>
5:14 pm - Monday April 20, 6415

መካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ ዘመን ሌላ ጥፋት‼ (በነጋሽ መሐመድ DW)

መካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ ዘመን ሌላ ጥፋት‼

በነጋሽ መሐመድ DW

*…..የዳዊት አስተምሕሮ፣ የክርስቶስ ስብከት፣ የመሐመድ ስገደት ለሰዉ ልጅ ሠላም፣ለፍትሕ ርትዕት ፅናት ነበር።አረብ አይሁድ ግን እዚያ ምድር ላይ  ዛሬም ይተላለቅበታል። አዉሮጳ፣አሜሪካ በየዘመኑ ያፈራዉን ጦር  መሳሪያ ይፈትሽበታል። ዘንድሮም እንደ 1948ቱ፣ እንደ 1956ቱ፣ እንደ 1967ቱ፣እንደ 1973ቱ እንደ 2007ቱ፣ እንደ 2014ቱ ሕፃናት፣እናቶች፣ወጣቶች፣ አባቶች ይገደሉበታል።
 
የእስራኤል ምርጥ ጦር ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ጋዛ ሰርጥ ላይ ካየርና ከምድር በሚያወርደዉ ሚሳዬል፣ ቦምብና አረር ወደ 200 ፍልስጤሞችን ገድሏል።የጋዛ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት የከተገደሉት 58ቱ ክፉ ደጉን የማያዉቁ ልጆች፣ 34ቱ ሴቶች ናቸዉ።
ጋዛ ከ1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ እንደኖረችበት እየተገነባች ትጋያለች።አሽኬሎን፣ አሽሎድ፣ስዶርት እየዘመኑ ይቃጠላሉ።እየሩሳሌም፣ ቴልአቪቭ፣ ኢያርኮ፣ ቤተ ልሔም በእሳት ጢስ-ጠለስ ይታጠናሉ፣ በጫጫታ፣ ጩኸት ዋይታ ይተራመሳሉ።የዳዊት አስተምሕሮ፣ የክርስቶስ ስብከት፣ የመሐመድ ስገደት ለሰዉ ልጅ ሠላም፣ለፍትሕ ርትዕት ፅናት ነበር።አረብ አይሁድ ግን እዚያ ምድር ላይ  ዛሬም ይተላለቅበታል።አዉሮጳ፣አሜሪካ በየዘመኑ ያፈራዉን ጦር  መሳሪያ ይፈትሽበታል። ዘንድሮም እንደ 1948ቱ፣ እንደ 1956ቱ፣ እንደ 1967ቱ፣እንደ 1973ቱ እንደ 2007ቱ፣ እንደ 2014ቱ ሕፃናት፣እናቶች፣ወጣቶች፣ አባቶች ይገደሉበታል።ሌላ ዘመን ሌላ ጥፋት።መከከለኛዉ ምሥራቅ። የሰሞኑ ጥፋት መነሻ፣ ምክንያቱ ማጣቃሻ፣ የዓለም ሆይ ሆይታ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
 የመብት ተሟጋቾች፣ የፍትሕ አቀንቃኞች በመላዉ ዓለም አደባባዮች ይጮሐሉ።የዓለም ታላላቅ ዲፕሎማቶች ይጠይቃሉ።ሠላም አዉርዱ እያሉ።ከሕዳር፣ 1947 ጀምሮ ከትርይግቭ ሊ እስከ ባን ጊ ሙን የተፈራረቁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፍት ብለዉታል።አንቶኒ ጉተሬሽም  ትናት በዘመኑ ቋንቋ አሉት።«ዉጊያ አቁሙ»
«ዉጊያዉ መቆም አለበት።ባስቸኳይ መቆም አለበት።ካንድ ወገን የሚወነጨፉት ሮኬቶችና ሞርታሮች፣ ከሌላዉን ወገን የሚደረገዉ የአዉሮፕላን ድብደባ መቆም አለበት።ሁሉም ወገኖች ይሕን ጥሪ እንዲያከብሩ እጠይቃለሁ።አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሁሉም ወገኖች ጋር ይጥራል።»
ቀሳዉስት፣ መሻኢኮች፣ ራቢ፣ ዳይለላማዎች ለዚያ ምድር ሠላም ፀልየለዋል።ጦረኞችን ተማፅነዋል።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ደገሙት።
  «በቅድሱ ምድር የሚሆነዉን በከፍተኛ ስጋት እየተከታተልኩ ነዉ።ባለፉት ጥቂት ቀናት በጋዛ ሰርጥና በእስራኤል መካከል የሚካሔደዉ የጦር መሳሪያ ዉጊያ ከፍተኛ ሞትና ጥፋት አስከትሏል።በርካታ ሰዎች ቆስለዋል።ብዙ ንፁሐን ሰዎች ተገድለዋል።ከሟቾቹ መሐል ልጆችም አሉበት።ይሕ በጣም አሳዛኝ ነዉ።ተቀባይነት የለዉም። የነሱ (የልጆቹ) መገደል ሰዎች የወደፊቱን ማፍረስ እንጂ መገንባት እንደማይፈልጉ የሚያመለክት ነዉ።»
የዲፕሎማት፣ መንፈሳዊ መሪዎቹ ጥሪ፣ተማፅኖ ከፖለቲከኛ-የጦር መሪዎቹ ጆሮ እየተላተመ ተመለሰ እንጂ እስካሁን  የፈየደዉ  የለም።ከነብስ ወከፍ ጠመንጃ እስከ ኑክሌር ቦምብ ዘመናይ ጦር መሳሪያ መታጠቁ የሚታመነዉ የእስራኤል ምርጥ ጦር ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ጋዛ ሰርጥ ላይ ካየርና ከምድር በሚያወርደዉ ሚሳዬል፣ ቦምብና አረር ወደ 200 ፍልስጤሞችን ገድሏል።የጋዛ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት የከተገደሉት 58ቱ ክፉ ደጉን የማያዉቁ ልጆች፣ 34ቱ ሴቶች ናቸዉ።
ጓዳ ሰራሽ ሮኬት ታጥቆ ጋዛ ሰርጥ የሚሽሎኮለከዉ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ድርጅት ሐማስ ወደ እስራኤል ባወነጨፈዉ ሮኬት ደግሞ 10 እስራኤሎች ተገድለዋል።ሁለቱ ልጆች ነበሩ።በንብረት ላይ የደረሰዉ ጉዳት መጠን በዉል አይታወቅም።ይሁንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ የእስራኤል የጦር ጄቶች ጋዛ ዉስጥ የሚገኙ ሕንጻዎችን፣ የጋዜጠኞችን ፅሕፈት ቤቶችን፣ የሐኪሞችን መስሪያ ቤቶችን፣ የስደተኞችን መጠለያ ጣቢያ ሳይቀር እያወደሙ ነው።
«ጋዛ ዉስጥ በስደተኞች መጠለ ጣቢያ ላይ በተፈፀመ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አስር ሰዎች መገደላቸዉ አስደንግጦኛል።ሰብአዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ጥበቃ ሊደረግላቸዉ ይገባል።ጋዜጠኞች ከፍራቻና ወከባ ነፃ ሆነዉ እንዲሰሩ ሊፈቀድላቸዉ ይገባል።ጋዛ ዉስጥ የሚገኙ የመገናኛ ዘዴዎች ፅሕፈት ቤቶች በደብደባቸዉ በጣም አሳሳቢ ነዉ።»
ግድያ፣ ጥፋት፣ ዉድመቱ ለብዙዎች በርግጥ አሳዛኝ፣ አስጊ፣አሳሳቢ፣ አስጨናቂም ነዉ።በብዙ ዓለም የሚገኙ ሰላም ወዳዶችና የመብት ተሟጋቾች በየአደባባዩ የሚጮኽቱም ለዚሕ ነዉ።ሊያቆመዉ የሚችለዉ ግን የአል ጀዚራዉ የፖለቲካ ተንታኝ መርዋን ቢሽራ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳለዉ አንድም የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት፣ ሁለትም ብቸኛዋ የምድራችን ኃያል ኃይል፣ የእስራኤል ጥብቅ ወዳጅ  ብቻ ናት።ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ።የአሜሪካ ባለስልጣናት የጦር መሳሪያቸዉ አቅም በቅጡ እስኪታወቅ፣ የጥብቅ ወዳጃቸዉ የብቀላ ጥማት እስኪረካ ወይም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ደካማ ሐገራትን አዉግዘዉ እስኪያበቁ፣ እነ ኢራንን እስኪያስፈራሩ ብቻ ምክንያቱን በግልፅ ባልተናገሩበት ምክንያት እስከ ዛሬ ሐማስን ከማዉገዝ ባለፍ እልቂቱን ለማስቆም ያደረጉት የለም።ቀጥሏል።
ኢትዮጵያዊዉ የጆኦፖለቲክስ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአንድ መፅሐፋቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ስለመካከለኛዉ ምሥራቅ የምትከተለዉን መርሕ ከኮምፒዉተር ባለሙያዉ ሴራ ጋር ያመሳስሉታል።
የኮምፒዉተር አዋቂዉ ቫይረስ የሚባል ነገር በየኮፒዉተሩ ይለቅና የቫይረስ መከላከያ የሚባል ነገር ደግሞ ለየባለኮፒዉተሩ ይሸጣል።ዩናይትድ ስቴትስም እስራኤልን እስካፍንጫዋ እያስታጠቀች፣ በየአለም አቀፉ መድረክ ለእስራኤል እየተሟገተች ከፍልስጤሞች ጋር የማስታርቅ እኔና እኔ ብቻ ነኝ ትላለች-«የማይቻለዉን የሚቻል ታደርግ ይመስል» እንደ ፕሮፌሰሩ።
ለረጅም ዘመናት ምናልባትም ለ2000 ዓመታት «ፍልስጤም» ይባል የነበረዉን ያን ጥንታዊ ግዛት ለሁለት እንዲገመስ ከፍተኛ ግፊት ያደረገችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።ሕዳር፣ 1947 የተሰየመዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ ግፊት፣ ጫናና በአባል ሐገራት ላይ ባደረጉት ማስፈራራት ጭምር ያ ግዛት ለሁለት ተገምሶ ባንደኛዉ ገሚስ የሁዲዎች በሌላቸዉ አጋማሽ አረቦች የየራሳቸዉን መንግሥት እንዲመሰርቱ ወሰነ።
 «የፍልስጤምን መገመስ የሚከታተለዉ ኮሚቴ የዉሳኔ ሐሳብ፣ በ33 የድጋፍ፣ በ13 ተቃዉሞና በአስር ድምፀ ተዓቅቦ ፀድቋል።»
ሕዳር 29፣ 1947 ኒዮርክ፦
በዉሳኔዉ መሰረት የሁዲ፣የክርስቲያንና የሙስሊም  ቅዱስቲቱ ከተማ  እየሩሳሌም በዓለም አቀፍ ተቋማት መተዳደር ነበረባት።በ1967ቱ ጦርነት እስራኤል ለአረቦች የተከለለዉን ግዛት  በሐይል ስትይዝ፣ ወይም የዓለም ዉሳኔን የእስራኤል መሪዎች ሲጥሱት እንደ ዶናልድ ትራም የመሳሰሉ የኃይለኞቹ ኃይለኛ ምዕራብ እየሩሳሌምን ጭምር ለእስራኤል ሲመርቁ፣ ከትራምፕ በፊትና በኋላ የነበሩት ብጤዎቻቸዉ የማይቻለዉን የሚቻል ለማስመሰል እንደባተሉ እነሆ ዛሬ ላይ ደረስን።
በአዲሱ ግጭትና ጥፋት ለመነጋገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈዉ አርብ ሊያደርገዉ የነበረዉን ስብሰባ ዩናይትድ ስቴትስ አግዳለች።ምክር ቤቱ ትናንት ባደረገዉ ስብሰባም ለወትሮዉ ጥፋተኛ የሚሉትን መንግሥት የሚያወግዙት አሜሪካዊቷ ዲፕሎማት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ተፋላሚዎች «ተኩስ የሚያቆሙ ከሆነ—-»  ብለዉ አለፉት።
 «ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም የሚሹ ከሆነ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፏንና መልካም ርዳታዋን ለመስጠት ዝግጁ መሆንዋን ግልፅ አድርገናል።ምክንያቱም እስራኤሎችና ፍልስጤሞች በደሕና በሠላም የመኖር እኩል መብት አላቸዉ ብለን እናምናለን።ያሁኑ ግጭት ሁለቱንም ማሕበረሰብ ይሕን መሰረታዊ መብት ነፍጓል።»
ተኩስ ካላቆሙ ይቀጥሉ ማለት ይሆ? የእስራኤል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አቪቭ ኮሽቪ በቀደም እንዳሉት ጦራቸዉ የሐማስዋን ጋዛ አይቀጡ መቅጣቱን ይቀጥላል።«ሐማስ የኛን የአፀፋ ጥንካሬ አሳንሶ ገምቶታል።እና ጋዛ ሰርጥ ከፍተኛ ዉድመት ይወርድባታል። በኔ ግምት እና ካካባቢዉ በምናገኘዉ መረጃ መሰረት ጋዛ የሚደርስባት ድንበዳ እስካሁን አይታዉ የማታዉቀዉ ነዉ።»
በርግጥም ጋዛና ሕዝቧ ከ2014 ወዲሕ አይተዉት በማያዉቁት እቶን እየነፈሩ ነዉ።ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ያን መከረኛ ሕዝብ ለሚፈጀዉ ግጭትና ጥፋት መነሻዉ እንደየተመልካቹ ለየቅል ተቃራኒም ነዉ።የእስራኤል ባለስልጣናት እንደሚሉት ጠቡ የተጫረዉ «አሸባሪ» የሚሉት ሐማስ በእስራኤል ግዛቶች ላይ ሮኬቶች በመተኮሱ ነዉ።
ለአረቦች ደግሞ እስራኤል ሼክ ጃራሕ በተባለዉ የእየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ ፍልስጤሞችን በኃይል ነቅሎ አካባቢዉን ለየሁዲዎች ለመስጠት መወሰኗ፣ የእስራኤል ፀጥታ አስከባሪዎች አልአቅሳ መስጊድና አካባቢዉ ፍልስጤሞችን በመደብደብ-ማቁሰላቸዉ ምክንያት ነዉ።እንደ ዶሮና እንቁላሉ ቀዳሚ ተከታይ።
ከ1948 ጀመሮ የተፈራረቁ ዲፕሎማት፣ ተንታኝ፣ አዋቂዎች እንደሚሉት በዚያ ምድር ሰላም እንዲወርድ የሚፈልግ ካለ ሠላም የሚገኘዉ በድርድር ብቻ ነዉ።አንቶኒዮ ጉተሬሽም ለዘመናት የተባለዉን እንደገና አሉት።
«የቅድ ስ ስፍራዎቹ  አስተዳደር ገቢር መሆንና መከበር አለበት።ይሕንን አዉዳሚ የግጭት ዑደት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስወግድና ለፍልስጤሞችምና ለእስራኤሎች የወደፊት ሰላም የሚጠቅመዉ በድርድር ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ነዉ።»
በ1960ዎቹ ማብቂያ የያኔዉ የግብፅ ፕሬዝደንት ገማል አብድናስር ከሶቭየት ሕብረቱ ዋና ፀሐፊ ሊዮንድ ብሬዥኔየቭ ጋር «ሲወያዩ» ይላል ዕዉቁ ግብፃዊ ጋዜጠኛ መሐመድ ሐይከል ባንድ መፅሐፉ፣ «ጓድ ብሬዥኔቭ የኡታንትን (የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ነበሩ) የሰላም ሐሳብ ልቀበል ነዉ» አሉ ናስር።የግድምድሞሽ ንግግር ያዘዉትራሉ የሚባሉት ብሬዥኔቭ ቀበል አደረጉና «ኡታንት ሰላሙን የሚያስከብረት አንድም ታንክ የለዉ—» ብለዉ መለሱ አሉ።ሠላም የሚወርደዉ «ከጠመንጃ አፈሙዝ ነዉ» እንደማለት ይሆን? Via፦
Filed in: Amharic