>

እሳት...! እሳት. ..! እሳትና...አንበጣ …  !!! (ዘመድኩን በቀለ)

እሳት…! እሳት. ..! እሳትና…አንበጣ …  !!!

ዘመድኩን በቀለ

… ልብ ብላችሁ ከሆነ ካለፈው ወር መጀመሪያ ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ መነሻው የማይታወቅ የእሳት አደጋ እየተከሰተ ነው። አደጋው ደግሞ እንዲህ በቀላሉ አደጋ ተብሎም የሚታለፍ ነገር አይደለም። የተኪቫህን ዘገባ ስከታተል ቀበሌና ሙሉ መንደር ከተማም ጭምር የሚያወድም እሳት መነሣቱን ነው እያየን ያለነው።
… ለቁጥጥር የማያመች እሳት፣ እንደ ድሮው በርብርብ የማይጠፋ እሳት። ከአንድ ሱቅ የሚነሳ እሳት ከተማ ሙሉ ሲያወድምም እያየን ነው። በተለይ ደቡብ ክልል ብዙዎች በአንድ ጀንበር ከድኅነት ወለል በታች የሚቀብራቸው ሆኗል የእሳት አደጋው?
… በሃላባ ዞን ዌራ ወረዳ ላይኛ በደኔ ቀበሌ በጦሮንቦራ ንዑስ በደረሰ የእሳት አደጋ 11 መኖሪያ ቤቶች ሲወድሙ በሰውና በእንስሳት ላይ ግን ምንም ጉዳት አለመድረሱ ይታወሳል። ይሄ ደቡብ ነው።
… በጅጅጋ ከተማም በቀበሌ 02 በልዩ ስሙ ድብኡራሾ ሱቅ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ በተነሣ የእሳት አደጋ 7 የንግድ ሱቆች ሲወድሙ ግምታቸው 1.2 ሚልዮን ብር የሚጠጋ ንብረት ወድሟል። ይሄ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ነው።
… ደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ መነሃሪያ ሼድ ላይ የእሳት አደጋ ተከስቶ በአካባቢው የነበሩ ሱቆች መውደማቸው ተነግሯል። ይሄ ደግሞ ሰሜን ኢትዮጵያ ነው።
… ከዚህ በፊት 4 ጊዜ ተመሳሳይ የእሳት አደጋ አስተናግዳ የነበረችው ወላይታም ባለፈው ወር ነበር በወላይታ ሶዶ ከተማ “መርካቶ ገበያ” በሚባለው ስፍራ ላይ የተነሣው እሳት በሥፍራው የነበሩ ሱቆችን ሙሉ በሙሉ በማውደሙ ዜጎች በአንድ ጀምበር ባዶ እጃቸውን አስቀርቷቸዋል። ይሄኛው አደጋ ደግሞ በቢልዮን የሚገመት ንብረት ያወደመ ነው። ይሄኛው ደግሞ ደቡብ ኢትዮጵያ ነው።
… በዓለምማያ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ ህንፃ በተነሣ ንበረት አውድሞ በቁጥጥር ስር ውሏል። ይሄኛው ምሥራቅ ኢትዮጵያ ነው።
… ደቡብ ወሎ መካነ ሰላም ከተማ ከሌሊቱ 8:ሰዓት ድንገት ተከሰተ በተባለ የእሳት አደጋ ከአምስት በላይ ሱቆች እና የተለያዩ ማሽኖች መውደሙ ተነግሯል። ይሄም ሰሜን ኢትዮጵያ ነው።
… ባህርዳር ከተማ በተለምዶ ጉዶ ባህር ተብሎ በሚጠራው ሰፈር የተነሣ እሳት ዜጎችን በአንድ ጀንበር ባዶ እጅ አስቀርቶ የስንዴና የዘይት ተረጂ ወደ ማድረግ ነው የደረሰው። ይሄም ሰሜን ኢትዮጵያ ነው።
… በምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ “ ሾላ ቀበሌ” ታህሳስ 19/2013 ዓም የዜጎች ንብረት ወድሟል። ይሄም ደቡብ ኢትዮጵያ ነው።
… በሃድያ ዞን ምሻ ወረዳ በ3 ቀበሌዎች ማለትም ኤራ ጌሜዶ፣ ኩናፋ እና ጉና ሜጎቾ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ23 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሞ ከ4መቶ 36 በላይ የቤተሰብ አባላት ተፈናቅለው ሜዳ ላይ መፍሰሳቸው ተነግሯል። ይሄም ደቡብ ኢትዮጵያ ነው።
… በምዕራብ ሰሮ ወረዳ ታህሳስ 18/2013 ዓም መነሻው የመብራት ኮንታክት ነው በተባለ የእሳት አደጋ በጃቾ ከተማ በደረሰ አደጋ ከ250 ሺ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተነግሯል። ይሄም ደቡብ ኢትዮጵያ ነው።
… ሰሜን፣ ምስራቅና ደቡብ እሳት በእሳት ሆኗል። በተለይ ደቡብ ኢትዮጵያ እሳት በእሳት መሆኑን እያየን ነው። እሳት፣ እሳት፣ እሳት።
… ከእሳት ወሬ ስንመለስ በኦሮሚያ ክልል 6 ዞኖች ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የአንበጣ መንጋ መከሰቱ ተነግሯል። የአንበጣ መንጋው የተከሰተው በክልሉ ሁለቱ የባሌ ዞኖች ፣ ምስራቅ ሐረርጌ ፣ አርሲ፣ ጉጂና ቦረና ዞኖች ውስጥ ነው ተብሏል።
… የክልሉ መንግሥት የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር ክልሉ ካለው ዝግጅት አንፃር ከአቅም በላይ እንደማይሆን ገልጿል። እንደ ሰሜኑ አያስቸግረንም ማለቱ።  ያድርግላቸወ አሜን
             … ወይ እሳት …
እሳት በእሳት … ደቡብ፣ ምሥቅና ሰሜን…  እሳት በእሳት … እግዚአብሔር መነሻው ከማይታወቅ ፥ አልያም ታውቆ እንዳይታወቅ ከሚደረግ የሴራ እሳት ይሰውረን አሜን  !!
Filed in: Amharic