ትልቅ ሀገር ትንንሽ መሪዎች…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
*…. የምዕራባዊያን ጫና እና የኢትጵያን የውጭ ግንኙነትን በነቀዝ ስንዴ ደረጃ የሚመዝኑ ሹሞች፤
የነቀዘው ዲፕሎማሲያችን ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን እንደሆነ እርግጥ ነው። የኢትዮጵያ ዲያስፖራም ለአገሩ ቀናይ ቢሆንም የተበታተነ እና በተቃርኖ የተዋጠ፣ እርስ በርሱ የማይግባባ እና ቡድናዊ ጥበብ የጎደለው ስለሆነ ኢትዮጵያን ሊታደግ የሚችልና የተሳካ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሊሰራ እንደማይችል ጠቁሜ ነበር።
ዛሬ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጫና ባሳደሩት እና አገሪቷንም አስጊ ወደሆነ ደረጃ የከተቱት የውጭ ጫናዎች እንዲበረቱብን ያደረጉትን ጉዳዮች በስሱ እቃኛለሁ።
በአለም አቀፍ የአገሮች ግንኙነት ሦስት አይነት የማዕቀብ ምንጮች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው በተባበሩት መንግስታት በኩል፤ በተለይም የጸጥታው ምክር ቤት የሚጥለው እገዳ ነው። ማዕቀቦቹ የተለያዩ ደረጃዎች አላቸው። ሁለተኛው ደግሞ የተወሰኑ አገራት፤ ሁለት እና ከዛ በላይ ሆነው በአንድ አገር ላይ ማዕቀብ ሊጥሉ ይችላሉ። ሦስተኛው ደግሞ አሁን አሜሪካ እንዳደረገችው አንድ አገር በሌላው ላይ በነጠላ የሚጣል ማዕቀብ ነው። ስለነዚህ የማዕቀብ አይነቶች ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ። አሜሪካ የጣለችው የቪዛ ማዕቀብ ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ እንዲል እና ሌሎች አገራት እና አለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ድርጅቶች እንዲቀላቀሏትም ግፊት እያደረገች ነው። ከቪዛ መለስ ያሉት ሌሎቹ ማዕቀቦች ቀጥታ ጫናቸው የሚያርፈው አገሪቷ እና ሕዙቡ ላይ ስለሆነ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ልትቋቋማቸው አትችልም። መዘዙም ብዙ ነው።
የሰሞኑን እቀባ ተከትሎ አንዳንድ እንጭጭ ሹማምንት ስለማዕቀቡ ባደባባይ የሰጡት ምላሽ እጅግ የሚያሸማቅቅ፣ ኢትዮጵያ በእነማን እጅ ነች የሚያስብል እና አገሪቱ ለዚህ አይነቱ መከራ የተዳረገችው በእነሱ ክሽፈት መሆኑንም የተረዱ አይመስልም። ለቪዛ እገዳው በመንግስት ደረጃ በጽሑፍ የተሰጠው ምላሽ አንዳንድ ግልጽነት የጎደላቸው ነገሮች ቢኖሩትም የተሻለ ነው።
ወደ ሹሞቹ ልመለስና በቪዛ እገዳው ላይ በማላገጥ መልክ የሰጡት ምላሽ ለአቅመ ፖለቲካ መድረሳቸውንም እንድጠራጠር አድርጎኛል። አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ አድርጋ የማታቀውን አይነት ከፍተኛ ጫና መፈጸም ስትጀምር ለአንድ አገር ለሚመራ ሹም ሊታየው የሚገባው ነገር የነቀዘ ስንዴ እና ባለስልጣናት ቪዛ በመከልከላቸው አገሪቷ ከወጪ የምታድነው ዶላር ወይስ አሜሪካ ስታራምደው የቆየችው ከገዢዎቹ ጋር የመሞዳሞድ የውጭ ፖሊሲ መቀየሩን?
የእኔ ስጋት አንዳንድ ሹሞች በየመድረኩ እያንጸባረቁት ያለው ያላዋቂ መግለጫና ድፍረት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በሚንስትሮች ምክር ቤት አካባቢም ውስጥ ለውስጥ የሚንጸባረቅ እንዳይሆን ነው። እንዲያ ከሆነ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል አይሆንም።
ዛሬ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ፍዳ እየከፈለች ያለችው በትላንቱ ኢህአዴግ፤ በዛሬዎቹ ህውሃት እና ብልጽግና አመራሮች ክሽፈት እንደሆነ እነዚህ ሹሞች የተረዱ አልመሰለኝም። አዎ እደግመዋለሁ ኢትዮጵያን ያዳከማት የእናንተ ክሽፈት ነው።
– ወያኔ የጀመረውን እና ያጠመቃችሁን የብሔር እና ጥላቻ ያዘለ ፖለቲካ በብዙ እጥፍ አክርራችሁ ቀጥላችሁበታል፣
– የተሳሳተ የፖለቲካ ቅኝታችሁ እና ለሕግ የበላይነት ባሳያችሁት ከልክ ያለፈ ዳተኝነት ምክንያትሚሊዮኖች በገዛ አገራቸው እንደ ባዳ እየታዩ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ ገሚሶቹም በጨካኞች እንዲጨፈጨፉ አድርጋችኋል፣
– የአገሪቱ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ከድጡ ወደማጡ እንዲወርድ እና አለም ፊቱን እንዲያዞርብን አድርጋችኋል፣
– ወያኔ በጎሳ ከፋፍሎ የበታተነውን ሕዝብ እናንተ ትሰበስቡታላችሁ ሲባል ጭራሽ አግላይ በሆነ አደረጃጀት ከሁለት ብሔር ስም ቃላት እያዳቀላችሁ ከ80 በላይ ብሔረሰብ ባለበት አገር የሁለትዮሽ ዳንስ ጀመራችሁ። ኢትዮጵያ በሁለት ብሄሮች ጥምረት ብቻ ትቆም ይመስል የባህርዳር እና የአዳማ ከአንገት በላይ የሆነ የፍቅር ጨዋታ፤ ኦሮ-አማራ በሚል ማደናገሪያ ብሽሽቅ ውስጥ ገባችሁ።
– ይህ የብሄሮች ጥምረት የመሰለ የብሽሽቅ ፖለቲካ የትግራይን ጦርነት ወለደ። ከመከላከያ ሠራዊት አባላት አንስቶ የብዙዎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ቀጠፈ። ትግራይን የመሰለ ሰፊ ክልል እንደገና በብዙ አመት ወደኋላ ወስዶ ድባቅ አስገባ። ከፍተኞ ግምት ያለው የአገር ንብረትም ወደመ። ገሚሱም በኤርትራ ጦር ተዘረፈ። እዳው የአገር እንደሆነ የነቀዝ ፖለቲካ አራማጆች የገባቸው አልመሰለኝም፣
– በመተከል፣ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች፣ በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች፣ በአፋር እና በሱማሌ ክልል አዋሳኞች፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ መንደሮች፣ ጌዲዮን ጨምሮ በተለያዩ የደቡብ ክልሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ ለደረሰው ሰቆቃ፣ የሰዎች መገደል፣ የንብረት መውደም እና መፈናቀል ቀጥተኛ ተጠያቂዎቹ እናንተ ሹሞቹ እንደሆናችሁ አሁንም የገባችሁ አልመሰለኝም። ይሄ መዘዝ በቪዛ እቀባ የሚያበቃ መስሏችው ከሆነ ማዕቀቡን ከነቀዝ ስንዴ ጋር ማያያዛችሁ የጉድ አገር ነው የሚያሰኘው።
– የቪዛ ማዕቀቡ በሹሞች ላይ የማነጣጠሩ እንድምታ ባለፋት አመታት እና በትግራይ ለተፈጸሙት ሰቆቃዎች እና ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ መሆናችሁን ማሳያ ምልክት ነው። ምዕራባዊያኑ ቪዛ ከልክለው ብቻ አያቆሙም ቀውሱ ከተባባሰ እናንተን ወደ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማምጣቱ ቀጣይ እርምጃቸው እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው።
– ምዕራባዊያኑ ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ለሰብአዊነት ካላቸው ተቆርቋሪነት ሳይሆን፤ በዋነኝነት በቀጠናው ላይ ካላቸው የውጭ ፖሊሲ ለውጥ ጋር የተያያዘ ይመስላል። ይሄ ደግሞ ከህዳሴ ግድብ፣ ከግብጽና ሱዳን ፖለቲካ፣ ከዛም ፈቅ ካለ ከእስራኤል እና ከአረቡ አለም ጋረ እና ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ የቆዩ ችግሮች ጋር ይያያዛል።
– በእርዳታ የሚገኝ የነቀዘ ስንዴ እየበላን አድገን የነቀዘ ፖለቲካ ብናራምድ እና አገሪቱ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት በነቀዘ ስንዴ ብናሰላው አይገርምም። የሚያሳስበው እንዲህ ያሉ ፖለቲከኞች የሚመሩት አገር እያደር አብሮ መንቀዙ ነው። አገርም እንደ ስንዴ የነቀዘ እንደሆን ያኔ ማጣፊያው ያጥራል። ኢትዮጵያ ወደዛው እየሄደች ይመስላል፣
– ሌላው የሚያሳዝነው ሹሞች ሲባልጉ፣ መስመር ሲስቱ፣ በነቀዘ አስተሳሰብ አገር ሲያነቅዙ ተውእንጂ፣ ይሄ አካሄድ አያዋጣም፣ በሕግ አምላክ፣ አደብ ግዙ የሚል ሌሂቅ መጥፉቱ ነው። አንዳንዱም አገርን መከላከል እየመሰለው አብሮ ሲያጫፍር እና ሹሞቹ ከስህተታቸውም እንዳይታረሙ ዙሪያቸውን ከቦ አይዟችው እያለ የውጪዎቹን ሃይሎች ሲራገም መዋሉ እጅግ ያሳስባል። ማን ነበር 60% የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ልሂቅ አስተሳሰቡ የቀነጨረ ነው የሚል ሳይንሳዊ ጥናት ይፋ ያደረገው? Hmmmmm
እናማ ባጭሩ፤ ኢትዮጵያ ከውስጥ የነቀዘ ፖለቲካ የሚያራምዱ ሹሞች እና የቀነጩሩ ልሂቃን፤ ከውጪ ደግሞ መዳከሟን በሚፈልጉ የግብጽ አይነት ታሪካዊ ጠላት እና በሰብአዊ ቀውስ በሚነግዱ ሃያላን አገራት ተቀስፋ ተይዛለች። ይህ ጊዜ ለኢትዮጰያ እና ለኢትዮጵያውያን እጅግ ፈታኝ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው። እውነተኛ ምሁራን፣ ለአገር ከልብ የሚቆረቆሩ ወገኖች፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች እና በመንግስት ሃላፊነት ላይ የሚገኙ አካላት በአፋጣኝ ቁጭ ብለው ሊመክሩ እና ኢትዮጵያን ከዚህ አደጊ ልትወጣ የምትችልበትን አቅጣጫ ሊቀይሱ ይገባል። የመጣውን አደጋ መንግሥት ብቻውን የቀነጨሩ ሹሞቹን ይዞ የሚወጣው አይመስለኝም።
አገራችንን እንታደግ! ያንጃበበው አደጋ ግን እጅግ ያስፈራል።y