>

በኢትዮጵያ ሳምንት ሥለ አገር አንድነት እንትጋ!!  (ደጀኔ አሳምነው)

በኢትዮጵያ ሳምንት ሥለ አገር አንድነት እንትጋ!! 

ደጀኔ አሳምነው

 በሰላም ግዜ ተባባሪ ፣ በዘመቻ ግዜ ጀብዶኛ ፣ በጦርነት ግዜ መንፈሰ ቆራጥ የሚያደርግ፣ የወንድነት ሀሞት የሚያፈላ፣ የአርበኝነት ወኔን የሚያገነፍል ፣ የድፍረት ግመት የማያሞኘው አንድነት ነው።
ጎበዝን የሚያስሞካሽ፣ የሚያጋንን የሚያስፋፋ..እከሌ እንደ  ጥይት ተወርዋሪ እንደ አንበሳ ግርማዊ አንደ ነበር ግልፍተኛ ቁጡ ሀይለኛ፣ የማይደፈር ወንድ ነው የሚያሰኘው..ለሴት አሞት ለወንድ ድፍረት የሚሰጠው አንድነት ነው።
አንድነት ነፃነት ነው። ነፃነት አንድነት ነው። አንድነት አገር! አገር አንድነት ነው።አንድነታችን አትዮጵያዊነታችን ነው። ኢትዮጵያዊነታችን አንድታችን ነው። አንድነት ባይኖረን ኖርሮ አድዋ ላይ የሆነው ባልሆነ ነበር! አድዋ ላይ ያ ባይሆን ኖሮ ዛሬ ወግ ባህልና ቋንቋችን ብለን የምንጋደለበት ማንነት ባለ ነበረን። አዎ አትዮጵያ የምትባል አገርም ፣ ኢትዮጵያዊ የሚባል ህዝብም ባልነበር!።
አንድነት መንግሥት ነው።  መንግሥት አንድነት ነው። ሥልጣኔ አንድነት ፣ አንድነት ሥልጣኔ ነው። ሕይወት አንድነት፣ አንድነት ሕይወት ነው። ኃይል አንድነት አንድነት ኃይል ነው። ሕዝብ ዛሃ ብዙ ድር ነው። የድር ውሉ መቆጠሪያው ደግሞ አንድነት ነው። ስለዚህ የሀገር ማተቧ የድሩ ዉል መቋጠሪያ ከተበጠሰ፣ የሕዝብም እምነቱ ከጎደለ፣ ሀገሩም ህዝቡ አወዳደቁ አያምርም።
ህወሀት እንደ ሜዳ የፏለለበት ግራካሶ ሲያንሸራትተው የደለቀበት አምባላጌ ሲያዳልጠው አንደ ማለዳ ጠሀይ የሚሞቀው ቆላ ተምቤን ሲያቃጥለው እንደ ሙሴ በከዛራው የሚከፍለው ተከዜ ሲተፋው በእድሚያችን አይተናል።
የትግራይ ህዝብ ላይም የደረሰውን ሰምተናል። በመተከልስ የሚሆነውን የምናውቀው ነው። በአማራና በኦሮሞ፣ በሲዳማና በወላይታ ባጠቃላይ በህዝቦች  መሀል መጠራጠርና መፋጠጥ እርስበእርስ መገዳደል እና መሳደድ የመጣው በአንድነት አጦት ነው። ለዚህ ነው አንድነት ሕይወት ነው አንድነት አገር ነው የሚባል።
አገር አንድነት ፣ አንድነት አገር ነው። አለዚያማ አገር አገር አይሆንም፤ ውሃው ይመራል፣ ያንገፈግፋል፣ አየሩ ይጎመዝዛል፣ መሬቱ እንደ ረሞጫ ያቃጥላል የሣር የቅጠሉ ሽታ ይመርዛል ሸጥ ሸለቆው ይከብዳል፣ ያስጠላል ተራራ ሸንተረሩ ያንሸራትታል ያዳልጣል ነዋሪውም አንደ አይጥና ድመት እንደተኩላና ፍየል፣ ተፋጦ ዕድሜውን በሙሉ ድንግጥ ድንግጥ ፍርግግ ፍርግግ ንቅል ንቅል ትክል ትክል ሲል ነጠላ ትከሻ ሆኖ የተጠራበትን ምድራዊ ኑሮ በህልም አለምና በገደል ማሚቶ ዘዬ ይጨርሳል።
ይህ እንዳይሆን ታዲያ የስልጣኔ ኩርንችት፣ የኑሮ አሸክላ፣ የመወያየት እንቅፋት፣ የፍቅር፣ ሻህላ እየሆኑ በጥራዝ ነጠቅነትና በጎሰኝነት በተመረዘው ወጣት መካከል እንቁራሪት በሆዱ እንደቋጠረ እባብ ተቋጥረው አየተርመሰመሱ በወገንና በጐሳ የሚያባሉንን አንዳንድ አጉራ ዘለል አጥንተ ብልዝ
እንክርዳድና መጮች ነቃቅለን በመጣልና በየልባችን የጠቀረሸውን የአገር እርሾ ለቅልቀን በማፍሰስ የሕይወት አክሊል የሚሆነውን አንድነትን መርጠን በመቀዳጀትና በሱ ሥር በመራመድ አያት ቅድመ አያት ቅም አያቶቻን የጀግንነት ሥራቸውን አሳይተው ቅርስ አሳልፈው የረገፉባትን የአካል ክፋያችን አለኝታችን መሸሻችን መሸሸጊያችን የህነችውን የጋራ አገራችን ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት አደጋ እንታደጋት
Filed in: Amharic