኛ ተናጋሪ መሆን አለባቸው ማለት ነው፡፡ በነፃ ዝውውር ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ አስተማሪዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡  ዛሬ በዚህ ከተጀመረ በጥቂት አመታት ውስጥ ከተማዋ ውስጥ መምህራን ሁሉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ይሆናሉ፡፡ ከኦሮሞ ውጭ ያሉ መምህራን ተለጥመው ከሥራ ውጭ ይደረጋሉ፡፡ በዚህም አያበቃም፡፡ ቀጣዩ መዳረሻ ተማሪዎችን በሙሉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ማድረግ ነው፡፡ ‹ከኦሮሞ ውጭ አናስተምርም› መባል ይጀመራል፡፡ ሌላው የትምህርት ፍላጎቱን ለማሳካት ሲል ከተማውን እየለቀቀ ይወጣል፡፡ ይህ እንዲህ ሲፃፍ ተረት ተረት ሊመስል ይችላል፡፡ ሆኖም የሚፈፀቅ ሐቅ ለመሆኑ የገዳ ሥርዓት ታሪክና የሽመልስ አብዲሳ ንግግር ምስክሮች ናቸው፡፡ ጉዳዩ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ብቻ ተፈፅሞ የሚቀርም አይደለም፡፡ የግል ትምህርት ቤቶችም ነፋሱን ተከትለው እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ ገደማ በሜጫ ቱለማ ማሕበር ሥር ይሰጥ በነበረው የፊደል ሰራዊት የትምህርት ፕሮግራም ያስተምሩ ከነበሩ የተማሪ አስተማሪዎች መካከል አማራዎችም ነበሩበት፡፡ ለምሳሌ ሐምዛ ይመር ይጠቀሳሉ፡፡ በማሕበሩ ፕሬዚደንት ታደሰ ብሩ መሪነት ያስተምሩ ከነበሩ ስድስት ተማሪዎች መካከል ሐምዛ አንዱ ሲሆኑ የሜጫ ቱለማ ማሕበር አዳራሽ ሓላፊም ነበሩ፡፡ የኦሕዴድ የቁቤ ትውልድ ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ያስተማሩትን በማጥቃት ተጠምዷል፡፡
በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችም አዲስ የርዕሰ መምህራን ምደባ እየተደረገ ነው፡፡ ነባሮቹ ከደረጃቸው ዝቅ ብለው በመምህርነትና በአስተባባሪነት እንዲቀጥሉ ተነግሯቸዋል፡፡ ከአዳዲስ መጭዎች ጋር ፈተና ተፈትነው ሊመለሱ እንደሚችሉም ተነግሯቸዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን እየለቀቁ እንዲወጡ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሆነም ለዚህ ፅሁፍ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ቁጥር 188 ሲሆን 160ዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከፊሎቹ ለቀው ወጥተዋል፡፡ ገሚሶቹ በአስተባባሪነት ወርሃዊ ደሞዛቸውና ጥቅማጥቅሞቻቸው ተቀንሶ እየሠሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በተመሳሳይ ከነበሩበት የሙያ ርከን ዝቅ ብለው በመምህርነት እየሠሩ ነው፡፡ ይህ የሞራል ጉዳት እንዳስከተለባቸውም ይናገራሉ፡፡ ርዕሳነ መምህራኑን መንግሥትን ለመክሰስ ወደ ሕግ ተቋም ቢያቀኑም ‹አይቻልም› ተብለው ተመልሰዋል፡፡
ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ቅሬታቸውን አቅርበው ከተቀረፀ በኋላ እንደማይሰራጭ የተነገራቸው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ እዚህ ላይ የጋዜጠኞችን እሮሮም ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ በቅርቡ ስሙን የቀየረው የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ጋዜጠኞች ልክ እንደ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ሁሉ ለአመታት ከሰሩ በኋላ እንደገና ተፈትነው ጋዜጠኛ እንደሚሆኑ ታዝዘዋል፡፡ ተፈትነዋልም፡፡ የፈተናው አላማም ተቋሙን በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ለማጥለቅለቅ እንደሆነም ግልፅ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙሃኑም ሆነ የትምህርት ዘርፎች ሌላውም ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ አዋጭ መንገዶች ስለሆኑ ቀዳሚ ሆኑ እንጂ በየዘርፉ ይህ አይነቱ የማፈናቀልና በአዳዲሶች የመተካት እንቅስቃሴው መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ከዛሬው በላይ የነገው ሰቆቃ ይከፋል፡፡ በዚህ ላይ የመምህራን ማህበሩም ሆነ በየአዳራሹ ስለ ጋዜጠኝነት የሚደሰኩሩ የጋዜጠኝነት ማህበራት ትንፍሽ አላሉም፡፡ ኢመሪተስ ፕሮፌሰር እየተባሉ በሙያው ስም የሚሸለሙ መምህራንም ጉዳዩን ከመጤፍ አልቆጠሩም፡፡
 የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት 
ከወራት በፊት ደኢሕዴን 20 ምሁራንን በማሰማራት እና 17 ሺህ ዜጎችን በማሳተፍ አጠናሁት ባለው መሰረት ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ ሲዳማ ነኝ፣ ሀድያ ነኝ፣ ጉዳራጌ ነኝ፣ ወላይታ ነኝ. . .  ከሚለው ይልቅ ደቡብ ነኝ የሚለው ማንነት ተስፋፍቷል፡፡  ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚንስትሩ የዴሞክራሲያዊነት መገለጫ ነው ባሉት የ‹ክልል›ነት ጥያቄ ይህ ማንነት እየጠፋ ነው፡፡ የደቡቤነት ማንነትን አጥፍቶ በመሰነጣጠቁ ኦሕዴድ/ብልፅግና ሰፊውን ድርሻ ይወሰወዳል፡፡ የአዲስ አበባ ብሔርተኝነትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነዋሪዎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ቢመጡም በከተማዋ ሲኖሩ ግን አዲስ አበቤነታቸውን አጉልተው መጠበቅ አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ይህ ቢጠፋ ደስታቸው ነው፡፡ ጎጃም በረንዳ፣ ወሎ ሰፈር፣ በቅሎ ቤት፣ ጠመንጃ ያዥ፣ ጦር ሃይሎች፣ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ መገናኛ፣ ጃን ሜዳ . . . የተለያየ ማንነትና ስነ ልቦና ቢኖራቸው ደስታቸው ነው፡፡ ሆኖም የአዲስ አበቤነት የአንድነት ስሜትን በማጎልበት ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ሁሉ መቅረፍ ይቻላል፡፡ ከክፍለ ሀገር እየመጡ ከተማዋን መምራትም ይቀራል፡፡
Filed in: Amharic