>
5:33 pm - Friday December 5, 7253

ይሆናል ያሉት እንዳይሆን ሆነ....!!! (ታገል አልማው)

ይሆናል ያሉት እንዳይሆን ሆነ….!!!

ታገል አልማው

ኢትዮጵያ አለቀላት ህዝቦቿ ተበተኑ ሲባሉ የበለጠ ከፍ ይላሉ። የመኖሯ እጣ ፈንታ ትልቅ ነን አድገናል በሚሉት ይወሰናል ሲሏት እጣ ፈንታዋን የሚበጃትን በራሷ ወስና ታሳያለች።
ኢትዮጵያን በትነን እንበለፀጋለን ከፍ እንላለን የሚሉትን ከኢትዮጵያዊነት በታች  መሆናቸውን አሳይተን እናውቃለን። እንቀብራቸዋለን ያሉትንና የሚሉትን የምናሳፍር ጀግኖች በመሆናችን ደግሞ ልንኮራ ይገባል። ሀገራችንን ብዙዎች  የሚመኟት ግን ደግሞ መቸም የማያገኟት ሀገር ናት ።
ኢትዮጵያ ይች ናት ፡፡ ስለ ከፍታዋ እንጂ ስለውድቀቷ የሚሰሩትን የማትቀበል ስለ አንድነቷ እንጂ ልዩነትን የሚተነትኑትን የማትሰማ ኩራትና ክብር የሆነች ምድር ናት ኢትዮጵያ። ኢትዮጵያዊነት ምርጢርነት ልበሙሉነት እስከ ማንነት መኖርም መሞትም ነው።
እንደ እኛ ትውልድ ደግሞ በዚህ የታደለ የለም። ስራቸው ሁሉ አስተማሪ ተግባራቸው ሁሉ አሸናፊ የሆኑ ድንቅ አያቶች ያሉን ምርጦች ነን። ይህን እድል ያልታደሉ ያላገኙ ብዙዎች ናቸው። ይህን ስናስብ ሁሌም ትልቅነት ሊሰማን ይገባል።
ይህ ታሪካችን በተቃራኒ እንዲሆን የሚፈልጉ የውስጥም የውጭም ሃይሎች ግን በየ ጊዜው መፈጠራቸውን እያየን ነው። ልክ እንደ አሸባሪው ህወሀት እና ህወሀት ወለድ ተላላኪዎች አይነት ማለት ነው።
ሀገሩን ህዝቡንና ማንነቱን ለባዕዳን አሳልፎ የሰጠ ምግባር ብሎ ያልፈጠረበት ለከት የለሽ ሆዳምነት በትልቁ የተጠናወተው ህወሀት ክፋትና ጥፋት ሁለቱንም ነው። መኖር የሚፈልገው እድሜዬ የሚረዝመው ብሎ የሚያስበው ግጭት ውስጥ ባለች ሀገር ነው። ይህ አሁን ያመጣው ወይንም ጊዜ የቀየረው ባህሪው አይደለም። ተወልዶ ያደገበት ተፈጥሮው ነው። ይህን ተፈጥሮውን ሂደት አልቀየረውም።
ተፈጥሮን ተመክሮ አያድነውም እንዲሉ ባለበት እንደውም በቀጣይነት እያነሰ ሄደ። እያነሰ የሚለው ከሰዋዊነት እየወጣ የሄደ የሚለውን ለመግለፅ ነው። በሀገሪቱ ሞት መፈናቀል ግጭት ሲሆን  ፅዋውን ከፍ ያደርጋል። ከበሮ ይደልቃል።
ይህ ክፉነት ብቻ ሳይሆን ሰይጣናዊነትም ጭምር ነው። በርግጥ የህወሀት ሰዎች ሰይጣንን ያሰለጠኑ የክፋት ጠበብቶች ናቸው። ይህን የምለው በተግባራቸው ነው። ሰዎቹ የሀሳብ ሰው አይደሉም። የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን የፍቅር እና ታላቅነት ችቦን ነጥቀዋል።
የክፋት ክንፋቸውን ከአንደኛው ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ዘርግተው በክፋት ሰረገላቸው የብዙውን ህይወት ረግጠዋል። በንፁሀን ደም ላይ ቆመው ደንሰዋል። በርግጥ ቢሆን ደስ የሚላቸው ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ የደም ዝናብ ቢያጥለቀልቃት ነው።
ፀሀይ ዝናብ ጨለማና ብርሀን የማግኘት ተፈጥሯዊ መብቷን ሳይቀር ማስቆም ቢችሉ እንዴት ደስ ባላቸው። ግን አይችሉም። አሁን ላይ ፍላጎት እንጂ አቅም ከእነርሱ ጋር አይደለችም። ሁሉ ነገራቸው ወርዶ ማላዘን እንጂ ችለው መጮህ እንኳ አይችሉም። ባዶነት አፍን ከፍቶ እየሳቀባቸው የክፋት ተሰጥዖቸው ስቃይ ሆኖ በተግባር ዋሻ ውስጥ እየኖሩት ነው። በቀጣይም ከዚህ እያነሱ እንደሚሄዱ እርግጥ ነው።
ይህ የሆነው በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ነው። ኢትዮጵያ ሁሌም በከፍታ መንበሯ ላይ ትሆን ዘንድ ከሚተጉት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
የመከላከያ ሰራዊቱ አካል በመሆን ግዳጅ እየተወጡ ከሚገኙት የሰራዊቱ ክፍሎች መካከል ደግሞ ምዕራብ ዕዝ አንዱ ነው። እዙ በሀገራችን ሰሜኑ ጫፍ ጁንታውን ያስጨንቃል። በመተከል ጁንታው ሌላኛው ግንባር ሲል ያሰለፋቸውን ቅጥረኞችና ተከፋዮች መግቢያ መውጫ ያሳጣል።
በጉባ የአለም ትኩረት የሆነውን የህዳሴ ግድብ በልዩ ጥንቃቄ እና ትኩረት ሰጥቶ በአስተማማኝ ሲጠብቅ ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ  የወለጋ ዞኖች ህወሀት ወለዱን አሸባሪው ሸኔን ያጠፋል።
በትንሽ ሃይል ብዙ ቦታ በመድረስ መስዕዋትነት ጭምር እየከፈለ  ይሰራል። ይህን የሚያደርገው ስለ ህዝብ ሰላም ስለ ሀገር ሉዓላዊነትና ስለ ሀገር አንድነት ነው። ይህን ለማድረግ ሙሉ ጊዜውን ይጠቀማል። እረፍት ለሰራዊቱ አንፃራዊ ነው።
መብላት መጠጣትም እንደዛው። በርግጥም እንደዚህ አይነት ታሪካዊ ሀላፊነት የሚወጣ የመከላከያ ሃይል ባይኖር እንደ ጠላቶቻችን ብዛትና ይዘውት ከተነሱ አላማ አንፃር ክብር ያለው ኢትዮጵያዊ ይቅር በህይወት ያለ ኢትዮጵያዊ አይኖርም ነበር።
ግን በሰራዊቱ ብርታት ሁሉም ነገር በተቃራኒው ሆነ። ጨካኞችን አፍራሾችን የሽንፈት ጎርፍ ወሰዳቸው። ሰው በሆኑት ጀግኖች አባት አያቶቻችን የተሰራችው ሀገራችን የሰውነት ምግባር በሌላቸው ስግብግቦች አትፈርስም።
Filed in: Amharic