>
5:15 pm - Tuesday May 1, 1038

"ሕገመንግሥታዊ" ሐይማኖት በኢትዮጵያ! (አሰፋ ሀይሉ)

“ሕገመንግሥታዊ” ሐይማኖት በኢትዮጵያ!

አሰፋ ሀይሉ

– በኢህአዴግ (ብልፅግና) ‹‹ሕገመንግሥታዊ›› ሥርዓት.. እውን መንግሥትና ሐይማኖት ተለያይተዋል? – መልሱን ከዚህ ፅሑፍ ያግኙ!
 
ጽሑፌ ሁለት ግልጽና አጭር ዒላማዎች ላይ ያተኩራል፡-
1ኛ/ በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ በሃሳብም በተግባርም መንግሥት እና ሐይማኖት እንዳልተለያዩ ማሳየትና፣
 
2ኛ/ የወያኔ-ኢህአዴግ ‹‹ሕገመንግሥት›› ሐይማኖታዊ ዳኝነትን መንግሥታዊ ተቋማዊ ቅርጽ እንደሰጠውና ኢ-ተገቢነቱን ማሳየት፡፡ 
 
አሁን በቀጥታ ወደ ነጥቦቼ፦
________________
1ኛ/ በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ መንግሥትና ሐይማኖት በሃሳብም በተግባርም እንዳልተለያዩ
ህገመንግሥት ተብዬው በአንቀጽ 11 ላይ እንዲህ በማለት ያውጃል (ይደሰኩራል)፦ ‹‹መንግሥት እና ሐይማኖት›› ተለያይተዋል –  መንግሥት የሚያፀድቀው ወይም በመንግሥት መመሪያ የሚተገበር ሐይማኖት የለም፡፡
ከዚህም ያልፍና መንግሥት በሐይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባና፣ ሐይማኖትም በመንግሥት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባ ይገልጻል፡፡
ይህ ግን ፍፁም ኩሸት መሆኑን ብዙም ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገኝ በዚያው በህገመንግሥት ተብዬው ላይ ስላለ እጠቅሰዋለሁ፡፡ ይሄው ሕገመንግሥት ይሄንኑ ባለበት አፉ – ዝቅ ብሎ ቃሉን ይሽረውና በአንቀጽ 78 (በንዑስ አንቀጽ 5) ላይ እንዲህ ይላል፦
‹‹ሐይማኖታዊ ፍርድ ቤቶች በዚህ ህገመንግሥት መሠረት እውቅና አግኝተው ይደራጃሉ››!
እንደዚህ እንደኛ ሀገር ህገመንግሥት ተብዬ በሳቅ ፍርስ የሚያደርግ ህገመንግሥት በዓለም ላይ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም!
ከመንታ ምላሶቹ በአንዱ – መንግሥት ከሐይማኖት ጋር ተለያይቷል፣ መንግሥት በሐይማኖት ጣልቃ አይገባም ይልሃል፡፡ በሌላኛው ምላሱ ደግሞ – የሐይማኖታዊ ፍርድቤት በህገመንግሥቱ እውቅና ተሰጥቶታል፣ በመንግሥት ይደራጃል ይልሃል! ምን ዓይነት ቀልድ ነው ይሄ?
– አላውቀውም! ምናልባት ወያኔያዊ ወይም ኦነጋዊ ወይም ጃራዊ ቀልድ ይሆናል በወቅቱ። አዘለም አንጠለጠለም ግን ያው ኢህአዴጋዊ (ብልፅግናዊ) ቀልድ ሆኖ ቀጥሏል! ዋናው ዓላማዬ መንግሥትና ሐይማኖት እንዳልተፋቱ – እንዲያውም እንደ አዲስ እንደተጋቡ – ለማሳየት ነውና ወሬዬን በዚሁ እቀጨዋለሁ።
_______________
2ኛ/ የወያኔ-ኢህአዴግ ‹‹ሕገመንግሥት›› የሐይማኖታዊ ዳኝነትን መንግሥታዊ ተቋማዊ ቅርጽ እንደሰጠውና ኢ-ተገቢነቱ
ከላይ እንዳቀረብኩት – የወያኔ-ኢህአዴግ ሕገመንግሥት ተብዬው ሐይማኖታዊ ዳኝነትን መንግሥታዊ ቅርጽ ሰጥቶ ለማደራጀት ቃልኪዳን የተገባበት ሰነድ ነው!
ይህን – ከሕገመንግሥት ተብዬው ወጣ ብሎ የሚያስተውል ሰው ታዲያ – የወያኔ-ኢህአዴግ (የብልፅግና) ካድሬዎች (ከአውራሻቸው ከመለስ ጀምሮ) ቀንና ሌሊት ሲያዜሙት የማይጠግቡትን “በንጉሡ ዘመን ሐይማኖት የመንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት በህገመንግሥት ተቀምጦ ነበረ” የሚል ቡራከረዩ ምን አመጣው? – ብሎ መገረሙ አይቀርም፡፡
ይልቅ ማመስገን ካለብን በዚህ አጋጣሚ ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን በአንድ ጉልህ ህገመንግሥታዊ ፋናወጊነቱ ልናመሰግነው ይገባናል። በኮ/ል መንግሥቱ ወታደራዊ መንግሥት የፀደቀው የኢህዲሪ ህገመንግሥት – መንግሥትና ሐይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በሃሳብም የደነገገ፣ በተግባርም የገለጸ ህገመንግሥት ነበረ፡፡
የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት ግን ሐይማኖትና መንግስት ተለያይቷል እያለ፣ መንግሥታዊ የሐይማኖት ዳኝነት ተቋምን ህገመንግሥታዊ ዕውቅና ሰጥቶ አደራጃለሁ ብሎ ተነሳ፡፡
የመለስ ዜናዊ የወያኔ ኢህአዴግ መንግሥት ከንጉሡ መንግሥት የሚለየው – በመንግሥት ዕውቅና ሰጥቶ ባደራጀው የሐይማኖት ተቋም አይነት ብቻ ነው፡፡
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የታወጁት ሁለቱም ህገመንግሥቶች “የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ጳጳስ ንጉሡን ካልቀቡ ንግሥናው አይፀድቅም” የሚል ሐይማኖታዊ አካል በመንግሥት ሥራ የሚገባበትን አሠራር አውጀዋል፡፡ ነገር ግን ሐይማኖትን መንግሥታዊ ተቋም አድርገው  የዳኝነት ሥራ ውስጥ እንዲገባ አላደራጁትም፡፡ ደርግም ይሄንን አላደረገም፡፡ መለስ ዜናዊ (እና ኦነግ) ግን ይሄን ሊያደርግ ተነሳ፡፡
እና “የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት” የሚባል – የመንግሥት የእስልምና ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ምድር ህጋዊም ህገመንግሥታዊም እውቅና አግኝቶ ተቋቋመ፡፡
ለመሆኑ በኢህአዴጓ (ብልፅግናዋ) “ህገአራዊት” – የኢትዮጵያ መንግሥት “ሴኪዩላር” – ማለትም ዓለማዊ – መንግሥት ነው? ማለት እንችላለን? ወይስ ሃይማኖታዊ? መንግሥት ከሐይማኖት በተለየበት ሀገር – እንዴት መንግሥት “ሐይማኖታዊ ፍርድ ቤት” ያቋቁማል?
– መልሱን የሚያውቀው ህገመንግሥቱን የጻፈውና ያስፃፈው የወያኔ-ኢህአዴጉ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ብቻ ይመስለኛል! እሱ ሞቷል። ስለዚህ አብሮት ሕገመንግሥቱን የፃፈው የአብይ አህመድ አማካሪ ኦቦ ሌንጮ ለታ ቢመልስልን የተሻለ ይሆናል።
መለስ ዜናዊ – በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ከዓለማዊው እና ለሁሉም በገለልተኝነት ከሚሠራው መደበኛ የዳኝነት አካል በደባልነት – መንግሥታዊ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ማቋቋሙ ብቻ እኮ አይደለም የሚገርመው! የሚገርመው ብዙ ነው፡፡
በበኩሌ እጅግ ከሚገርሙኝ ነገሮች መካከል አንዱ – ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ ላይ ከሚሰበሰብ ታክስ ላይ እየተመዠረጠ – በየዓመቱ ለሸሪዓ ፍርድ ቤት የሚመደበው በሚሊዮን ብር የሚቆጠር መንግሥታዊ ባጀት ነው!
ሌላ ሌላውን ትቼ – በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣው የፌዴራል መንግሥቱ ዓመታዊ ባጀት ላይ የ2 ተከታታይ ዓመት የባጀት ምደባዎችን በምሳሌነት ልጥቀስ፡፡
በእነዚህ ማንም ሰው አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም መደብር ሄዶ ገዝቶ ሊያመሳክረው የሚችላቸው የመንግሥት ባጀት ታትሞ ከወጣባቸው የነጋሪት አዋጆች መካከል – የምርጫውን ግርግር ተከትሎ በነበረው የ1999 ዓመተ ምኅረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ዓመታዊ ባጀት ውስጥ – ለፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት የተመደበው ባጀት ብር 1,569,300 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ስድሳ ዘጠኝ ሺህ ሶስት መቶ ብር) ነበረ፡፡
በተከታዩ ዓመት በ2000 ዓመተ ምህረት ላይ ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ለሐይማኖታዊው የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት የመደበው ዓመታዊ በጀት በእጥፍ ገደማ አድጎ ብር 2,756,100 (ሁለት ሚሊየን ሰባት መቶ ሃምሳ ስድስት ሺህ አንድ መቶ ብር) ያሳያል፡፡
አሁን ስንት እንደደረሰ ደንታ የሰጠው ዜጋ ብርሃንና ሰላም ወረድ ብሎ ከነጋሪት ጋዜጣ ላይ ይመልከተው። ሌላ ሌላውን አልገባበትም፡፡  ጉዳዩን ለሚያጠና ተመራማሪ እንዲጨነቅበት እተወዋለሁ!
ይሄ ማለት ምን ማለት ነው?
ይሄ ማለት በመለስ ዜናዊ (በኢህአዴግ-ብልፅግናዋ) ኢትዮጵያ ከቀኃሥ ዘመነ መንግሥት ወዲህ የተደረገው ለውጥ – ካርታውን በውዞ – አንዱን ሐይማኖት በሌላው መተካት ብቻ አይደለም።  ለአንድ ሐይማኖታዊ ተቋም የህገመንግሥት ዕውቅና መስጠት ብቻ አይደለም። በመንግሥት ማደራጀት ብቻም አይደለም።  በመንግሥት ባጀት እየተመደበ የእስልምና ሐይማኖት በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እንዲንቀሳቀስ ተደርገዋል ነው!
እና በመለስ ዜናዊዋ የኢህአዴጓ ኢትዮጵያ – መንግሥትና ሐይማኖት ተለያይተዋል? ሌሎችስ ሐይማኖቶች በዳኝነት ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብተው ሃይማኖታዊ የዳኝነት አካል እንዲያቋቁሙ ይፈቀድላቸዋል?
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን የሚያቋቁመው በምን ምክንያት ነው? ኢትዮጵያ እንደ ሣዑዲ አረቢያ እስልምና የመንግሥት ሐይማኖት የተደረገባት አረባዊት ሀገር ነች ወይ? የኦፔክ (የነዳጅ ላኪ ሀገራትስ አባል ነን ወይ?)..???!! ከዚህ በላይ አልሄድበትም፡፡ እዚሁ ላይ ተቆጥቤ ምሳሌዬን በሰነዘርኳቸው ጥያቄዎቼ እቋጨዋለሁ፡፡
__________________
እንግዲህ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡ 2ቱን ነጥቦቼን አትርሱብኝ አደራ ብዬ አበቃለሁ፡-
1) በመለስ ዜናዊዋ – በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ – “በደም መስዋዕትነት የተገኘ ህገመንግሥት!” እየተባለ በእነ አብይ አህመድ አሊ በሚፎከርባት የብልፅግናዋ ኢትዮጵያ – ሥርዓት ውስጥ – መንግሥትና ሐይማኖት ፈጽሞ አልተለያዩም፡፡
2) እንዲያውም ‹‹ሕገመንግሥት›› ተብዬው ወደ አንድ ወገን የተንሸዋረረ ሐይማኖታዊ የዳኝነት ሥልጣንን መንግሥታዊ ተቋማዊ ቅርጽ ሰጥቶታል፡፡
እውነቱ ይኸው ነው፡፡
አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ይታረቀን!
እናት ኢትዮጵያ በአይበገሬ ልጆቿ ፀንታ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic