>

“ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው”  ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ 

“ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው” 
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ 
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ – ከወፍ አርግፍ

 ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ ነፃነት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በወፍ አርግፍ ከተማ የምስጋና እና የእውቅና ዝግጅት እየተካሄደ ነው። በእውቅና ዝግጅቱ ላይ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለየት ያለ ከአፓርታይድ አገዛዝ ከፍ ያለ ግፍና በደል ተፈፅሟል ነው ያሉት።
አሸባሪው ትህነግ በሕዝቡ ላይ ግልፅ ዘር ማጥፋት ፈፅሟልም ብለዋል። ከከፋኝ እስከ አሁኑ ትውልድ ድረስ በተደጋጋሚ ትግል ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ካስገደዱ አጀንዳዎች ውስጥ የወልቃይት ጠገዴ የነፃነት ጥያቄ አንዱ ነው ብለዋል።
ትህነግ ገና ከደደቢት በረሃ ሲነሳ በአማራ ጠል ትርክት የተነሳ መሆኑን ነው የተናገሩት። በተስፋፊነት ባሕሪው አካባቢውን በኀይል ይዞ የወልቃይት ጠገዴን ያልተነካ ሀብት ለመጠቀም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘውን የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙንም አስገንዝበዋል።
ትህነግ የአማራን ማንነት ለማጥፋት ያልሞከረው ነገር እንደሌለም ተናግረዋል። “ማንነት ከውስጥ የሰረፀ በጭቆና ብዛት የማይተውት በመደለያ ገንዘብና ጥቅማጥቅም የማይቀይሩት ነው” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ወልቃይቴው ለአማራነት ክብሩ መስዋዕትነት ከፍሏልም ብለዋል።
ህፃናት በቤተሰቦቻቸው ቋንቋ እንዳይናገሩና እንዳይማሩ ሲደረጉም መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የትህነግ የመጨረሻው የጥፋት መርከብ በማይካድራ ላይ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ቢሆንም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለዓመታት ብዙ ማይካድራዎችን አይቷል ነው ያሉት።
ትህነግን በተለያዩ የትግል ዘርፎች በመውጋት ድል መገኘቱንም ተናግረዋል። የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና መከላከያ ሠራዊት ባደረገው ተጋድሎ ነፃነት ተገኝቷልም ብለዋል። ወልቃይት ጠገዴ ቁልፍ የሀገሪቱ ሥፍራ መሆኑንም አንስተዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ነፃ እንዲወጣ ላደረጉ ሁሉም አመስግነዋል።
Filed in: Amharic