የከፋፍለህ ግዛው ምንጭ…!!!
ግርማ ታፈረ
ሰፊውን አገር ትተህ፣
ከጠባብ ሥፍራ ገብተህ፣
እጠብቃለሁ አንተን
መምጫህ መቼ ይሆን?
በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት የሃገርህ አርበኞች በዱር በገደል፣ አዝማሪ በግጥም፣ ባህታዊውና አበጋሩ በትንቢትና ህልም በመፍታት ሕዝቡ የሃገር ፍቅሩና ስሜቱ አገርሽቶ እምቢ ለሃገሬ እንዲል ይቀሰቅሱት ነበር፣ ላፍታ እንኳ ዝንጋኤ ውስጥ እንዳይገባ። ጣልያኖችን እረፍት ነሷቸው። ምን ይሻላል ብለው መከሩ፣ ትርክት እየፈጠሩ ህዝቡን በከፋፍለህ ግዛው ማስተዳደር የሚል ብልሃት ዘየዱ።
ከፋፍለህ ግዛው!
የደብረታቦር አስተዳዳሪ የነበረው ማጆር አጎሊኒ ህዝብ ሰብስቦ በሶስት ረድፍ ድሃ፣ ሙስሊም እና መኳንንት( ሹማምንትን) አድርጎ አሰለፈ።
ወደ ሙስሊሞቹ ጎራ በመሄድ በአስተርጓሚው መርዛማ መልዕክቱን ይጠምቅ ጀምር “እናንት የታላቁን ነቢይ የመሐመድን ሃይማኖት የተከተላችሁ እስላሞች ኢትዮጵያ አገራችሁ ስትሆን በሃይማኖት ልዩነት የተነሳ ክርስቲያን ነን የሚሉት ሃበሾች የበታች አድርገው ከርስት ነቅለው ሲገዙአችሁና ሲቀጠቅጧችሁ ይኖሩ ነበር፣ አሁን ግን ጩሆታችሁና ለቅሷችሁ ተሰምቶ የኢጣልያ መንግስት እናንተን ነፃ ለማውጣት የኢትዮጵያን ግዛት ይዟል። ከእንግዲህ ወዲህ ጭንቀታችሁና ውርደታችሁ ከናንተ ተወግዷል ለገናናው ገዥአችን ለሞሶሎኒ ረዥም እድሜ እየለመናችሁ በታማኝነት መኖር ነው” ሲል ተናገረ።
ከዚያ ወደ ድሆች መስመር አለፈና እንዲህ ሲል ተናገረ ” እናንት ድሆች እየተባላችሁ አሁን በናንተ ፊት ለተሰለፉት መኳንንትና ሹማምንት፣ ባላባቶች፣ ሊቃውንትና ካህናት ገንዘባችሁንና ጉልበታችሁን ስትገብሩላቸው፣ ወዛችሁንና ደማችሁን ስታንጠበጥቡላቸው የምትኖሪ ሕዝቦች ከዛሬ ጀምሮ መከራችሁ ተፋቀ፣ በኃያሉ መሪአችን የእኩልነት መብት ይኸውና ዛሬ ወሰዳችሁ። ስለዚህ መንግስት ከናንተ የሚፈልገው ግብር በቅንነት መገዛትና በታማኝነት ማገልገል ብቻ ነው” ብሎ ጨረሰ።
ቀጠለና ወደ መኳንቶቹ ጎራ አቀና ” እናንት የበጌምድር መኳንንትና ባላባቶች ካሁን ቀደም በናንተ ላይ የሚኖረውን ተገዥነት ከናንተ ይልቅ የኢጣልያ መንግስት ስለሚያውቀው የነበረባችሁን የተራዋጅነት አኗኗር ከዚህ ዘመን ጀምሮ ሰርዞታል። በእናንተ አስተያየት የአለፈው መንግስት በማዕረግ የሚያኖራችሁ ሳይመስላችሁ አይቀርም። ዳሩ ግን ገዥዎች ሁናችሁ ስትታዪ አንድ #የሽዋ ተራ ሰው የበላይ ሆኖ ያዛችሁ ነበር። ስለዚህ የሽዋ ህዝብ ተገዥዎች ናችሁ ናችሁ እንጂ እናንተ #አማሮች ገዥዎች አልነበራችሁም። በሹመትም ቢሆን ከደጃዝማችነት ማዕረግ አታልፉም ነበት፣ አሁን ግን በቅንነትና በታማኝነት ከሰራችሁ ለዋጋችሁ ወሰን አይደረግበትም።…እያለ ፓለቲካውን ከጨረሰ በኋላ የተሰበሰበው ህዝብ በኃዘንና በትካዜ በደስታና በዘፈን እየዋኘ በየቤቱ ተበተነ…ይሉናል የታላቁ የፊልም ባለሙያ የኃይሌ ገሪማ አባት ገሪማ ታፈረ (ዘብሄረ ጎንደር) “ጎንደሬ በጋሻው” በተሰኘው ድንቅ መፅሃፋቸው።
ጎበዝ ንቃ!
ማጆር የተጠቀመውን አመክንዮ ስታየው ሙስሊሙንም፣ ድሃውንም፣ መኳንንቱንም ነፃ ያወጣ ይመስላል፣ ግን የጭቆና ቀንበሩን እየጫነባቸው ነበር። ነፃ ፍቃዳቸውን አታሎ እየቀማ ነበር። ፍቃድህን ካገኘ በኋላ እርስ በርስህ እንደ ሃገር ልጅነት ሳይሆን እንደጠላት እየተፈራረጅክ ረዥም እድሜ ለታላቁ መሪ ለቦንቶ ሞሶሎኒ እያልክ ትኖራለህ።
እንግዲህ እንደዚህ ነበር እስከዛሬ ድረስ ከፋፍለው ሲገዙህ የነበረው፣ የውጭም የውስጥም ገዥዎችህ። አሁንም አሳምኝና ግልፅ የሆነ የሮሮ አመክንዮ እየጋቱህ አገርህን ወደ ገደሉ አፋፍ እንድትገፋት እያደረጉህ ያሉት። ከሁሉም በፊት ከግልና ከቡድን ጥቅምህ የሃገርህን ደህንነት አስቀድም። ሊዚህ ነው አዝማሪው:-
ሰፊውን አገር ትተህ፣
ከጠባብ ሥፍራ ገብተህ፣
እጠብቃለሁ አንተን
መምጫህ መቼ ይሆን? ብሎ የተቀኘው። ጠባቡ የግልና የቡድን ክንንብህ ገፈህ ጣልና ትልቁን ብሉኮ ተመልከት፣ ሰፊዋን ሃገርህን። እንጠብቅሃለን።
ሃገር አልባ ሆነህ ነፃነትን ተቀናጀሁ አይባል። የቀረበልህ አማላይ ሃሳብ የግልህን ደህንነት ሊያስቀድምልህ ይችላል ግን በረዥም ጊዜ ሃገርህንን ያሳጣሃል። ሁሉንም ነገር በሃገርህ ማዕቀፍ ውስጥ ገምግመህ አሳልፍ። አስፈላጊም ከሆነ እስከ መስዋዕት።
“አርኩም ይሄድና ፈረንካው ያልቅና፣
አንተ የምትይኝ አንቱ ትይኝና፣
ውጣ የምትይኝ ግባ ትይኝና፣
ያስተዛዝበናል ይኸ ቀን ያልፍና”
ነፃነት ያለሃገር ምንም ነው፣ ስደት ነው!
ኢትዮጵያ ወይም ሞት!
(መፅሃፉን የትም ፈልጋችሁ አንብቡት)