አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ(ም) አነጋጋሪ ሆነ አሉ
አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)
የዚህች ሀገር ፖለቲካ ከማርጀት አልፎ እየጃጀ መምጣቱን የምንረዳው በየቀኑ ሊባል በሚችል ሁኔታ በጣም አስቂኝና አነጋጋሪ የሆኑ ክስተቶችን በመታዘባችን ነው፡፡ ፖለቲካን ከከተማ እስከጫካ ከልጅነት እስከሽምግልና ሲያራውጠው የነበረው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በዕረፍት ከሚገኝበት ሥፍራ ሆኖ ሰሞኑን በአሜሪካ ላይ በወሰደው አደገኛ ስጉምቲ ማለትም እርምጃ አሜሪካ እየተንቀጠቀጠችና ዲያስፖራውም ሰውዬውን በማግባባት አደገኛ እርምጃውን ቀለል እንዲያደርግ በማባበል ላይ እንደሚገኝ በኢትዮ360 አንድ ዝግጅት ዛሬ ምሽት ሰማሁ፡፡ ጀግና ማለት እንዲህ ነው! አሜሪካን በዓለም ላይ እንደልቧ የምትፈነጨው እንደ አቶ አንዳርግ ያለ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢንተርናሲዮናል ወደር የለሽ ጀግና በመጥፋቱ ነው፡፡ ይህን አንግሎ-ኢትዮጵያዊ ወይም ኢትዮ-እንግሊዛዊ ቼኩቬራና ሆቺሚን በዚህ ወቅት ማግኘት ለግንቦት ሰባትም፣ለኢዜማም፣ለብልጥግናም ….እ … ለአርበኞች ግንቦት ሰባትም፣ ለኦነግም፣ ለኦህዲድ ሸኔም፣ ለብአዴንም ትልቅ የምሥራች ነው – ምሥር ያብላንና፡፡ ግን ግን እውነቱን ለመናገር ካበዱ አይቀር እንዲህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገና ከዚህ የባሰ ለጥገና የሚያስቸግር የአእምሮ ብልሽትም ያሳየናል፡፡ “ካላበዱ ወይ ካልነገዱ (የልብ አይገኝም)” መባሉም እኮ ለዚህ ነው፡፡
አሞራና ጭልፊት መጥተው ጫጩቶቹን ሲልፏቸው በአጥር ሥር ተወትፎ ካሳለፈ በኋላ በሚስቱ በእመት እናት ዶሮ ፊት አንድ አውራ ዶሮ እንዲህ ብሎ ፎከረ አሉ – እንደመፎገ(ከ)ር የሚቀል የለምና፡፡
አምጪማ አምጪማ ጦሬን፤ ወንዙን ሳይሻገር እንድዠልጠው ወገቡን! ዘራፍ! ዘራፍ አካኪ ዘራፍ!
እመት እናት ዶሮም መለሰች፡-
አንቱም አንቱም አይዋሹ፤ አሁን ተመልሶ ቢመጣ አጥር ላጥር ሊሸሹ፡፡
የዛሬ ስንት ዓመት ገደማ ደግሞ (በ1978ዓ.ም ይመስለኛል) አሜሪካ ሊቢያን አጥቅታ ጋዳፊ ለጥቂት ከሞት ተረፈ፤ አንዲት ሴት ልጁ ግን በአየር ጥቃቱ ሞተችበት፡፡ ያኔ ታዲያ ኢትዮጵያም ፀረ አሜሪካ ስለነበረች (ወግ አይቀርምና ሲዳሩ ማልቀስ) ሚዲያዎቿ ሁሉ በአሜሪካ ላይ ተቃውሞ አዘነቡ፡፡
በዚያን ወቅት ከሰማሁት ዜና መቼም የማይረሳኝ የሚከተለው ነው፡-
“የአጋርፋ ገበሬዎች ማኅበር የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አስጠነቀቀ!”
የሚገርም ማስጠንቀቂያ ነበር፡፡ እርግጠኛ ነኝ – የአሜሪካ ጦር ያኔ በመጀመሪያ ደረጃ ተጠንቀቅ ተሰልፎ የአጋርፋ ገበሬዎችን ወረራ ይጠባበቅ ነበር፡፡ ግና እግዜር ሰወራቸውና አሜሪካኖች ተረፉ፡፡
ቀልድ ጥሩ ነው፡፡ ያለ ቀልድ ሕይወት ጎምዛዛ ናት፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ግሥላ ሆኖ አሁን “አንድነቷ ተጠብቆ” ስለሚገኘው ሀገሩ ምን ነበር ያለው?
“እኔ ክንዴን ሳልንተራስ አሜሪካ ኢትዮጵያን አታፈርስም፡፡ ባንዲራቸውን ዐይናቸው እያዬ አቃጥላለሁ፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁትም ከዚያ በላይ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፡፡” ፐ! ፐ! ፐ! አይ ወኔ!! ወላድ በድባብ ትሂድ፡፡ እንኳን የኔው ሆነ አንዱካ! የኛ ባይሆን እንዴት በቆጨኝ፡፡
በል አንተ ደግሞ “ስልብ አሽከር በጌታው እንትን ይፎክራል” በልና ሳንወድ በግድ አስቀን፡፡
ጥቂት ጥያቄዎች አሉኝ፡፡ አንደኛ ነገር ባንዲራው ምን አጠፋ? ሁለተኛ ነገር ባንዲራን ማቃጠል የሥልጡን ፖለቲካ አካል ነው ወይ? ሦስተኛ ነገር ዋናው አገር አፍራሽ መሀል አራት ኪሎ ተቀምጦ የማይመስል ነገር ውስጥ መግባት የምጣዱን ትቶ የዕንቅቡን እንደማማሰል አይቆጠርምን? አራተኛ የሰው ሀገር ባንዲራ ማቃጠል አማራን በነፃነት ትግል ስም ወደ ኤርትራ በረሃ ወስዶ በአውሬና በአማራ-ጠል ፖለቲከኞች ሤራ እንደማስጨረስ ቀላል ነው ወይ? አምስተኛ በሀገራቸው መኖር ያልቻሉ የዘር ፖለቲካ ሰለባዎችንና የኢኮኖሚ ስደተኞችን በክፉ ቀን ያስጠጋችን ሀገር በዚህ መልክ ወሮታውን መክፈል ነውር ከመሆኑም ባሻገር በህጉ መሠረትና ከህግ ውጪም ለሚደርስ ቅጣትና የበቀል በትር ተጠያቂው ማን ሊሆን ነው?
የምን አትርሱኝ ነው? በቃ፤ ዒላማ ተስቶ ዓላማ ሲጨናገፍ አርፎ መቀመጥም እኮ ያባት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ሁሉም ነገር ገብቶታልኝ – በጎንደርኛና በኃይሌ ገ/ሥላሤኛ ልንገርክ፡፡ የዓዞ ዕንባን ከእውነተኛ ዕንባ የመለየት ችሎታውም በእጅጉ አድጓልኝ፡፡ ይህን ጥሬ ሃቅ አንዴክስ አልሰምቶ ከሆነ ችግሩ ከሌላ ሳይሆን ከራሱ ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ስም ለትዝብት ከሚዳርግ ንግግርና የማስመሰል ሞቅታ መቆጠብ ይገባል፡፡ እንዳማሩ መሞት በዚህ ዘመን ሲያምር የሚቀር ቢሆንም አንዳንዴ አካባቢያዊና ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማጤን በቀላሉ ሊያስወግዱት ከሚቻል ሕዝባዊ ትዝብት ይታደጋልና ከወደቁ በኋላ መንፈራገጥን መቀነስ ደግ ነው እላለሁ፡፡ እውነታን ማሽሞንሞን ለማንም አይጠቅምም፡፡ አንዳርጋቸውና በብዙ ውጣ ውረዶች አልፎ ኢዜማ ላይ የደረሰው የፖለቲካ ስብስብ ፈተናውን ዘጭ ብሎ ወድቋል፡፡ “ማንነትህን እንድነግርህ ጓደኛህን ንገረኝ” የሚባለው ምሣሌያዊ አባባል ትልቅ መልእክት አለው፡፡ ሽንት ቤት ውስጥ የተቀመጠ ሰው የፈረንሣይ ሽቱ ቢቀባ ወይም የናርዶስ ሽቱ ሰውነቱ ላይ ቢያርከፈክፍ እውነተኛ መዓዛውን ለመለወጥ ይቸገራል፡፡ ከአሁን በኋላ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በማስመሰልና በጠላትህ ጠላቴ ነው የሲብስቴ ፈሊጥ የሚመራ አይሆንም፡፡ ይህን ሁሉ ስል ግን የአንዱን የቀደመ አስተዋፅዖ የማላወድስና የሰሞኑን ተቃውሞ መነሻ ምክንያት የማልቀበል ሆኜ አይደለም፡፡ ሰውዬው ለሀገሩ ብዙ ለፍቷል – በተሳሳተ አቅጣጫ ቢሆንምና ትግሉ በአሰለጦች ቢጠለፍም፡፡ “ኢትዮጵያን አትንኩ” ብሎ መጮህም ያስመሰግናል እንጂ አያስወቅስም – የአጯጯሁን መንገድ አለመለየት ለትዝብት ከመዳረጉ በስተቀር፡፡ ስለዚህ ወዝና ጣም ከሌለው ትያትራዊ የብልጽግናዎች ቀልድ ወይም ኮሜዲ እንታቀብ – The moral of the story. አሃ፣ ያን ያል ትልቅ ስብዕና ያው ሰው እንደዚህና እስከዚህ መውረድ የለበትማ! “ሳይበላስ ቢቀር” አለ ቴዲ አፍሮ፡፡ “እኔ ቆሜ ዐቢይ ማነው አሜሪካ ኢትዮጵያን አታፈርስም!” ይባላል? ዋናው አፍራሽ ማን ሆነና? ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ፡፡ በልጅነቴ እንግሊዝኛን እያጣመምኩና የአማርኛ ፈሊጦችን በቀጥታ ወደ እንግሊዝኛ እየመለስኩ ጓደኞቼን አዝናና ነበር – አንደኛዋ ፈሊጥ አሁን ትዝ አለችኝ – “tell me sayer!” – ከገባችህ ወንድ ነህ! ሆድህን አሞህ ውሎ አሞህ ይደር እንጂ አልነግርህ፡፡ “ንገሩኝ ባይ”፡፡