>

   "ሃገሬን እንጅ መንግስትን አላገለግልም " ሊጋባው በየነ 

“ሃገሬን እንጅ መንግስትን አላገለግልም ” ሊጋባው በየነ 

 

ጸጋው ማሞ

   የአትንኩኝ ባይነት ፣ የሃገር ፍቅር ጠኔ ፣  የኢትዮጵያዊነት ኩራት ፣ የሞራል ልዕልና የአባቶች ደማዊ ውርስ ማያሳ ለአመነበት እውነት ሥልጣንን እምቢኝ ብሎ ግዞትን የመረጠ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ  ሰው  ሊጋባው በየነ  ነው ።
         “ጠጅ ጠጣ ሲሉት ውሃ እየለመነ
            የጎንደር ባላባት ሊጋባው በየነ
              እንደ ኮራ ሄደ እንደተጀነነ “
   ተብሎ በወቅቱ በሕዝብ  “ኩራቱ”  በቅኔ  የተነገረለት ። ጠጅ የተባለው ምቾትንና ሥልጣኑን ሲሆን ወሀ ያሉት ቀዝቃዛውን እስር ቤት ነበር ።
    ———–
    በየነ ወንድም አገኘሁ ከቤተ መንግስት አጋፋሪነት ተነስተው የሊጋባነትና የደጃዝማችነት ማዕረግ ያገኙ  ሲሆን በባሌና በወላይታ የአስተዳዳሪነት ሹመት ተሰጥቷቸው አገልግለዋል ። ይሁንና ከአፄ ኃይለስላሴ ጋር በነበራቸው ተደጋጋሚ አለመግባባት ግርፋትና ለተደጋጋሚ እስር ተዳርገዋል ። ሊጋባው በየነ ለየት የሚያደርጋቸው በፍርድ አደባባይ ላይ ሳይቀር  የሚያሳዩት ኩራትና ጅንንነት ነው ። ከፍርድ በፊትም ሆነ ከተፈረደባቸው በኋላ በአፄ ኃይለሥላሴ ላይ የሚያሳዩት ንቀትና ትችት ጅንን አስብሏቸዋል ።
     ——-
  ከመጀመሪያው ግዞት መፈታት በኋላ ለኃብተ ጊዎርጊስ ዲነግዴ አፄ ኃይለ ሥላሴን ከስልጣን ለማውረድ በጻፉት ደብዳቤ ተከሰው በፍርድ አደባባይ  ታላላቅ ባለሥልጣት  በተገኙበት ስለ ወንጀላቸው ሲጠየቁ  አቋማቸውን ስላንፀባረቁ “ሽብርተኛ ” ተብለው በአባ ሻውል  ሀረር እንዲታሰሩ በተወሰነባቸው መሰረት ታሰሩ ።  ኋላም በምሕረት ከተለቀቁ በኋላ  በጎንደር የሀገረ ገዥነት ሹመት ቢሰጠውም ” እኔ ሃገሬን እንጅ ያሰረኝን መንግስት አላገለግልም ” በማለት  በኩራትና በልበ ሙሉነት አፄ ሃይለስላሴን ስለዘለፉ ዳግመኛ ወደ ኮንታ ለግዞት ተልከዋል ።
      ——–
      ጣሊያን የመረብን ወንዝ ተሻግሮ አገራችንን በወረረ ጊዜ  ሊጋባው በየነ ለአፄ ኃይለሥላሴ  “ሀገሬን ከጠላት ልከላከል ቁርጥ አድርጌአለሁና እዘምት ዘንድ  ይፈቀድልኝ ” ብለው ከእስርቤት ደብዳቤ ጻፉ ። በደብዳቤው መሰረት ከተፈቀደላቸው በኋላም  የሰላሌና የበጌምድር አስተዳዳሪ የልዑል ራስ ካሳ ኃይሉን ጦር ተቀላቅለው ተንቤን ላይ በተካሄደ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ጀግናው ሊጋባው በየነ  ተንቤን አባያዲ ማይሎሚን ተራራ ላይ  በጀግንነት እየተዋጋ የካቲት  19  በ1929 ዓ.ም በክብር ከነኩራቱ ለናት ሃገሩ ተሰዋ ።
   ————–
   ስንት ባንዳና ተላላኪ ለጊዜያዊ ጥቅም ሃገሩንና ሞራሉን በሚሸጥበት ሃገር ላይ እንደነ ሊጋባው በየነ ባሉ ከጊዜያዊ ባለጠግነት ይልቅ ከነሞራላቸው ለሃገር በከፈሉት  የሞት ዋጋ ኢትዮጵያ  ነጻነቷን ልትጠብቅ ችላለች ። ለዚህም ነበር ድምጻዊ ግዛቸው ለሊጋባው በየነ በዘፈነው ዘፈን ላይ….
     ኧረ ምነው ምነው ፣
 ከሞተልሽ ሌላ የወደደሽ ማነው።
    ብሎ ያዜመለት ።
   —–
   በርግጥም ሊጋባው በየነ በወቅቱ ፖለቲካንና ሃገርን
   ለይቶ  ከጊዜያዊ የፖለቲካ ሥልጣንና ማሽቃበጥ ይልቅ  ለሃገር ሰርቶ መሞትን በተግባር አስተምሮናል ።
 
Filed in: Amharic