>

ከፖሊሲ አውጪነት ወደ ክላሽ አንጋችነት...!!! !  (ሳምሶን ሚሀይሎቪች)

ከፖሊሲ አውጪነት ወደ ክላሽ አንጋችነት…!!! ! 

ሳምሶን ሚሀይሎቪች

*….የዛሬ ስድስት ወር በአፍሪቃ ቀንድ ትልቁ ጦር የእኛ ነው ያሉን ሰዎች እንዲህ ሆነው ከማየት የሚያሳዝን ፣ የሚገርም ሁነት ይኖር ይሆን?
ጦርነት አማራጭ ስታጣ ፣ አማራጮች ኖሮህም የተሻለው መንገድ ነው ብለህ የፖለቲካ አላማ ለማሳካት የምትገባበት ስልት ነው። ጦርነት በራሱ ግብ አይደለም ወደ ግብህ ለመድረስ የምትከተለው ስትራቴጂ እንጂ። ህወሃት ጋር ግን ጦርነት ስልት ሳይሆን ‘ ባህላዊ ጨዋታ ‘ ወይም በራሱ ግብ ነው። ዝም ብሎ መዋጋት ፣ እንዲሁ በባዱ ህዝብ እያስፈጁ እምበር ተጋዳላይ የህወሃት ሰዎች ህመም ነው። ይህ ያለምክንያት አልሆነም። ህወሃት እኛ ከሌሎች የተለየን ፣ የላቅን ህዝቦች ነን የሚል ፋሽስታዊ ዕይታ ስላለው ነው። ሂትለር የጀርመን ቻንስለርነቱን እንደ ጨበጠ ጀርመንን በኢኮኖሚ አፈር ድሜ ያበሉትን የአንደኛው አለም ጦርነት ፍጻሜ ስምምነቶችን እምቢ ማለትና ዳግም ድርድር ማድረግ ይበቃው ነበር። ጀርመናውያን ” ኣርያን ዘሮች ናቸው ” በሚለው ብሽቅ ህሳቤው እስከ ሌኒንግራድ ጥግ ሄዶ የተዋጋው ልዩ ፣ ሀያል ዘር ነን የሚለው ዕብሪቱን አለም እንዲያውቅ ሰለፈለገ ነው።
የቀድሞው ኮሚኒኬሽን ሚኒስትራችን ኣይተ ጌታቸው ረዳ ከሆነ ዋሻ ውስጥ ሆኖ ፎቶ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይለጥፋል። የሬዲዮ ቃለምልልሶችን ይሰጣል። ጌታቸው ሲናገር ደጋግመው ከሚያዳምጡት ሰዎች መሀከል ነኝ። የጌታቸው ረዳ ቃለመጠይቆችን ያህል ስለ ህወሃት ነባራዊ ሁኔታ ገላጭ ያለ አይመስለኝም:
፩. ባለፉት ሁለት ወራት ጌታቸው ረዳ የሰጣቸውን ቃለመጠይቆች ልብ ብሎ ላደመጠ ህወሃት እንደ ፓርቲ በጋራ መወሰን እንዳቃታት ይረዳል። የጌታቸው ቃለምልልሶች አንድ አፈ ጮማ በራሱ የሚያናበንባቸው ተውኔቶች እንጂ ህወሃት በሽሽት ላይ እንዳለ የክልል መንግስት ወይም ፓርቲ በጋራ ያወጣቸው መግለጫዎች አይደሉም። አመራሩ በያለበት ተበታትኗል ከፊሉም የጦርነት ሰለባ ሆኗል። የአመራር ማዕከል የሌለው ስብስብ ደግሞ የተጠና የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድና ስትራቴጂ አውጥቶ መንቀሳቀስ አይቻለውም። ይሄ በራሱ ትልቅ ክፍተት ትልቅ ጉዳት ነው።
፪ . የህወሃት አመራር መበተኑ እርግጥ ቢሆንም ትልቁ ችግሩ ቀሪው ሀይል በጋራ ሆኖ የጦርነቱን ግምገማ ማድረግ አለመቻሉና አዲስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራር መምረጥ አለመቻሉ ነው። ወጣቶቹ የህወሃት ካድሬዎች መጪውን የሽምቅ ፖለቲካ ህወሃት ሳይሆን አዲስ የተባበረ የትግራይ ኮንግረስ ይምራው እያሉ ነው። ሽማግሌዎቹን ከፖለቲካው ገሸሽ የማድረግ ትንቅንቅ እዚህም እዚያም ተጀምሯል። ከጥቂት ወራት በኃላ ሁለትና ሶስት የሽምቅ ሀይሎች ትግራይ ውስጥ አለን ማለታቸው የማይቀር ነው።
፫. የጌታቸው ረዳን ቃለመጠይቆች በጥንቃቄ ያደመጠ ሰው ሌላ የሚረዳው ይልቁ ነጥብ ሰውየው ከስትራቴጂስነት ( በፊትስ ነበር ወይ ? ) ወደ ፕሮፖጋንዲስትነት መቀየሩን ይረዳል። የጌታቸው ቃለ መጸይቆች እየዋሉ እያደሩ የትግራይን ፖለቲካ መጪ አቅጣጫ ከማሳየት ይልቅ ባዶ ተስፋን መመገብና የመከላከያ ሹማምንትን መዝለፍ ላይ እያተኮሩ ነው። ጌታቸው ቁንጮ የህወሃት አመራር እንደመሆኑ ስድቡን ተከታዮቹ እንዲሰሩት አድርጎ እርሱ አጃንዳ ማመላከት ላይ ቢያተኩር ይሻል ነበር። ምናልባትም ያለበት ሁኔታ ፣ ብስጭቱ ከሸራተን ወደ ራያ ሰርጣ ሰርጦች የወረደበት ፍጥነት ስሜቱን መቆጣጠር እንዳይችል አድርጎት ይሆናል።
የዛሬ ስድስት ወር በአፍሪቃ ቀንድ ትልቁ ጦር የእኛ ነው ያሉን ሰዎች እንዲህ ሆነው ከማየት የሚያሳዝን ፣ የሚገርም ሁነት ይኖር ይሆን ?
ፎቶ (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ ድምፃዊ ሙሉጌታ ካሳ፣ መዘክር አባዲ (የአባዲ ዘሙ ልጅ)፣ ድምፃዊ አማኑኤል፣ ጌታቸው ምላሱ እና የቀድሞ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕረዜዳንት #ታጋይ ፕ/ር ክንደያ ናቸው። የአባዲ ዘሙ ልጅ መዘክር ከጌታቸው ረዳ ጋር
Filed in: Amharic