>

የምዕራባዊያን ጫና፤ ባለቤቱን ካልናቁ ... ( ያሬድ ሀይለማርያም)

የምዕራባዊያን ጫና፤ ባለቤቱን ካልናቁ …

ክፍል ሁለት
ያሬድ ሀይለማርያም

የምዕራባዊያንን ከልክ ያለፈ ጣልቃ ገብነት መቃወም እና አደብ ግዙ ማለት አግባቢ ቢሆንም ኢትዮጽያን ለዚህ አይነቱ ጫና የዳረግናት ግን እራሳችን መሆናችንን ሊሰመርበት ይገባል። ‘ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁም’ ነው።
ኢትዮጽያን ያስናቅናት እኛው ነን። 
– በመንደር ተቧድነን የተባላን እኛው፣
– የገዛ ወገናችንን ዘር እየቆጠርን ያሳደድን እና ያፈናቀልን እኛው፣
– አገሪቱን መረን ለለቀቁ፣ በሙስና ለተጥለቀለቁ፣ እውቀት ለራቃቸው እና እራሳቸውን ከአገር በላይ ለሚያስቀድሙ ጎጠኛች ፖለቲከኞች አሳልፈን የሰጠናት እኛው፣
– ትልቋን ኢትዮጵያን ወደ ትናንሽ አገር የሚቀይር ፈንጅ የተጠመደበት ሕገ መንግስት አዘጋጅተን አገሪቱን ማለቂያ ወደሌለው የእርስ በርስ ንቁሪያ የገፋናት እኛው፣
– በኩርፉያ ፖለቲካ አንባጓሮ ውስጥ የገባን እኛው፣
– የሰከነ ፖለቲካ መስራት ተስኖን ጦር ተማዘን እርስ በርስ ስንፋጅ ወገኖቻችንን ያስጨረስን እኛው፣
እኛው ገዝግዘን ባዳከምናት አገር ላይ ታሪካዊ ጠላቶች ቢበረቱ ምን ይደንቃል። ዛሬ ምዕራባዊያንም ሆኑ ሌሎች የውጭ አካላት ለምን ደፈሩን፣ ለምን በዚህ ልክ ተጋላጭ ሆንን፣ ለምን በውስጥ ጉዳያችን የውጭ ጣልቃ ገብነት በረታ የሚሉትን ያገጠጡ እውነትች መጋፈጥ ካልቻልን በመፈክር የውጭውን አለም ተጽዕኖ መቋቋም አንችልም።
እንደ ማህበረሰብ እውነትን የመፍራት በሽታው እየባሰብን ስለመጣ እንጂ የዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ እና ለውጭ ጫና በዚህ ደረጃ ተጋላጭ ያደረገን  ጤና ያጣው የውስጥ ፖለቲካችን ነው። ስለዚህ የውጪዎቹን ጏይሎች ጫና ከማውገዝ በዘለለ የውስጥ በሽታችንን በፍጥነት ማከም ካልቻልን ውርድ ከራስ ነው። እነሱ ስንጠነክር አብረውን ይቆማሉ፣ ወዳጅ ይሆናሉ፣ ኖቤል ይሸልማሉ፣ ወዳጅ መስለው ያደናግራሉ፣ አቅል ያስጥላሉ። በራሳችን ችግር ተጠላልፈን ስንወድቅ ግን ይሳለቁብናል፣ ይጠቋቆሙብናል፣ ሲከፋም ምሳር ይዘው ይመጣሉ። ከቻሉም አንድ የነበርነውን አሥር አገር ያደርጉናል።
ስለዚህ እኔን የበለጠ የሚያሰጋኝ፣ የሚያስፈራኝ እና የሚያሳስበኝ ኢትዮጽያን ገዝግዞ እየጣላት ያለው የውስጥ ፖለቲካችን የቆየ ነቀርሳ፣ የተጠናወተን የጎጥ ልክፍት፣ እርስ በርስ ያለመተማመን ህመም፣ የአድር ባይ ፖለቲካ አዙሪት እንጂ ከወደቀችበት ምሳር ይዘው የሚመጡት የውጭ ጏይሎች አይደሉም። ኢትዮጵያን ከተተበተበችበት የተንኮል እና የጎጥ ፓለቲካ እንታደጋት። ያኔ የውጪውን ጏይል አሳፍረን መመለስ እንችላለን። በምሳር ፈንታ የወዳጅነት አበባ ታቅፈው እንዲመጡ ማድረግ እንችላለን። ፖለቲካችን ሲሰክን አሁን ጉም መስሎ የሚታየን የውጭ ጏይሎች ያስነሱት አቧራ ይሰክናል።
ይሄው ነው። ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic