>
5:33 pm - Wednesday December 5, 2891

የዐረቦችና የፍልስጥዔማውያን ነጻ አውጪው ወያኔ...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የዐረቦችና የፍልስጥዔማውያን ነጻ አውጪው ወያኔ…!!!

አሰፋ ሀይሉ

     — ኢትዮጵያና ፅዮናዊት ወገናችን እስራኤል!
ወያኔ ሀ ብላ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ባወጀችበት በ1968 ዓ.ም. ላይ ባወጣችው 38 ገጾች ባላት የተ.ሓ.ህ.ት ማኒፌስቶ፣ ፀረ-ፅዮናዊ ድርጅት እነደሆነችና ከፍልስጥዔሞችና ከዐረብ ሕዝቦች ጋር በአጋርነት እንደምትቆም ሁለቴ ሶስቴ ምላና ተገዝታ ነበር፡፡
በወቅቱ የዐረብ ሀገሮች በሙሉ (እና ሱዳን፣ ግብጽ፣ ሊቢያና አልጄሪያን ጨምሮ) ፅዮናዊት ብለው የፈረጇትን ኢትዮጵያን ለሚወጉ ሀይሎች ሁሉ ፔትሮ ዶላራቸውን በገፍ አፍስሰዋል፣ የጦር መሣሪያዎችን አጉርፈዋል፣ ሥልጠናዎችን ሰጥተዋል፣ የጦር ካምፖችንና ነጻ መንቀሳቀሻ ቀጣናዎችን ለግሰዋል፡፡
ወያኔም (ከወቅቱ ፈጣሪዋ ከሻዕቢያ ጋር) የሚደርሳትን ያህል የድርሻዋን ፍርፋሪ ከዐረቦቹ ለመቀበል ስትል፣ በማኒፌስቶዋ ላይ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዬ ብላ ‹‹ከፍልስጥዔሞች ጋር በትግል አጋርነት እሰለፋለሁ፣ ፀረ-ፅዮናዊ ነኝ፣ የዐረብ ሕዝቦች ወዳጅ ነኝ›› በማለት አውጃለች፡፡
ከማኒፌስቶውና የወያኔ መሥራቾች ከጻፏቸው ድርሳኖቻቸው ማየት እንደሚቻለው፣ ወያኔ የቀራት ነገር በወቅቱ መሪዎቿ በብዛት ከዐረቡ ዓለም ጋር ግንኙነት ያላቸው ሙስሊሞች እንደነበሩት እንደ ሻዕቢያ ‹‹ዐረብ ነኝ›› ማለት ብቻ ነበር፡፡ ያንን ለማለት ግን ይሉኝታ ይዟት የተወችው አልመሰለኝም፡፡
በቅርቡ አይተ ኢሳያስ አፈወርቂ ወያኔ በመጀመሪያ ማኔፌስቶዬ ነው ብላ ጽፋ የመጣችውንና ዐረብ ነኝ ለማለት የዳዳችበትን፣ ነገር ግን ሻዕቢያ አስተካክለሽ አምጪ፣ ከመቼ ወዲህ ነው ዐረብ የሆንሺው? ብላ ተቆጥታ ለእርማት ስትልክባት፣ ወያኔ ይሄንኛውን ማኒፌስቶዋን አስተካክላ ጽፋ እንደመጣች የሚያሳዩ ሰነዶችን ይፋ አድርገዋል የሚል ነገር ሰምቼያለሁ፡፡ የወያኔ ማኒፌስቶ በሻዕቢያ ‹‹ይሄን ጻፊ፣ ያን አትጻፊ›› እየተባለ እንደተጻፈ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የተባለው የአይተ ኢሣያስ ሰነድ በእጄ ስላልደረሰኝ ምንም ማለት አልችልም፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው የኢትዮጵያችን ዕጣ – በወቅቱ ወያኔዎች የፍልስጥዔም ነጻ አውጪ ድርጅት ደጋፊነታቸውንና ፀረ-ፅዮናዊነታቸውን በይፋ ማኒፌስቶ አውጀው በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት ሲያውጁ፣ በአንድ በኩል ዐረቦች ሁሉ ድጋፍ ሲያደርጉላቸው ኖረዋል፡፡ ፍልስጥዔም ድረስ ሄደው የደፈጣ ውጊያ የሠለጠኑ ‹‹ታጋዮች›‹ ሁሉ ነበሩ፡፡
በሚያስገርም መልኩ ግን የፅዮናውያን-አጋር በመባል የምትታወቀው እና ወያኔዎች በማኒፌስቷቸው ‹‹ኢምፔሪያሊስት›› እያሉ በጠላትነት ፈርጀው እንደሚዋጓት የሚፎክሩባት የአሜሪካ በመንታ ገጽ የተሳለ ፀረ-ኢትዮጵያ ተሰላፊነት ነው፡፡ የዚህ ነገር ምስጢር እስካሁንም ሁልጊዜ ሲገርመኝ ይኖራል፡፡
በወቅቱ አሜሪካ በአንድ በኩል ኢትዮጵያን ‹‹አፍሪካዊቷ ፅዮናዊት!›› በማለት ለዓለም እያስተዋወቀች፣ በዙሪያዋ ባሉ የዐረብ ሀገሮች ሁሉ በጠላትነት እንድትፈረጅ በእጃዙር ኢትዮጵያ በዐረቦች ድጋፍ የምትወጋበትን የፕሮፓጋንዳ ጭድ ስታቀብል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘወር ብላ ኢትዮጵያ ውስጥ እግሯ የረገጠውን ሶቭየት ህብረትን (ራሺያን) በእጃዙር ለመዋጋት ስል ኢትዮጵያን ለሚወጉት ወያኔዎች (እና ሻዕቢያ) እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፌን እሰጣለሁ በማለት – በሁለት ወገን ስለት ባለው ሠይፍ ኢትዮጵያን ስታስወጋ ነበር፡፡ ወናው ዓላማዬ የኢትዮጵያን ሶሻሊስቶች ለመገርሰስ ነው በሚል የሶማሊያውን ዚአድባሬንም እስካፍንጫው አስታጥቃ የላከችብን አሜሪካ መሆኗ አይዘነጋም፡፡
‹‹ፅዮናውያን የኢምፔሪያሊስት አጋሮች›› ተብለው በወያኔ ማኒፌስቶ በጠላትነት በጠላትነት የተፈረጁት፣ እና በአሜሪካ በቁጥር አንድ የሚደገፉት እስራኤሎችስ በወቅቴ በኢትዮጵያ ጉዳይ የወሰዱት አቋም ምንድነበር? እስራኤላውያን በወቅቱ ያደረጉት ነገር ሁልጊዜ በኢትዮጵያውያን ሲወሳ ይኖራል፡፡ እስራኤሎች አቅፋ ደግፋ ከያዘቻቸው ከአሜሪካ ግልጽ ፀረ-ኢትዮጵያ ፖሊሲ አፈንግጠው – ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በብዙ ወታደራዊና የፀጥታ መስኮች ሲረዱና ሲያግዙ ቆይተዋል፡፡
የወያኔን የደፈጣ ተዋጊዎችን ሠርጎ ገቦች እንቅስቃሴ በመግታት ሀገራችንን ለማዳን በወቀቱ ለተደረገው ተጋድሎ ታላቅ እገዛን የሰጠውን በአጠቃላይ ድምሩ ወደ 24ሺህ የሚደርስ የኢትዮጵያን ሠራዊት በፀረ-ሽብርና በፀረ-ጎሪላ የውጊያ ሥልት በእስራኤል ሀገር በመውሰድና ወደ ኢትዮጵያ ኤክስፐርቶቻቸውን በመላክ ሳይታክቱ በማሰልጠን፣ ከኢትዮጵያውያን ጎን ቆመዋል እስራኤሎች፡፡ በአየር ሀይል፣ በስለላና ፀረ-ስለላ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ሳይቀር፣ እስራኤሎች በታሪካቸው ድሮም ሆነ አሁን፣ ለሁልጊዜውም ከኢትዮጵያ ጎን ሳይሰለፉ የቀሩበት አንዳችም ጊዜ የለም፡፡
እስራኤል የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ዘለዓለማዊ ወዳጅነቷን ያስመሰከረች፣ በመከራችን ቀን ከጎናችን የማትለይ፣ በደም፣ በታሪክና በባህል ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ጋር የተሣሠረች የቁርጥ ቀን አጋራችን ነች፡፡ በፀረ-ፅዮናዊ ጥላቻ ተሞልተው፣ ፍልስጥዔማውያንን እንደ ትሮይ ፈረስ በመጠቀም፣ የቆየ ጥላቻቸውንና ቂማቸውን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ለመወጣት የሚነሱትን የዐረብ ካሊፋቶች መደገፍ ማለት – ፀረ-ኢትዮጵያ ሀይሎችን መደገፍ ማለት ነው፡፡
በዘረኝነትና በፀረ-ኢትዮጵያዊነት የናወዘውን ወያኔን መደገፍ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያን የምንጊዜም ባለውለታ እስራኤልን ለማጥፋት መተባበር ማለት ነው፡፡ ዛሬ ዘጠኝ ሚሊየን ህዝብ ብቻ ያላት (ከኦሮሚያ የምታንስ) ትንሿ ፅዮናዊት ሀገር እስራኤል፣ በዙሪያዋ ባሉ በመቶ ሚሊየኖች በሚቆጠሩ አረቦች ጠላቶቿና የፍልስጥዔም ደጋፊ ነን በሚሉ የሽብር ሀይሎች ተከብባ ከመጥፋት ለመትረፍ ብቻዋን በቆራጥነት በምታደርገው ተጋድሎ ሁሉ ከጎኗ መቆም፣ እጅግ ፍትሃዊው የተቀደሰ ተግባር አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ ይህን ሀሳቤን ሁሉም ባይሆን ብዙው ኢትዮጵያዊ እንደሚጋራኝ አምናለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ይህ ዐረቦች ረዥም ፀረ-ኢትዮጵያ ካራቸውን ሲመዙበት የከረሙበት የነዳጅ ሀብታቸው  (ፔትሮ ኢኮኖሚያቸው) በቅርብ ዓመታት ውስጥ እሳት የጎበኘው ቋያ ሆኖ ወደ ግብዓተ መሬቱ እንደሚገባ ብዙ ፍንጮች እያመላከቱ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት አንቱ በተባሉ ታላላቅ የዓለማችን ምሁራን ከሚጻፉ የጥናት ውጤቶች አንዱ መጪውን የዓለማችንን የሀይል ምንጭ የሚመለከተው አንዱ ነው፡፡
በብዙዎቹ በዐለም ዙሪያ ከሚገኙ አንቱ የተባሉ ተመራማሪዎችና የጥናት ተቋማት የሚወጡ ሳይንሳዊ ትንተናዎች እንደሚያረጋግጡት፣ የዓለማችንንና የሰው ልጆችን አጠቃላይ የህልውና ዋስትና አሳሳቢ አደጋ እየከሰተበት ያለው ጉዳይ የአካባቢ ብክለት ነው፡፡ የዚህ ለዓለም አደጋ የጋረጠ የአካባቢ ብክለት ደግሞ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ እያበረከተ የሚገኘው የ‹‹ፎሲል ፊዩልስ›› አጠቃቀም ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ በአውሮፓና አሜሪካ እየተደረጉ ያሉ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች መኪናንና ሌሎች የሀይል ፍጆታዎቻቸውን፣ አካባቢን ከሚበክሉ የነዳጅ ዘይት አጠቃቀሞች ይልቅ፣ ከሰውና ተፈጥሮ ጋር ስምም ወደሆኑ የታዳሽ ሀይል ምንጮች ፊታቸውን እያዞሩ ነው፡፡
በመሆኑም ምናልባትም ከዛሬ 40 እና 50 ዓመታት በኋላ፣ የዓለማችን ኢኮኖሚ ከነዳጅ ዘይት አጠቃቀም ራሱን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በማላቀቅ፣ ለምድሪቱና ለእኛ ፍጡራኗ ተስማሚ የሆኑ ታዳሽ የሀይል ምንጮትን ወደ መጠቀም መሸጋገሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይህም ማለት በዚህ የአንድ ሰው የጉልምስና ዕድሜ በማይሞላ ከፊታችን በተዘረጋው መጪ ጊዜ ውስጥ፣ ፔትሮ ዶላራቸውን እየመነዘሩ ኢትዮጵያችንን ሲወጉና ሲያስወጉ የኖሩት ዐረብ ሀገራት በነዳጅ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚያቸው ተንኮታኩቶ፣ ቀድሞ ወደ ነበሩበት የበረሃ ኑሯቸው የሚመለሱበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ማለት ነው፡፡
ያንን ከፊታቸው የተዘረጋ አይቀሬ እውነት ያወቁት እንደ ካታር፣ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ፣ ወዘተ ሀገሮች ዛሬ ኢኮኖሚያቸውን ከነዳጅ ጥገኝነት አውጥተው ከዓለም የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር ለማቆራኘት እየተሟሟቱ ነው፡፡ እንግዲህ ፔትሮ ዶላሯም ታልቅና፣ እጃቸውን እያጨበጨቡ ሊቀመጡ የቀራቸው ጥቂት አስርት ዓመታት ነው ማለት ነው፡፡ ይህንንም የፅዮናውያን ሴራ እንደሚሉት አልጠራጠርም፡፡
ዐረብ ባትሆንም ‹‹የፍልስጥዔሞች ዋና አጋር›› ብላ ራሷን በመሰየም፣ በፀረ እስራኤልነት ከተሰለፉ ሀገራት ግንባር ቀደሟ የሆነችው ኢራን – ከሁለት ዓመት በፊት የመካከለኛው ምስራቅና የእስያ (እንደ ኢንዶኔዥያ ያሉ) ሀገራትን በሐይማኖት ጥላ ሥር አሰባስባ የጋራ ፀጥታና የደህንነት ምክክር የሚል ኮንፈረንስ አዘጋጅታ ስታበቃ፣ በማጠቃለያው ላይ በቀጥታ በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ንግግሩ የኢራኑ መሪ ለእስራኤል በቀጥታ ያስተላለፈውን መልዕክት – እዚያው በዚያው በኢራን ቲቪ እየተተረጎመ ስሰማው ባለሁበት ክው ብዬ ነው የቀረሁት፡፡ እንዲህ ይላል የኢራኑ መሪ ለእስራኤሎች፡-
‹‹ለእስራኤሎች የማስተላልፍላቸው የመጨረሻው መልዕክቴን  አድምጡ፣ መንግሥታችሁ አልሰማ ቢል እንኳ እናንተ መልዕክ ቴን ሰምታችሁ ተግባራዊ አድርጉ፣ የሰው ሀገር ቀምታችሁ ለዘለዓለም ልትኖሩ አትችሉም፣ የፓለስቲኒያን መሬት ቀምታችሁ እስከዛሬ ባልተፈለገ እንግድነት ቆይታችኋል፣ አሁን ግን ጊዜያ
ችሁ አብቅቷል፣ አንድ የምመክራችሁ ነገር ሁላችሁም ፅዮናው ያን ከዚህ ምድር ማቄን ጨርቄን ሳትሉ በቻላችሁት ፍጥነት  ሳይረፍድባችሁ አሁኑኑ አምልጡና ነፍሳችሁን አትርፉ፣ ምክሬን እምቢ ብላችሁ በሰው መሬት ላይ እንቆያለን ካላችሁ
ግን፣ ከዚህ ምድር በህይወት ተርፎ የሚወጣ ሰው አይኖርም፣  ማንም ሊያድናችሁ አይችልም፣ ከምድረ ገጽ እናጠፋችኋለን፣  ለነጋሪ ሳናስተርፍ ነው ከዓለም ካርታ ላይ የምንፍቃችሁ፣  አሁኑኑ ሳይረፍድባችሁ ውጡ፣ ይሄ እስራኤሎች ልብ ብላችሁ
 ስሙኝ፣ የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ ነው!››
የእውነት ክው ብዬ ነው የደነገጥኩት፡፡ እንዴ! በዚህ አሁን በምንኖርባት ዓለማችን ላይ እንዲህ ዓይነት ኦፊሴላዊ ዛቻ በላያቸው ላይ እየወረደባቸው በሰላም ተጎራብተው የሚኖሩ ሀገሮች አሉ ብዬ አልጠበቅኩምና ገረመኝ፡፡ እንዴ! ግልጽ የዘር ማጥፋት እወጃ እኮ ነው እስራኤሎቹ ዓለም እየሰማ በግልጽ የሚነገራቸው፡፡ እስራኤሎቹ ለምደውት ይሆናል፡፡ እኔ ከሩቅ ሆኜ የኢራኑን መሪ ዛቻ የማዳምጠው ሰውዬ ግን የሆነ አስፈሪ የሽብር መንፈስ ሰውነቴን ወረረኝ፡፡ ይገርማል፡፡
ጽሑፌን ስደመድም፣ እስራኤሎች የቆሙት ህልውናቸውን ለማትረፍ ነው፡፡ እስራኤሎች ቀን ከሌት የሚሠሩት ዙሪያቸውን ከከበቧቸውና ሊያጠፏቸው በአደባባይ ከሚምሉ የሩቅና የቅርብ ጠላቶቻቸው ራሳቸውን ለማዳን ነው፡፡ በግሌ – እንደ ኢትዮጵያዊ ብቻ አይደለም – እንደ አንድ ለሰው ልጅ እንደሚቆረቆር ሰብዓዊ ፍጡር – ዙሪያቸውን በአንገታቸው ላይ የካራ ስለት ከሚያፏጭባቸው ከእስራኤሎች ጎን ከመቆም በላይ – ፍትሃዊ ልለው የምችለው ነገር ፈልጌ ማግኘት ይቸግረኛል፡፡
ፈጣሪ የተስፋ ቃልኪዳን የገባላቸውን እስራኤሎችን አያሳፍርም፡፡ ኢትዮጵያ እና እስራኤል እስከ ተፍጻሚተ ዓለም በተስፋ ቃሉ ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያንና እስራኤልን ሲወጉና ሲያስወጉ የኖሩት ዐረቦች፣ እና እንደ ወያኔ ያሉ በዘረኝነት የናወዙ ቅጥረኞቻቸው፣ ዓይናችን እያየ ወደ ከርሰ-መቃብራቸው የሚወርዱበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ እየወረዱም ነው፡፡ ይወርዳሉም፡፡
የእስራኤል አምላክ እስራኤልን ይጠብቅ፡፡ ስንቱ የሩቅና የቅርብ ጠላት እጅና ጓንት እየሆነ ሲያደማት የኖረችው ምስኪኗ አይበገሬ ኢትዮጵያችንም – አንድ ቀን – በትውልድ ፊት ትንሳዔዋ እንደሚበሰር – ከልቤ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ 
ወገናችን ጽዮናዊት እስራኤልም ጭምር! 
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic