>

በአራት ቀሚስ ለአማራ ተፈናቃዮች  2,064,000 ብር ያሰባሰበችው ወጣት አስደናቂ ተግባር (አስራት መገናኛ ብዙሀን)

በአራት ቀሚስ ለአማራ ተፈናቃዮች  2,064,000 ብር ያሰባሰበችው ወጣት አስደናቂ ተግባር

አስራት መገናኛ ብዙሀን

 

ጉዳዩ እንዲህ ነው፤
ሰሜን አሜሪካ ፊላደልፊያ የምትኖረው የ23 ዓመቷ ወጣት ቅድስት ዘውዱ የአማራ በአገሩ መገደል፣ መፈናቀልና መገፋት ሰርክ ያስጨንቃታል።
ዘወትር በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች፣ የድጋፍ ጥሪዎች እና ወገንን በመርዳት ውስጥ ቀዳሚ ናት።
የአማራን ባሕል፣ እሴትና ስነ-ልቦናም በምትኖርበት አገር በስፋት በማስተዋወቅ ምስጋና ተችሯታል።
ከዕለታት አንድ ቀን አገር ቤት ከሚኖሩ ቤተሰቦቿና ወዳጆቿ አራት የአገር ባሕል ቀሚሶች ይላኩላታል።
<<ወገን እየተጨፈጨፈ፣ በግፍ እየሞተ፣ እየተፈናቀለ፣ አማራ በአጣብቂኝ ተይዞ ከተሞቹ እየወደሙ፣ ቀሚስም ውበት፣ ዘመኑም ጥምቀት አይሆንምና ቀሚሶቼን ሸጨ አንድ ተፈናቃይ ብረዳበት ይሻላል>> በማለት ገበያ መውጣቷን ለአሥራት ሚዲያ በሰጠችው ቃለ-ምልልስ ተናግራለች።
ገበያውም በዋናነት በማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፎው የሚታወቀው <ዮኒ ማኛ> ወደተባለ ሌላ ወገን ወዳድ በመሄድ እገዛውን ትጠይቃለች።
ግለሰቡም ሃሳቧን በመቀበል ቀሚሶቹን ይዛ በማህበራዊ ትሥሥር የቀጥታ (Live) ጨረታ በማድረግ በአራት ቀሚስ 40 ሺህ ዶላር (2,064,000 ብር) ትሰበስባለች።
ይህንንም ገንዘብ ለወልቃይት የዘመናት ሰቆቃ ተጎጂዎች፣ ለመተከል፣ ከተለያዩ የኦሮሚያና ደቡብ አካባቢዎች ለችግር ለተዳረጉ የወሎ ተፈናቃዮች እና በአጣዬ ጥቃት ለተፈናቀሉት መልሶ ማቋቋሚያ እንዲሆን እኩል ቦታ በማካፈል አድርሳለች።
ይህች አርአያ ወጣት በጨረታው ወቅት ላገዙኝ ለዮኒ ማኛ፣ ሰናይት አማረ፣ ሚጡ ግርማ፣ እየሩስና ፍረሕይወት ክብርም ምስጋናም አቅርባለች።
በተግባር፣ የፈጠራ ችሎታና አንድነትን የሚያፀናው ይሕ እውነተኛ ውግንና እና አርበኝነት ትልቅ ክብር እንደሆነ የዝግጅት ክፍላችን ያምናል። ያበረታታልም።
እናመሰግናለን!
Filed in: Amharic