>
5:33 pm - Tuesday December 5, 9741

እኔን ብትመርጡኝ....!!! (በላይ በቀለ ወያ)

እኔን ብትመርጡኝ….!!!

በላይ በቀለ ወያ

እኔን ብትመርጡኝ ፣ ለሚመጣው ምርጫ
መብራትና ውሃ ፣ እንደ አለም ዋንጫ
በአራት አመት አንዴ ፣ መምጣቱ ይቀራል
ማይደፈርስ ውሃ
የማይጠፋ ብርሃን ፣ ቀን በቀን ይኖራል
።።።
ለሚመጣው ምርጫ
እኔን ብትመርጡኝ ፣ በውድም በግድም
ሰው እየረከሰ ፣ ኑሮ አይወደድም
ቀን በቀን ሰንጋ እንጂ ፣  ሰው አይታረድም
።፣፣፣
ለሚመጣው ምርጫ
እኔን ብትመርጡኝ ፣ ያላንዳች ውይይት
በዳቦ ቀይሬ  ፣ እያንዳንዷን ጥይት
ህዝቤን አጠግባለሁ
ለእያንዳንዱ ቤት ፣ በነፃ አድላለሁ ፣ በርሜል ሙሉ ዘይት
።።።።።
ለሚመጣው ምርጫ ፣ እኔን ብትመርጡኝ
እንድደግፋችሁ ፣ ድጋፍ ብትሰጡኝ
ቤት እየገነባሁ ፣ ከወዳደቀ ፖል
ያለ ሞት መበልፀግ ፣  ብርሃን ያለ አምፖል
ለእያንዳንዱ ሰው ፣ ሰጣለሁ በነፃ
እንኳንስ የሰው ነፍስ ፣ አይጠፋም አንድ ህንፃ
።።፣፣
እኔን ብትመርጡኝ ፣ ለሚመጣው ምርጫ
ለጠጪዎች ውስኪ ፣ ለቃሚዎች በርጫ
ለእግር ኳስ ክለቦች ፣ ለእያንዳንዱ ዋንጫ
ለፈረሶች ፍጥነት ፣ ለአህዮች እርግጫ
በነፃ አድላለሁ።
።።።
በሚመጣው ምርጫ ፣ እኔን ብትመርጡኝ
ድምፃዊ ሳትሆኑ ፣ ድምፅ ብትሰጡኝ
አንድ ዜማ ሰሪ ፣ አንድ ጊልዶ ካሳ
አንዲት ውብ ኮረዳ ፣ አንድ ውብ ጎረምሳ
አንድ ካሜራ ማን ፣
አንድ የባህል ቡድን ፣ ክሊፕ የሚሰሩ
ወይም ዘመናዊ ፣ ዳንስ የሚጨፍሩ
አስቀምጣለሁኝ ፣ በየ አንድ ሜትሩ
(ግጥሙን ለኔ ተውት )
።።።
ለሚመጣው ምርጫ ፣ እኔን ብትመርጡ
በዘር በሀይማኖት ፣ ምትቦጣቦጡ
ሰላም ያልገባችሁ ፣ ለፀብ የምትሮጡ
ከኪሴ መድቤ ፣ ከፍተኛ ባጀት
ጠብመንጃ ገጀራ ፣ ታንክና የጦር ጀት
ከሆነ ቦታ ጋር ፣ ለጦር ሜዳ ምቹ
በነፃ አድላለሁ ፣ እንዲዋጣላቹ !
።።።
ለሚመጣው ምርጫ ፣ ብትመርጡኝ እኔን
በምስራቅ ፣ በደቡብ ፣ በምእራብ ፣ በሰሜን
ላሉ ህዝቦች ሁሉ ፣ አንዳች ሳላዳላ
ቀስት የፈላ ውሃ ፣ ክላሽና ዱላ
ለተጠቃሚዎች ፣ በነፃ አድላለሁ
ለእያንዳንዱ ቤት ፣
ቤት ቁጥር አንስቼ ፣ ክልል እሰጣለሁ
።።።።
ለሚመጣው ምርጫ
እኔን ብትመርጡኝ ፣ ሔዋኔና አዳሜ
አልጋ ቤት በነፃ
አድላችኃለሁ ፣ ቅዳሜ ቅዳሜ
።።።
ለሚመጣው ምርጫ ፣ እኔን ብትመርጡ
ላመት ባል ላመትባል
ነጭ የጤፍ እንጀራ ፣ ጥብሱ ዶሮ ወጡ
ጥሬ ስጋ ቁርጡ
ጠላው እና ጠጁም
በቴሌቭዥን መስኮት ፣ አይታችሁ አትጎመጁም
ሁሉንም በቤታችሁ ታገኙታላቹ
ምርጫ በሌለበት
ምርጫችሁ እኔ ነኝ ፣ ምረጡኝ ባካቹ
።።።
ሁሉ እንደ ፈቀደው
ሁሉ እንደወደደው
ሚኖርባት ሀገር
መኖር ብትፈልጉ ፣ ምረጡኝ በሞቴ
ፍላጎታቹ ነው  ፣ ምርጫ ምልክቴ “
Filed in: Amharic