ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የ2013 ዓ.ም የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ትናንት በጸሎት ጀምሯል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱን ዓመታዊ ጉባዔ በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘወትር ለጸሎት የተጠመዳችሁ ሁኑ ብለዋል፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ የቤተክርስያን ቁልፍ መሳሪያ ጸሎት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ነገሮች ከመደረጋቸውና ከመታሰባቸውም በፊት ድንበርና ወሰን በሌለው እውቀቱ እግዚአብሔር ያውቃል ብለዋል፡፡ ሁሉን አዋቂው አምላክ ለሰው ልጆች ብሩህ አዕምሮ ሰጥቶ አገናዝበው የሚበጃቸውን እንዲመርጡ ፍጹም ነጻነት ሰጥቷቸዋልም ነው ያሉት፡፡ ሰዎችም ሆነ መላዕክት ነጻነታቸውን ተጠቅመው ያለ ምንም ተፅዕኖ ሲወስኑ በውሳኔያቸው ላይ እግዚአብሔር ተፅዕኖ አያደርግም፡፡ ውሳያቸውን ተከትሎ በሚመጣው ውጤት ግን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
የሰው ልጅ ውድቀት የተከሰተው በተሰጠው ነጻ ምርጫ ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ዛሬም በዓለም እየሆነ ያለው ይህ እውነት ነው ብለዋል፡፡ ሰው የከፋ ሐጽያትን ለመፈፀም ሲሮጥ ምክርና ትምህርት ከመስጠት ያለፈ ተፅዕኖ የለም፤ እሳትን እና ውኃን አቅርቤልሃለሁ እጅህን ወደ ፈለከው ክተት እንዳለ ነው ያሉት፡፡
የሰው ልጅ መከራዎችንና ፈተናዎችን እየጎተተ የሚያመጣቸው በራሱ ነጻ ምርጫና ውሳኔ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የምንኖርባት ዓለመ ሰብ ምንጊዜም ከፈተናና ከመከራ ተለይታ አታውቅም፤ ይህ የማይቀር ነገር መሆኑን የሚያውቅ ፈጣሪ የሰጠው መርህ ወደፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ የሚለውን ነው ብለዋል፡፡ ከመከራ ለመዳን የተሰጠው ስልት ተግቶ መፀለይ ነው፣ ስንፀልይም ለራሳችን ብቻ አይደለም ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፡፡
ቤተክርስቲያን ስለ ዓለም ሁሉ ትጸልያለችም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ ከባድ ፈተና እየተከሰተ ስለሆነ ከምንጊዜውም በላይ ወደ አግዚአብሔር ልንፀልይ ይገባል ብለዋል፡፡ ምእመናን፣ አብያተ ክርስቲያናት ፈተና ላይ ሲወድቁና መከራ ሲበዛባቸው ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመለከተው ስለሆነ የመፍትሔው አካል ሆኖ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
ይህን የመከራ ጊዜ ዓይተን እንዳላዬን ሰምተን እንዳልሰማን በዝምታ የምናልፈው ከሆነ ለቤተክርስቲያን ጠባሳ ታሪክ ይሆናል፤ በእግዚአብሔርም ያስጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ምዕመናን በቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔ ላይ አመኔታ እንዳያጡ መጠንቀቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ጉባኤው በሀገሪቱ በልዩ ልዩ አካባቢዎች እየተጎዱ የሚገኙ ዜጎችን መፍትሔ አምጭ ሆኖ ከጎናቸው ሊቆም ይገባልም ብለዋል፡፡ ድጋፉን በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ ቁሳቁስ በማቅረብ ሊያከናውን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ድጋፍ ለቤተክርስቲያን አዲስ ነገር አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው የአሁኑን ለዬት የሚያደርገው የችግሩ ውስብስብነትና ክብደት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ክብደቱን አይተን የምንሸሸው ሳይሆን በትብብር መከራውን እና ፈተናውን መቋቋም ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡
የሁሉም ነገር መሠረትና የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም አስፈላጊ ዋጋ መክፈል እንደሚገባ መክረዋል፡፡ ዋስትና ያለው ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ መወያዬት፣ መግባባትና ሀገራዊ ስምምነት መፈፀም ሲችሉ ነው ብለዋል፡፡ ሁሉም በመልካም ሥራ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርብዋል ቅዱስነታቸው፡፡