>

ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ራያን የመሳሰሉ ግዛቶችን በተመለከተ ያለኝ የማይናወጽ አቋም...!!! (ኤርሚያስ ለገሰ)

ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ራያን የመሳሰሉ ግዛቶችን በተመለከተ ያለኝ የማይናወጽ አቋም…!!!

ኤርሚያስ ለገሰ

 

ላለፉት አስር አመታት በዚህ አጀንዳ ላይ  የማይናወጥ በመርህ ላይ የቆመ እምነቴን ሳራምድ ቆይቻለሁ። ዛሬም የተለወጠ አመለካከትም ሆነ የመፍትሔ ሐሳብ የለኝም።
 እኔ እንዲህ ነው የማስበው፣
አንደኛ ፡– የዜግነትና የነፃነት መብት የሰጠችኝን አሜሪካ ጨምሮ የትኛውም የውጪ ኃይል በዚህ ጉዳይ አያገባውም። ይህ የአንዲትን ሉአላዊት አገር መብት የመጋፋት የንቀትና እብሪት አስተሳሰብ የወለደው በመሆኑ ከወዲሁ ሊታረም ይገባል። የኢትዮጵያን ውስጣዊ ወሰን የማካለል ጉዳይ የኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያውያን ብቻ ነው። የውጪ ኃይሎች ሚና ሊሆን የሚገባው ድጋፍ፣ ክትትልና እርምጃ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የጦር ወንጀሎች፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል።
ሁለተኛ ፡- አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ችግሩን ያወሳስበዋል እንጂ አይፈታውም። <<ለአንድ ክልል ብለን ሕገ መንግሥት አናሻሽልም፤ ሕገ መንግስቱ የአፈፃፀም እንጂ የይዘት ችግር የለበትም>> ያሉት የዘመኑ ገዥ መደቦች ( ኦሮሙማም) በምንም ተአምር ችግሩን አይፈታውም።
ሶስተኛ፡-  የመጨረሻውና የማያዳግም መፍትሔው ኢትዮጵያውያን በሚያደርጉት የተቀናጀ ሕዝባዊ ሰላማዊ የእምቢተኝነት ትግል አፓርታውዳዊውን የፌዴራልና የክልሎች ሕገ መንግሥቶች አሽቀንጥሮ መጣል ነው። በምትኩም ኢትዮጵያን የሁሉም ዜጎቿ ባለቤት የሚያደርግ ሕገ-መንግሥት አፅድቆ ተግባራዊ ማድረግ ነው።
አራተኛ፡-  የመጨረሻውና የማያዳግም መፍትሔው (ቁጥር ሶስት) ጊዜ የሚፈጅ ከሆነ በሁለቱም ወገን ይገባኛል የሚሉት ማህበረሰቦች ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ማንነታዊ መረጃና ማስረጃዎቻቸውን አቅርበው በግልፅ ሕዝብ በሚከታተለው አደባባይ ክርክር ያድርጉና ሁለቱም በመረጡት ገለልተኛ አካል ውሳኔ ይሰጥበት።
አምስተኛ፡– የተራ ቁጥር ሶስት ወይም አራት ውሳኔዎች ወደ ተግባር እስኪለወጥ ድረስ አሁን በስራ ላይ ያለው የፌዴራል ፓርላማና ፌዴሬሽን ምክርቤት ግዛቶቹን “የአማራ  ክልላዊ መንግሥት” እንዲያስተዳድራቸው ውሳኔ ይስጥበት። ይሄ የሚሆንበት ምክንያት በአንድ በኩል የይገባኛል የማንነት ጥያቄ ባለበት ሁኔታ ‘የትግራይ ክልላዊ መንግስት’ ለሩብ ክፍለ-ዘመን ቦታዎቹን ስላስተዳደረ ፤ ቀጣዩን አመታት ‘የአማራ ክልላዊ መንግሥት’ ቢያስተዳድረው የፍትሐዊነት ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም።
ስድስተኛ:- “የአማራ ክልላዊ መንግሥት” ቦታዎቹን ተረክቦ በሚያስተዳድር ወቅት አንድም ኢትዮጵያዊ በዘሩና በማንነቱ ምክንያት እንዳይፈናቀል፣ አድሎ እንዳይደርስበት፣ ሃብት ንብረት የማፍራት መብቱ እንዳይረገጥ ተጠያቂነት ያለበት ሕግ እንዲያወጣ ማድረግ።
Filed in: Amharic