በምዕራብ ወለጋ ሆሮ ጉድሩ ዞን ቦቶሮ ቀበሌ በተከፈተ ጥቃት በርካታ ንፁሃን አማራዎች መሞታቸው ተገለፀ
አሻራ ሚዲያ 11/09/13/ዓ.ም ባህር ዳር
በጥቃቱ ህጻናትን ጨምሮ የሌሎች ንፁኃን ዜጎች ሕይወት ማለፉንም በአካባቢው የሚኖሩ የአይን እማኞች የተናገሩ ሲሆን ማንነትን መሰረት አድርጎ በተደጋጋሚ የሚደርሰው ግድያ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ከሃብት ንብረታቸው ለማፈናቀል ያለመ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
እስካሁን በአካባቢው ከሰው ሕይወት መጥፋት ባሻገር በተደራጀ ሁኔታ የዘረፋ ወንጀል ስለ መቀጠሉም ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ የጥቃቱ ቀጣይነት መኖር ከታጣቂዎቹ ጎን የተሰለፈ ደጋፊ አካል ስለ መኖሩም አመላካች ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ በመንግስት በኩል አካባቢውን ለማረጋጋት የፀጥታ ሃይል ለማሰማራት የተሞከረ ቢሆንም በአንዳንድ የወረዳው ባለስጣኖች ምክንያት እርምጃው ተጠናክሮ እንዳይወሰድ ሆኗልም ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ አክለውም በወረዳው የሚገኙ የጤና ተቋማት በጥቃቱ ለተጎዱ ቁስለኞች ጭምር ተገቢውን እርዳታ እንደማያደርጉላቸውም በመግለጽ በዚህም በወረዳው በሚገኙ ሌሎች ተቋማት ሳይቀር መሰል በደሎች እየደረሰባቸው እንደሚገኙም ከነዋሪዎቹ አንደበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ ከሚደርሱት አስከፊ ጥቃቶች ለመሸሽ ብንሞክርም በመንገዶች መዘጋት ምክንያት የጥቃቱ ሰለባ እንድንሆን ተፈርዶብናልም ብለዋል፡፡አሻራ ሚዲያም በአካባቢው ለሚገኙ የመንግስት አካለት በመደወል ስለሁኔታው ጥያቄ ያነሳ ቢሆንም ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡