>
5:28 pm - Monday October 9, 6739

"በፍትህ አደባባይ ስለ ልጄ እጮሃለሁ....!!!" (ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ)

“በፍትህ አደባባይ ስለ ልጄ እጮሃለሁ….!!!”

ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ

 

*….ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ የት እንደደረሱ ያልታወቁት ታጋች የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወላጆች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ፍርድ ቤት ምስክርነታቸውን አሰምተዋል።
 ቢያንስ አስር የሚሆኑ የተማሪዎቹ ወላጆች ከማዕከላዊ ጎንደር፤ ከምዕራብ ጎጃምና ከምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከማክሰኞ ግንቦት 17 እስከ  ግንቦት 19 2013 ድረስ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ለዓቃቤ ህግ ምስክር ሆነው ፍርድ ቤት ተገኝተዋል፡፡
ከማዕከላዊ ጎንደርና ከምዕራብ ጎጃም የመጡት ወላጆች በዋነኝነት ‹‹የታገቱ ተማሪዎቹ የሉም›› የሚለውን ብዥታ በማጥራት ልጆቻቸው መታገታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክርነት የሰጡ ሲሆን ከወለጋ የመጡት አቶ መሳይ የተባሉ ወላጅ ደግሞ እኔም ከእገታ አምልጫለሁ በሚል  እማኝ ሆነው ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሁሉም ወላጆች በተለያየ አገላለጽ ይሁን እንጂ ልጆቻቸው ካለፈው ዓመት ህዳር 25/2012 ጀምሮ ልጆቻቸው እንደታገቱ የገለጹ ሲሆን የልጆቻቸውን መታገት ከራሳቸው ከልጆቻቸው አንደበት በስልክ መስማታቸውንና አጋቾቹ ኦሮምኛ ቋንቋ እንደሚናገሩ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም አጋቾቹ በወቅቱ ‹‹ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹን ያገትነው አማራ ክልል ውስጥ የታገቱ የኦሮሞ ተማሪዎች ስላሉ ነው›› የሚል ምክንያት ማቅረባቸውን ወላጆቹ ከልጆቻችን ተነግሮናል ሲሉም ለችሎቱ አብራርተዋል፡፡
ከችሎት በኋላ ስለታጋች ልጆቻቸው ለዓባይ ሚዲያ አስተያየት የሰጡት ወላጆች አሁንም ልጆቻችን ይመለሱልን ሲሉ ተማጽነዋል፡፡
አንድ ወላጅ ለምስክርነት አዲስ አበባ ስለመምጣታቸው ሲናገሩ ‹‹እኔ የመጣሁት በፍ/ቤት ሂደት ልጄ ትመለስልኛለች ብቻ ብየ ሳይሆን በፍትህ አደባባይ ለልጄ ድምጽ ለማሰማት ነው›› ብለዋል፡፡
ልጄ ከጠፋብኝ 18 ወራት ተቆጥረዋል የሚሉት ሌላኛው ወላጅ በበኩላቸው ‹‹ነገሩ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ አንድ ሰሞን የት ጠፉ ሲል የነበረው ብዙ ሰው ረስቷቸው ይሆናል፤ ለእኛ ለወላጆች ግን ሰቀቀኑ ብዙ ነው›› ይላሉ፡፡
‹ወይ አሉ ወይ ሞቱ› የሚለውን የሚያረጋግጥልን አካል እስካላገኘን አዕምሯችን ረፍት አላገኝም ሲሉም ወላጆች ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
Filed in: Amharic