>
5:13 pm - Sunday April 20, 2408

የህዳሴ ግድብ በክረምት የሙከራ ኃይል ማመንጨት ይጀመራል (አዲስ አድማስ)

የህዳሴ ግድብ በክረምት የሙከራ ኃይል ማመንጨት ይጀመራል

አዲስ አድማስ

   “የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው”

ኢትዮጵያ በመጭው የክረምት ወራት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የሙከራ ኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የገለጸ ሲሆን በመጭው ክረምት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድም ተነግሯል፡፡
ከግድቡ ሙሌትና ግንባታ ጋር ተያይዞ የአሠራር ሂደቱን “ምንም ዓይነት ኃይል አያደናቅፈውም” ብሏል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፡፡
የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል ዶ/ር  በለጠ ብርሃኑ ባለፈው ረቡዕ ለኢቢሲ በሰጡት አስተያየት፤ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና፤የታላቁ  የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረዋል፡፡ በጎረቤት ሃገራትና ታላላቅ ሃይቆች ክልል የሚገኙ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤትጋር በመተባበር፣ “የናይል ፍትሃዊ አጠቃቀም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለክልላዊ ትብብር ያለው ሚና” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በሶስቱ ሃገራት የተመራማሪዎች ብሄራዊ ቡድን በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደሚካሄድ ነው አቶ ደመቀ መኮንን የገለጹት፡፡  የሶስትዮሽ ድርድሩ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መርህ መሰረት ውጤታማ እንዲሆን የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነትም አረጋግጠዋል።
ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑም አልሸሸጉም፤አቶ ደመቀ መኮንን፡፡
በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩት የደቡብ ሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ጉዳዮች ሚኒስትር ደንግ ዳው ደንግ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የሰላም ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብጽ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፣ የግብጽ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር መግለጻቸው ጥሩ ጅማሮና የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ ገለጻ፣ ግብጽ በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ ቀደም ሲል ታራምድ የነበረውን አቋም በመቀየር፣ ኢትዮጵያ የምታራምደውን አቋም ወደሚደግፍ ሃሳብ መሸጋገሯን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

Filed in: Amharic