የመለስ የሁልጊዜ ፍርሃት፣ እና የእኛ የሁልጊዜ ፀሎት…!!!
አሰፋ ሀይሉ
መለስ በአንድ ወቅት ከዘመን መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ «በሕይወትህ እንዳይሆን እያልክ የምትፈራው በጣም የሚያሰጋህ ነገር ምንድነው?» በሚል ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹በሕይወቴ ሁሌም የምሰጋው፣ በሕይወት
እያለሁም ሆነ ካለፍኩም በኋላ ምን ይፈጠራል
ብዬ የምጨነቀው፣ በመሪነት ወንበር ላይ
የተቀመጠ አንድ ሰው በሚፈጽማት አንዲት
ስህተት የተነሳ፣ ለዚህ ሁሉ ዓመት የገነባነው
ሥርዓት ድንገት ብትንትኑ ወጥቶ እንዳይፈርስ
እያልኩ ነው የምፈራው፣ ሁሌም፣ ይሄ
ብቻ ነው የሁልጊዜ ብቸኛ ስጋቴ!››
የመለስ ስጋት የገነባው ሥርዓተ ባንዲት ቀጭን ስህተት ብትንትኑ የሚወጣ ረጋ-ሰራሽ ሥርዓት እንደሆነ እንደሚያውቅ ያመለክታል፡፡ የሁልጊዜ ፍርሃቱም ድንገት ያቺን አንዲት ስህተት የሚሠራት ሰው በመሪነት ወንበር ላይ እንዳይቀመጥና፣ ባንዲት ስህተት የገነባው የጎሳ አፓርታይድ እንዳይፈርስ ነበር!
በጣም የሚገርመው ነገር – ስለ ኢትዮጵያችን አስከፊ ሥርዓት ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ – ሁልጊዜ እንቅልፍ አጥቼ ጭምር የማውጠነጥነው – ያ መለስ የፈራው ይህን አፓርታይዳዊ የጋርዮሽ ሥርዓት ብትንትኑን የሚያወጣው ተግባር ምን እንደሆነ ለማወቅ ነው፡፡ በምህንድስና ጥበብና በወታደራዊ ሳይንስ ‹‹ዘ ቡልስ አይ›› (የበሬ ግንባር) የሚሉት – አንድ ትልቅ ግንባታን አንዲት ለህንጻው መቆም እጅግ አስፈላጊ የሆነች ቦታ ላይ መትተው ለማፍረስ የሚጠቀሙበት ረቂቅ «ማዕከላዊ የስበት ሥፍራ» ቀመር አለ፡፡
እስካሁን ያንን ዓይነቱን ይህን መለስ ዜናዊ ተክሎብን ያለፈውን አስከፊ ኋላቀር ሥርዓት ወገብ ዛላውን ብሎ ብትንትኑን የሚያወጣው አንድ ወሳኝ ስስ ብልቱ ምኑ ላይ ነው ያለው? የሚለውን ወሳኝ ዒላማ ለማግኘት ለዓመታት ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ያንን የአፓርታይዳዊውን ሥርዓት የበሬ ግንባር ለማግኘት በዙሪያው እሽከረከራለሁ፡፡ በትክክል ልደርስበት ግን አልቻልኩም፡፡ አንድ ቀን የኢህአዴግ ተረኞች ስህተት መፈጸም ሳያስፈልጋቸው፣ ያንን ነጥብ እንዳገኘው ወይም ሌላ ኢትዮጵያዊ እንዲያገኘው ፈጣሪ እንዲገልጽልኝ (እንዲገልጽልን) አጥብቄ እጸልያለሁ፡፡
አንድ ቀን አንድ ፈጣሪ ዘይቱን የቀባው የተባረከ ኢትዮጵያዊ ያንን ሁነኛ የመርዝ ማርከሻ መድሃኒት ያገኘውና፣ ይሄን የጠነዛ አፓርታይዳዊ ሥርዓት ብትንቱን ማውጣት ይቻለን ይሆናል፡፡ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር የምመኘውና፣ ባለመሆኑ የምቆጭበት ብቸኛ ነገር ይህ ነው፡፡ ግንቦት አልፎ ግንቦት በተተካ ቁጥር – ጎልያድን በአንዲት ጠጠር የዘረረ ልዑል እግዚአብሔር – ይሄንን ከናዚዎች የተረፈ አፓርታይዳዊ ቆሻሻ ሥርዓት በአንዲት እርምጃ ገርስሰን የምንጥልበትን ጥበብና ልብ ይስጠን እያልኩ እፀልያለሁ፡፡
ፈጣሪ ከዚህ የመለስ ዜናዊ አፓርታይዳዊ ሥርዓት በቃችሁ ይበለን፡፡
ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ መሐል – አንዲት ፍቱን ጠጠርን ያነገበ ኢትዮጵያዊ ዳዊትን ያስነሳልን የኢትዮጵያ አምላክ፡፡
ኢትዮጵያ ከተተከለባት መርዝ ተፈውሳ፣ ለዘለዓለም ትኑር!