>

ዘገምተኛውን* ‹‹ህገመንግሥት››... ‹‹አንቀልባው ወለቀ›› የምንለው መቼ ይሆን? (አሰፋ ሀይሉ)

ዘገምተኛውን* ‹‹ህገመንግሥት››… ‹‹አንቀልባው ወለቀ›› የምንለው መቼ ይሆን?

አሰፋ ሀይሉ

ለመሆኑ ከአንዲትም ከተማ አንሳ፣ የሆኑ ቀበሌዎች ውስጥ ላሉ አደሬዎች ‹‹ሐረሪ ክልል›› ብሎ የክልልነትን ሥልጣን የሰጠ፣ እና ከ7 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ላላት አዲስ አበባ ከተማ የክልልነትን መብት የነሣ የአዕምሮ ዘገምተኞች ካልሆኑ በትክክል ማገናዘብ የሚችሉ ሰዎች የማይጽፉት ዝግመተኛ ሕገመንግሥት እንዴት ‹‹ህገመንግሥት›› ተብሎስ ለመጠራት ይችላል? ያንን የዝግመተኞች ህገመንግሥት እጃቸውን ጭነው የማሉ ዘገምተኞችስ እንደት የሀገር መሪዎች ይባላሉ?
ህገመንግሥቱን ማሻሻል ማለት – አዲስ አበባን ከእነ 7 ሚሊየን ነዋሪዎቿ መዋጥ የሚመስላቸው ዝግመተኛ ዘረኞች እንዴትስ አድርገው ሀገርን ወደተሻለ ለውጥ ሊያሻግሩ ይችላሉ? ለመሆኑ ክልል-14 ተብላ በህገመንግሥቱ መጀመሪያ ላይ የታወቀችው አዲስ አበባ በየትኛው ሪፈረንደም ነው ክልልነቷ ተነጥቆ ‹‹ባለቤት-አልባ›› ከተማ ለመሆን የበቃችው?
ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ እና አዲስ አበባ – የፌዴራሉ መንግሥት ነፃ ክልሎች ናቸው በማለት የሚደነግገው የሽግግር መንግሥት ቻርተር ተሰርዞ፣ ሐረር ከተማ ከወቅቱ 300 ሺህ ነዋሪዎቿ ጋር 30 ሺህ ለማይሞሉ አደሬዎች በአፓርታይድ ገጸበረከነት ተላልፋ እንድትሰጥ በወያኔና አጋፋሪዎቿ የተወሰነበትን ምክንያት የሚያውቅ ሰው አለ ወይ?
ይሄ የብሔሮችን እኩልነት እና የብሔር ብሔረሰቦችን (እና ‹‹ሕዝቦችን››) መብት አስጠብቃለሁ የሚል የአዕምሮ ዘገምተኞች የጻፉት ህገመንግሥት – ለመሆኑ በኢትዮጵያ የሚገኙትን ከ80 በላይ ብሔሮች እንዴት የክልልነት መብት ነሳቸው? የብሔሮችን እኩልነት ያረጋገጠ ህገመንግሥት – እንዴት ጥቂት ብሔሮችን ብቻ መርጦ ክልል፣ ሌሎችን ደግሞ ክልል-አልባ አድርጎ ያስቀራል? ለመሆኑ ይሄ ‹‹ህገመንግሥት›› ከተራ የህጻን ልጅ የቤት ሥራ መለማመጃ ደብተር የተሻለ ነው ወይ?
በእኔ የግል አመለካከት፣ የአዕምሮ ዘገመተኞች ብቻ፣ አሊያም በትክክል ይዘቱን ያልተረዱ ብቻ ናቸው ይህን የዘገምተኞች ህገመንግሥት ‹‹ህገመንግሥት›› ብለው ሊጠሩትና፣ ሊጠብቁት የሚችሉት፡፡ እናም ይሄን ከህጻናት ሙንጭርጭር ጽሑፍ የማይሻል የቁጩ ህገመንግሥት ቀዳዶ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥንና እውነተኛና ፍትሃዊ የህዝብ አስተዳደር ሥርዓትን የሚያሰፍን እውነተኛ ህገመንግሥት ለማምጣት ቆርጠን መነሳት ያለብን ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው፡፡
ሁላችንም ዘገምተኞች ካልሆንን በስተቀር፣ ይሄንን ዘገምተኛ ህገመንግሥት ተሸክመን አንኖርም፡፡ ሁላችንም ደግሞ ዘገምተኞች እንዳልሆንን ግልጽ ነው፡፡ ህገመንግሥት የሚል ስም የተሰጠው ይኸው የዘገምተኞች ሙንጭርጭር ጽሑፍ ታግዶ፣ አሁኑኑ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የበለጸገ አዲስ ህገመንግሥት መጸፍ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ አለበለዚያ ከዘገምተኛው ህገመንግሥት ጋር አብረን እንዳዘገምን እንቀራለን፡፡
በእኔ አመለካከት፣ ከረዥም ዘመን ደም መፋሰስና የባሩድ ጭስ ተላቅቀው ከጫካ የመጡ ትኩስ ባለጠብመንጃ ታጋዮች ተሰብስበው የዛሬ 30 ዓመት የሞነጫጨሩትን ይህን ዘገምተኛ የህጻናት መልመጃ ደብተር፣ አሁን ላይ ያለ በሚሊዮን የሚቆጠር ነፍስ አውቄያለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ሚሊየን ጊዜ አስከንድቶ መጻፍ ካቃተው፣ እውነትም ራሳቸው ለቅላቂዎቹ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ካለእነሱ ሰው የላትም፡፡ እውነትም እነሱ ከሌሉ፣ እና ዘገምተኛ ህገመንግሥታዊ እቃ-እቃቸው ከፈረሰ፣ ኢትዮጵያ ያልቅላታል፡፡ ማለት ነው፡፡
ግን ነው ወይ? እንደዚያ ነን ወይ? ከነዚያ የናወዙ አፈሙዛሞች የተሻሉ ዜጎች ኢትዮጵያ ልታፈራ አልቻለችም? የሰው መካን ነች ሀገራችን? በእኔ የግል አስተያየት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የወል (የጋራ) አስተሳሰብ፣ ከዚህ የወረደ የጥቂቶች ዘገምተኛ ወረቀት በላይ ሆኖ ካልተገኘ፣ እንግዲህ፣ የሚሻለው ይህንኑ በጫካ አፈሙዘኞቹ የተጻፈልንን ‹‹ህገመንግሥት›› አዝለነው መኖር ነው ያለን ምርጫ፡፡
በበኩሌ ግን ይህን ለመምረጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ዘገምተኛ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ ሊታሰብ አይችልም፡፡ በቃን ብሎ ይህን ከደረጃችን ያሳነሰንን የዘገምተኞች ሰነድ መቀየሪያው ጊዜው አሁን ነው፡፡ እውነት ትመራለች፡፡ ይኸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic