>

አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ በግፍ የተገደለውን የኦሮሞ ልጅ ብዛት ቤት ይቁጠረው!  (ተረፈ ጌታቸው)

አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ በግፍ የተገደለውን የኦሮሞ ልጅ ብዛት ቤት ይቁጠረው! 

ተረፈ ጌታቸው

 

*….አንዴ ኦነግ ፤ አንዴ ሸኔ፤  አንዴ ቶርቤ እያሉ… እያስባሉ ያጭዱናል!
እንኳን እናቴ ሞታ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይልኛል እንደሚሉት ከሰሞኑ እጅግ ክፍት ብሎኝ ሰንብቼ እያለሁ ዛሬ አንድ ወዳጄ አንድ ቪዲዮ ልኮልኝ ብመለከተው ሀዘኔ ቢበዛብኝ ሸክሜን ብትጋሩኝ ስለ መጻፍ ጀመርኩ::
እንደማትሳፍሩኝ እገምታለሁ:: ብታሳፍሩኝም ግን ጥፋቱ የእናንተ ሳይሆን በስማችን በሚነግዱ የብሄር ነጋዴዎች እንደሆነ ስለማውቅ ብቻዬን በመሆኔ ባዝንም አልቀየማችሁም::
እኔ ነጌሌ ቦረና የተወለድኩ በማህበረሰብ ማንነቴ የቦረና ኦሮሞ ነኝ:: ሰቦ ነኝ:: ከሰቦም መጣሪ ነኝ:: በማንነቴ ኩራት ተሰምቶኝ ያደግኩ ቅብርር ያልኩ ቦረና ነኝ:: በዜግነቴ ኩርት ያልኩ ኢትዮጵያዊ::
የተገኘሁበት ማህበረሰብ ደግ: ሩህሩህ ነው:: አፍቃሪ:: ክፋትንና ግፍን የሚፀየፍ በቀልንም የማያውቅ ነው:: ቦረና የደም ካሳ አይወስድም:: ሰውም ሰውን ገደለ አይልም:: አኗሪና ገዳይ ቆቅ ጉራች: ዋቅ ጉዶ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለው:: ሟች ገዳይን ያጀግናል ይላል:: ሟችም ሊሞት: ገዳይም ሊገድል ከቤቱ አልወጣና የሚል በቀል የማያውቅ ማህበረሰብ ነው:: እንኳን 100 አመት 150 አመት እያለ ዘመኑን ሙሉ ሊያላዝን ይቅርና!
ስለ ተፈጥሮ ጥበቃ ከትምህርት ሳይሆን ከተፈጥሮ የተማረ: እንኳን ሰውን ይቅርና እንስሳ በአጠገቡ ሲያልፍ ነጋ ኦልቴ ብሎ የሚያልፍ ስልጡን ህዝብ:: ከእህቴ ጋር ስጣላ አያቴ በልጅነቴ አንተ መጣሪ ነህ:: መጣሪ ሴት አይመታ የሚል ምክሯ ሳድግ ገብቶኝ ሴት ልጄን ለመቅጣት እንኳን እጄን አንስቼ አላውቅም:: አምርሬ ስቆጣት እንኳን ከፍርሀት ይልቅ ብስጭት ነው የሚያደርጋት:: ዝምታዬ ነው ለሷ እውነተኛ ቅጣት::
ባደግኩበት ማህበረሰብ ቦረናነት የብሄር ጉዳይ ሳይሆን ሁሉም አማራ ይሁን ትግራዋይ: ጉራጌ ይሁን ወላይታ እጆሌ ቦረና ብሎ የሚነሳ ፍቅርንም ቁጣን የሚያውቅ አካታች ማንነት ነው:: የደም ወይም የሀረግ ጉዳይ ሳይሆን ቦረና በማደጉ ብቻ ሁሉም እኩል የሚወርሰው: እኩል የሚኮራበት: ማንም ባይተዋር የማይሆንበት ማንነት:: የምለውን እውነት ለመመርመር ከየትኛውም ማህበረሰብ የተገኘን ቦረና ለአምስት ደቂቃ ማናገር ብቻ በቂ ነው:: በዛች አምስት ደቂቃ አስሬ ቦረና ሲል ወይም ስትል ታደምጣላችሁ::
አባወራነት ለቦረና ስልጣን ሳይሆን ሀላፊነት ነው:: ሚስቱ የሰቀለችውን ሰሮራ እንኳን አውርዶ ወተት ለመጠጣት አይደፍርም:: እስኪሰጠው ይጠብቃል:: ጥጃ ጠብቶ ሳይጨርስ ላም አይታለብም:: ከጥጃዋ የተረፈውንና ላሚቷ ልትሰጥ የምትችለው ያህል አመስግኖ ይወስዳል:: ሰላምን አጥቆ ይሻል:: ስለሰላም አጥቆ ይፀልያል:: ይማፀናል::
እኔ ያደግኩበት ቦረናነት እኔ የማውቀው ኦሮሞነት እንዲህ አይነቱን ነው:: እጅግ ምኮራበት አምላክ የሰጠኝ ትልቅ ገፀ በረከት ቦረናነቴና ኢትዮጵያዊነቴ ነው:: በኔ ውስጥ ሁለቱ እንኳን ሊጣሉ ይቅርና ፍፁም ተዋህደው የማንነት ኩራቴን እጥፍ ድርብ አድርገውታል:: አንገቴን ቀና አድርጌና ደረቴን ነፍቼ እንድሄድ አድርገውኛል::
ነበር ልበል መሰለኝ!
ዛሬ ላይ ላንተ ነው የቆምነው: አንተን ነው የምንወክለው የሚሉ ቁማርተኞችና የፓለቲካ ነጋዴዎች አንገቴን እንድደፋ አድርገውኛል:: የከበረውን የኦሮሞ ማህበረሰብ እንደጨካኝ እና አረመኔ እንዲታይ: እንዲቆጠር አድርገውታል:: እንደማህበረሰብ ኩሩ ታሪካችንን አጥፍተው የነ ተስፋዬ ገብረአብ መጫወቻ አድርገውታል:: እስቲ ይታይችሁ አንድም የጭቆና ዲሪቶአቸው ማህበረሰብ በቀል አይደለም::
የተውሶ ጭቆና እንዴት አድ ኦሮሞ የተገኘበት ማህበረሰብ ላይ ይጭናል?! የብሄር ጭቆናን ከዋለልኝ መኮንን: አኖሌን ከተስፋዬ ገብረአብ ተውሶ እንዴት ይህን ሁሉ ብሩህ አይምሮ ያለው ወጣት ያደነዝዝበታል? የድንጋይ ሀውልት ሰርተው እንዴት ድንጋይ ያደርጉታል? እንዴት የጭካኔ አገዳደል አይነት መገለጫው ያደርጉትል?
ምን አለ ስለጀግንነቱ ስለ ለጋስነቱ ስለ ሀገር ወዳድነቱ ስለ ፍትሀዊነቱ አስተምረው መልካም ሰው: መልካም ዜጋ: መልካም ብል ሚስት ልጅ አባት እናት እህት ወዳጅና ጓደኛ እንዲሆን አድርገው ቢቀርፁት? እኔ ከወላጆቼ አኩሪ ማንነትና ታሪክ ተምሬ ቅብርር ኩርት ያልኩ ቦረና ሆኜ እንዳደኩት ሁሉ የኮራች ቦረና የኮራች ኢትዮጵያዊ ልጅ እንዳሰድግ እክል ባይሆኑብኝ የጭካኔ ጥግ ባያደርጉኝ ምን ነበረበት? ኩራቴ እና መልካም ስሜን ባወርሳት ምናቸው ይጎዳል? ልጄን በመልኬ እንደምሳሌዬ አድርጌ እንዳሳድግ እሱን ብቻ ቢፈቅዱልኝ ምን ነበረበት?
የሀገር ሀብት ንብረት ስልጣናቸውን ሽፋን አድርገው ይውሰዱ መቼም እምብርት የሌለው አልጠግብ ባይ ምን ይደረጋል? እንዴት ስልጣናቸውን መከታ አድርገው በማንነት ኩራትና መልካም ስም ይሰርቃሉ? እንዲህስ ላለው ሌባ ቅጣቱ ምንድነው? ብሩህ ጭንቅላትን ከእውቀት ይልቅ በጥልቻ ሞልተውት ድንጉጥ ወጣት ምማረትስ ጥቅሙ ምንድነው? ትርፉስ ምንድነው?
ዛሬ ልቤ በሁለት ጎኑ ይደማል:: የሌላ ማህበረሰብ ተወላጅ የሆኑ በተለይም ደግሞ በአማራነታቸው ብቻ በግፍና ይህ ነው በማይባል ጭፍጨፋ ሲገደሉ ወንድሞቼ እህቶቼን እናቶቼንና አባቶቼን ነውና የሚገድሉት ልቤ ክፉኛ በሀዘን ተወግቶ ይደማል:: በሌላ ጎኑ ደግሞ ግድያው በኔ በኦሮሞውና እኔ በተገኘሁበት ማህበረስ ስም እና አባልት ነውና ግድያውና ጭፍጨፋው የሚከናወነው ልቤ በውስጤ የሚሞትብኝ እስከሚመስለኝ ድረስ ልቤ በሀፍረት ፍላፃ ይወጋል::
አንገቴን ደፍቻለሁና እዘኑልኝ አፅናኑኝም እንዳልል አንገቱ የሚቀላው ብዙ: ወረፋ የሚጠብቀው እጅግ ብዙ ነውና እናቱ የሞተችበትም: እናቱ ገበያ የሄደችበትም እኩል ያለቅሳል እንዲሉ ይሆንብኝና እተወዋለሁ:: እስቲ አስቡት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ እስር ቤቶች ውስጥ ስለታጎሩ የኦሮሞ እናቶች: አባቶች እና ህፃናት ሪፓርት ካወጣ ቀናት ቢሆኑትም የኦሮሞን ማህበረሰብ ከወገኖቹ: ከወንድሞቹ ነጥለውና ብቻውን አስቀምጠውት ስላለ ጉዳዬ ብሎ የተወያየበት ብዙኃን መገናኛ ሁለት ቢበዛ ሶስት ቢሆን ነው:: በኦሮሞ ስም የሚምሉና የሚገዘቱት እነ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ በግፍ የተገደለውን የኦሮሞ ልጅ ብዛት ቤት ይቁጠረው!
አንዴ ኦነግ አንዴ ሸኔ አንዴ ቶርቤ እያሉ ያጭዱናል:: ከሁሉ የሚገርመኝ ነገር እነ አብይ አህመድ ማንነት ተኮር ጥቃት የልም አልተደረገም ለሚል ክህደት የሚያቀርቡት መሟገቻ <<ብዙ የተገደለው ኦሮሞ ነው>> የሚል ነው:: ኦሮሞ ሞት ይወድለታል? የኦሮሞ ነብስ የሰው ነብስ አይደለም? በሞቱ የሚጎዳና በድንገተኛ ሞቱ የሚደማ ልብ ያላት እናት የለችውም? አባት እህት ወንድም ልጅ ሚስት ወይም ባል የላቸውም? ኦሮሞ ነውና የሞተው አትጨነቁ ሲሉኮ ዶሮ እንኳን የሞተ አይመስላቸው? ግን በስማችን ይምላሉ:: ይገዘታሉ::
እንደው ነገርን ነገር ያነሳዋልና በወለጋ የአማራ ተወላጆችን ጭፍጨፋ ሲያስተባብል የኦሮሚያ ፓሊስ ኮሚሽነር ምን አለ መሰላችሁ? <<የተገደሉት ከወሎ የመጡት ናቸው:: ወሎ ደግሞ ኦሮሞ እንጂ አማራ አይደለም::>> የሚል ማብራሪያ ይዞ መጣ:: አስቡት እንግዲህ ከታሪክ ግድፈቱና ወሎ ኬኛ ከማለቱ ባሻገር ኦሮሞ ከሆነ በግፍ የተጨፈጨፈው ችግር የለውም ነው:: ወይም ይመስላል::
ጃዋር ተከበብኩ ያለ ጊዜም 57% የሞተው ኦሮሞ ነው ሲል ነው አብይ አህመድ የተናገረው:: ብቻችንን ነጥለው ለማስቀረት የሰሩትን ስራ ስለሚያውቁት <ስንኖር ኢትዮጵያዊ: ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ>> እንሆናለን ያሉን ሁሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን አትረበሹ የሞተው ስው ሳይሆን ኦሮሞ ነውና አይዞአችሁ ይሉናል:: ቀን ከሌት እየጨፈጨፉት ጭንቅላትህን ማደንዘዣና የጥላቻ ዲሪቶ መከናነቢያ የአኖሌን የድንጋይ ሀውልት ይሰሩልናል:: በድንጋይ ላይ ድንጋይ አድርገው ያን የመሰለ ብሩህ ጭንቅላት ያለው ማህበረሰብ ጠፍጥፈው ይሰሩታል::
በምናውቃት ቦረና ላይ በሰላም መኖር ከልክለው ተለጣፊ ስም እየሰጡ በግፍ እየገደሉት ከቦረና 580 ኪሎ ሜትር ርቃ ያለችውን እና የማናውቃትን አዲስ አበባ ፊንፊኔ እያደረግንልህ ነውና ወይ አርፈህ ተገዛ ካልሆነም ብንጨፈጭፍህ የሰብአዊ መንት ኮሚሽን የሚያወጣውን ሪፓርት አንብቦ እንኳን የሚራራልህ አሳጥተንሀልና በአደባባይ እንገልሀለን ይልሀል:: ወይ አራጅ ካልሆነው ታራጅ ከመሆን ውጪ አማራጭ ያሳጡት ምስኪን ማህበረሰብ ነው::
ሀጫሉ ሁንዴሳ እውነቱን ነው በመጨረሻ ከOMN ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በብልፅግና ዘመን የተረፈን ስድብ ብቻ ነው ያለው:: ተጠቃሚው ጥቂት ካድሬ እንጂ ለትግራይ ገበሬ ህዋኃ. ምንም እንዳልፈየደው ሁሉ ለኦሮሞም ገበሬ ከመሸማቀቅና ከሀፍረት ውጪ ምንም የሚተርፈው ነግር የለም:: አይኖርምም:: የነ ታከለ ኡማ ዲዛይነር ልብስ መልበስ: የነአዳነች አቤቤ ማሸብረቅ: የነ አባ ዱላ ባለሀብት መሆን ለገበሬው ዘር ለተጠማው ውሀ አይሆንም:: የአብይ አህመድ የሶፉመር ዋሻን ቤተ መንግስት ውስጥ መገንባት አንድ ኦሮሞን የኑሮ ውድነቱ ከሚፈጥርበት ጭንቀት አይታደግም::
ምቾቱን ለእነሱ: ሀፍረት መሸማቀቅና አይዞህ ባይ ማጣትን ለማህበረሰቡ ነው እየሰጡት ያሉት:: ትላንት ህዋኃት ለትግራይ ህዝብ ጥቅም መሆን እንዳልቻለና 1.5 ሚሊዮን ትግራዋህን ከሴፍቲ ኔት እንዳታደገ ሁሉ የኦሮሙማ ፕሮጀክት ያነገበው የአብይ አህመድ መንግስት ለኦሮሞ ማህበረሰብ የሚፈይደው ነገር የለም:: የማህበረሰብ ትርፍ የንፁኃን አማራ: የንፁኃን ኦርቶዶክሳዊያን ደም ከምድር ወደ ፈጣሪው መጮህ የሚይመጣው መአት ብቻ ነው::
እኔ ምነው ፊንፊኔ ቀርቶብኝ የዘመዶቼ ሞት በቀረልኝ:: እኔ ምነው ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ትሆናለህ የሚል እብሪት ቀርቶብኝ በሀዘኔ ባዶ ድንኳን ታቅፌ ባልተቀመጥኩኝ! ወሎ ኬኛ ቀርቶብኝ ለልጄ ማወርሰው መልካም ስምን ባስቀሩልኝ:: ዘመዶቼ ድንጉጥና ድንዙዝ ከመደረግ በተረፉልኝ::
አንደልማዴ አንገቴን ቀና አድርጌ እንድሄድ በደግነትና በርህራሬ በሚታወቀው የማህበረሰብ ዝና ደረቴን ነፍቼ ዳግም በተራመድኩ:: ወይኔ እኔ ቦረናው የነ ተስፋዬ ገብረአብ መጫወቻ ሆኜ ልረፈው!!! የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ ውስጥ በኦሮሞች ላይ የሚፈፀመውን ግፍ ቁብ የሚሰጠው ብዙኃን መገናኛ ቢጠፋ ወሬ ማዳመቂያ እንኳን የሚያደርገው ይጥፋ?! እነ አብይ አህመድ ምን ያህል Culture Genocide በኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ እንዳደረሱ ፈጣሪ ያሳያችሁ!!!!
ደጉን ማህበረሰባዊ ኦሮሞነታችንን ነጥቀው በአልጠግብ ባይ:ስግብግብ: ጨፍጫፊ ፓለቲካዊ ኦሮሞነት (ኦሮሙማ) ሊተኩት እየጣሩ መሆኑን ይህ የኦሮሙማ ፕሮጀክት እንኳን ማህበረሰባዊ ኦሮሞነትን ሊጠቅም ሊያስተዋውቅ ይቅርና ብዝኃነታችን: ህብረ ብሄራዊነታችንን: ኢትዮጵያዊነታችንን unique ባህል እና እሴታችንን ሰልቅጦ አንድ ወጥ ኦሮሞነት ለመፍጠር የሚዳክር ያን አላማ ለማሳካት ደግሞ የሚያርድ የሚያስር የሚጨፈጭፍ በመሆኑ የኦሮሞ ማህበረሰብ ቀንደኛ ጠላት ነው:: የመልካም ስም ሌባ!! የመልካም ባህል ሌባ!! የብዝኃነት ሌባ!! የኢትዮጵያዊነት ሌባ!! ብቻችንን ካለአዛኝ ያስቀረን ድንኳን ሰባሪ ነው!! ካላመናችሁኝ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ሪፓርት አንብቡት:: በየቤቱ ልጆቻቸው በግፍ የተገደለባቸው እናቶች መቼም ቤት ይቁጠረው!!!
Filed in: Amharic