>
5:14 pm - Thursday April 20, 1719

" የሚሞትለት የሌለው የሚኖርለትም አይኖረውም ! " (ዲን. ብርሃኑ አድማስ)

” የሚሞትለት የሌለው የሚኖርለትም አይኖረውም ! “

ዲን. ብርሃኑ አድማስ

“… ትዕግስትን እንደ ፍርሃት፣ አርቆ ለሀገር ማሰብን እንደጅልነት ቆጥሮ ቤትህ ካልገባሁ፣ ሚስትህ እንትና ጋር ስትጫዎት ሰላየኋት እኔም ለአንድ ቀን ከእርሷ ጋር ልጫዎት የሚል ዐይነት ማቆሚያ የሌለውን መዳፈር አሁንስ በቃ ..”
———-
      ከሀገር ውጭ ከሚኖሩት አንሥቶ ሀገር ውስጥ እስካሉት ድረስ በርከት ያሉ ሰዎች ደውለው ኢሳት ቴሌቪዥን የማኅበረ ቅዱሳን መግለጫ ላይ የሚያደርገውን ውይይት እንድመለከተው ጋበዙኝ። ቴሌቪዥኔ ስለማይሠራ አይቼም ስለማላውቅ ወደ ዩ ቲዩብ አድራሻቸው ገብቼ በደካሜ ላይ ሰዐት እላፊ ተመለክትኩት። ተከታትዬ ስጭርስ በማኅበሩ መግለጫ እነርሱ ላይ እንደተፈጠረ ያሰብኩት የመገረም ዐይነት ስሜት እኔም ላይ ተጋባብኝ። ለዚህ ስሜት አሳልፎ የሰጠኝ ደግሞ እነርሱ ያላቸውን መረጃ፣ መረዳት፣ ግንዛቤ እና ዕውቀት እንደመጨረሻ እውነትና እውቀት ወስደው መግለጫውን በዚያ መመዘኛ እየመዘኑ ሲናገሩ መስማቴ ነበር። ምንአልባት በሰዎች ጥቆማ በዩቲዩብ ከማያቸው የተወሰኑ ፕሮግራሞች በቀር የቴሌቪዥን ፕሮገራሞችን በመደበኛነት ካለመከታተሌና እኔ ለማኅበሩ መግለጫ ካለኝ የስሜት ቅርበት አንጻር ሆኖ ካልሆነ በቀር የየሚዲያው ትንታኔ እንዲህ ዐይነት ከሆነ በርግጥም ሀገራችንን አደጋ ውስጥ ከጣሏት ነገሮች አንዱ የብሮድካስት ሚዲያውም ነው ማለት ነው።
   ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ከመጀመሬ በፊት እንዲህ የተጻፈ መግለጫን በአግባቡ ለመረዳት ሳይጥሩ የየራሳቸውን መረዳት (በተለይ ሲሳይ) በርግጠኝነት የሚያናግራቸው ምን ሊሆን ይችላል ብዬ አንደኛው ተወያይ ጋዜጠኛ ደጋግሞ እንደሚናገረው ራሴን በእነርሱ ጫማ አስገብቼ ለማሰብ ሞከሬ ነበር። ለጊዜው የመጡልኝ የሚከተሉት ነበሩ። የመጀመሪያው መግለጫው ያገኘው ሰፊ ተቀባይነትና እየፈጠረው ያለው ውይይት የፈጠረባቸው ስጋት ለማኅበሩ ካላቸው ግምትና እነርሱ ካላቸው የፖለቲካ ፍልስፍና ጋር ተቃርኖባቸው ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ ከራሳቸው እውነተኛ ስሜት የሚነሣ ሆኖ (ልክ እንደ መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ሚዲያዎች) እነርሱ የሚያምኑበትና የሚሠሩት ብቻ ሀገራቸውን የሚጠቅምና ማኅበረሰብ የሚያንጽ የሌላው ግን ሀገር የሚያፈርስ መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ሌላው ለራሱ የግል ጥቅም ወይም ሲሳይ እንደሚለው የፖለቲካ ኮተት ከጀርባው ይዞ እነርሱ ደግሞ ሀገር አስቀድመው ነጻና ገለልተኛ ሆነው የሚሠሩ መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ለመግለጫው አሁናዊ ምክንያት የሆነውን ክስተት ይህን ያህል ትልቅ አድርጎ ካለማሰብ ጋር አሁንም ሲሳይ እንዳለው እነርሱ ሓላፊነት የሚሰማቸው ማኅበሩ ግን ኃላፊነት የጎደለው መስሎ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ከዚህ ሁሉ ውጭ ሊሆን ይችላል።
    በኋላ ግን ሁሉንም አማራጮች ሊያጠቃልል የሚችል የአንድ ምሁር አባባል አስታወስኩ። “We all have an inherent and natural tendency to search for evidence that already meshes with our beliefs” – ‘ ሁላችንም እምነት አድረገን የያዝነውን ነገር የሚያረጋግጥል ማስረጃ የመፈለግ ተፈጥሮአዊ የሆነ ዝንባሌ ወይም አድሎ አለን’ የሚለው የቶም ኒኮላስ አባባል(Tom Nicholas, The Death of Expertise, P.41)። በርግጥም ምንም ያህል የማያዳላ ቢመስለው ሁሉም ለሚያምንበት ያዳላል።
    በእኔ እምነት ዛሬ ኢሳቶች ሲያደርጉት ያመሹት ይህንን ነው። ከፖለቲካ  አስተሳሰባቸውም ሆነ ከሚዲያ ፍልስፍናቸው ወይም ደግሞ ፓረቲ ካላቸው ከፓረቲያቸው ማኒፌስቶ የሚቃረን ለሚመስላቸው ሁሉ ላደሉለት ነገር የሚስማማ የሚመስላቸውን ወሬና ማሰረጃ የራቀው ፍረጃቸውን እንደቆሙለት ለሚያስቡት እምነታቸው ሲደርቱ አምሽተዋል።
     የእኔም ፍረጃ እንዳይመስል ለዛሬው አንዲት ትንሽዬ ማሳያ ላቅርብ።  በዛሬው ውይይታቸው ላይ ሲሳይ ካነሣቸው ሁሉም ሊባሉ ከሚችሉ ስህተቶቹ መካከል በጣም ያሳቀችኝን አንዷን ብቻ ነው የማነሣው። ሲሳይ ዛሬ የማኅበሩን መግለጫ ከከሰሰባቸው ነጥቦች አንዱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጨምሮ ማኅበሩ ከውጭ በመጡ አባቶች ደስተኛ አይደለም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ማኅበሩ የሕዋሃት ጫና ለመቀነስ ሲል በአመራሩ ላይ ብዙ የትግራይ ልጆችን አስገብቶ እንደነበርና እነርሱ በሚያሳድሩበት ተጸኖ ሊሆን እንደሚችል ማኅበሩ አካባቢ ካለ ሰው እንደሰማ አድርጎ አቅርቧል። ከዚህች ብቻ ሦስት አስቂኝ ስሕተቶቹን ማሳየት ይቻላል።
   የመጀመሪያው ለእርሱ የነገረው ሰው የማይሳሳት መሆኑ ነው። በርግጥ የነገረው ካለ ነው፣ ቢኖርም ማን እንደሆነ አናውቅም፣ ለሲሳይ ትንታኔ ግን ያ ሰው የማይሳሳትና በቂ ነው ማለት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ማኅበሩ ከጫና ለማረፍ ሲል ወያኔዎችን አስገብቶ እንደነበር አሁን አንዳንዶቹ ውጭ እንደሄዱ ከተናገረ በኋላ ጫና ያደርግበት የነበረው ወያኔ ከለቀቀና ሰዎቹም ከተሰደዱ በኋላም እንደገና በተፅእኖ ውስጥ እንዳለ ማቅረቡ ከራሱ መላምትም የሚቃረን አስቂኝ ነው። በጣም ያሳቀኝ ደግሞ የወያኔን ሰርጎ ገብነት የሚቃወመው ሲሳይ ለእርሱ የነገረውን ሰው እነርሱ ያስገቡት ተረኛ ሰላይ ወይም ሰርጎ ገብ ተደርጎ ሊታሰብ የሚችል አለመሆኑን ማሰብ አለመቻሉ ነው።
   ይህን ጉዳይ ያስመረጠኝ ግን ሌላ መሠረታዊ ምክንያት አለ። እኔ በማኅበሩ አመራርነት በምሳተፍበት ጊዜ ከወያኔ ባለሥልጣናት በተለይ ደግሞ አሁን እሥር ላይ ከሚገኙት ከአቦይ ስብሐት ጋር በሚኖረን ሁሉ ውይይት ተደጋግሞ የሚነሣብን አንድ ክሥ ነበር። ለምን ዕርቁን ፈለጋችሁት? የሲኖዶሱን ዕርቅ የምትፈልጉት የአማራን የበላይነት ለመመለስ ለምታደርጉት ፖለቲካ አመቺ ስለሆነ ነው። በአመራሩ ውስጥ በቂ ቁጥር ያለው የትግራይ ልጆችን የማታስገቡትም ለዚህ ነው፤  አሁን ሲሳይ የከሰሳቸውን ዐይነቶች አንሥተን አሉ ስንል ደግሞ እነርሱማ ተጎታች ምንም የማያውቁ ናቸው ይሉን ነበር። ከዚህም ሁሉ በላይ አቡነ መሮቆሬዎስን እነርሱ እንዳልነኳቸውና ፈርተው እንደሸሹ ሰለዚህም አቡነ ቴዎፍሎስን የገደለውን ደርግ ሳናወግዝ እነርሱ ላይ የምናነሳው ጥያቄ ተገቢ እንዳልሆነ ተደጋግሞ የምነወቀስበት፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ አቡነ ጳወሎስንም ሆነ አቡነ ማትያስን በትገሬነታቸው እንደማንደግፋቸውና ለእኛ የሚቀርቡትን አቡነ መርቆሬወስን ማስመጣት እንደምንፈልግ ተደርገን እንከሰስ ነበር።
     ይህን ክስ አሁን ድረስ የምሰማው መሆኑ ሲይስገርመኝ ይኖራል።ይህን አባባላቸውንም ከማኅበሩ አመራር ውስጥ አማራ አይደሉም ብለው ላሰቧቸው በመንገር መለያየት ለማምጣት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደርጉ ነበር። ዛሬ ሲሳይ አንድ ሳያስቀር ይህንኑ በግልባጩ ደግሞት ስሰማው የፖልቲከኞች እናታቸው አንድ ናት እንዴ አሰኝቶኛል። ሌላው ቀርቶ ልክ ወያኔዎች ራሳቸውን ከደርግ እያነጻጸሩ እንዴት እንደሚሻሉ ይሰብኩን እንደነበረው ሲሳይ እንዴት ከወያኔ እንደሚሻሉ በማቅረብ ሲሞግት ሰመለከተው ፖለቲክኞች ጉዳያቸውና ፍልስፍናቸው ካልሆነ በቀር ፐሮፓጋንዳቸውን እምነት እድረገውት እንደሚኖሩ አመንኩ። የእኔ ጉዳይ የአንዱ ከሌላው መሻልና አለመሻል አይደለም፣ ያ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፣ እንደተመልካቹና እንደተጠቃሚው ሁሌም የሚነገር መሆኑን እንኳ ተትን በማስረጃ ቢታይና እንደተናገረው ቢበልጥ ንግግሩ የሚበልጥ ሰው የሚናገረው አይመስለኝም። ያንን ሕዝብ ይናገረው።
    ለውይይቱ ማኅበሩ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ቢሆንም ከሌለኝ ጊዜ ላይ በሌሊት ይህን እንድጽፍ ያደረገኝ ንግግራቸው በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ቢፈተሽ በጠቀስኩት መንገድ ስሕተት መሆኑ ሊረጋገጥ የሚችል መሆኑን ለማሳየት ብቻ ሳይሆን የመግለጫው ጭብጥ እኔ ሙሉ በሙሉ የምጋራው መሆኔንም ለመግለጽ ነው።
    ጉዳዩ የአንድ አደባባይ የአንድ ምሽት ጉዳይ ሳይሆን ትዕግስትን እንደ ፍርሃት፣ አርቆ ለሀገር ማሰብን እንደጅልነት ቆጥሮ ቤትህ ካልገባሁ፣ ሚስትህ እንትና ጋር ስትጫዎት ሰላየኋት እኔም ለአንድ ቀን ከእርሷ ጋር ልጫዎት የሚል ዐይነት ማቆሚያ የሌለውን መዳፈር አሁንስ በቃ የሚል አድርጌ ስለወሰድኩት ነው።
    በጣም የገረመኝ ደግሞ ተንኳሹን ረስተው ተተንኳሹ ላይ ያሳዩት ርብርብ ነው። ሌላው ቀርቶ የዚህኛውን የተገፊውን ማኅበረሰብ ስሜት አለመረዳት ብቻ ሳይሆን ተደራራቢው የተገፊነት ስሜትና የተንኳሾቹ ፉከራ ለሀገር ያለውን ጉዳት በቅጡ እንኳ ሳይረዱ ይህን ያክል መናገር በእውነት ያስተዛዝባል።
    በዚሁ አጋጣሚ ከመግለጫው የወሰድሁትን ጭብጥ ልንገራችሁና ልፈጽም። የሌሎችን ይገባኛል የሚያሰኝ አስተምህሮ ባይኖረኝም የእኔን አሳልፎ የሚያሰጥ ግን አይደለም። ሲሳይ በግልጽ እንደተናገረው የምገድልለት እምነትና ዐላማ ባይኖረኝም ጌታ በወንጌል እንደተናገረው የምሞትለት ግን አለኝ። የምተንኩስለት ተልእኮ ባይኖረኝም የምቆምለት ግን አለኝ። ስለዚህም እቆምለታለሁ፣ ካሰፈለገም ሌሎች እንደተሰውለት እኔም እሰዋለታለሁ ማለት ይመስለኛል።  ይህ ከሆነ እኔም በሙሉ ልብ እቀበለዋለሁ። የሚሞትለት የሌለው የሚኖርለትም አይኖረውምና።
Filed in: Amharic