>
5:26 pm - Thursday September 15, 4489

ባልደራስ ምርጫ ቦርድ ላይ የአፈጻጸም ክስ ሊመሰርት ነው...!!! (መታሰቢያ ካሳዬ)

ባልደራስ ምርጫ ቦርድ ላይ የአፈጻጸም ክስ ሊመሰርት ነው…!!!

መታሰቢያ ካሳዬ

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንዲፈጽም  ክስ ሊመሰርት መሆኑን አስታውቋል።
ባልደራስ በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች ለመጪው ምርጫ እንዲወዳደሩ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቢያቀርብም ቦርዱ “በእስር ላይ ያሉ አመራሮችና አባላትን እጩ ተወዳዳሪ አድርጌ አልመዘግብም” በማለቱ ፓርቲው ለፍ/ቤት አቤቱታ ማቅረቡ ይታወሳል። ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቶ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ፓርቲው ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ወስዶት የሰበር ችሎት ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ምርጫ ቦርድ በእስር ላይ የሚገኙትን የፓርቲውን አመራሮች በእጩነት ሊመዘግብ ይገባል የሚል ውሳኔ ሰጥቷል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎም ምርጫ ቦርድ ለእጩ ምዝገባ የተሰጠው የጊዜ ገደብ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም የተጠናቀቀ በመሆኑና እያንዳንዱ እጩ ተወዳዳሪ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖረውን ስፍራ የሚወስን ሎተሪ እጣ በመውጣቱና የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ህትመትም ተጠናቆ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የመላኩ ተግባር በቅርቡ የሚጀመር በመሆኑ እንደ ውሳኔው ለመፈጸም እቸገራለሁ ሲል ምላሽ ሰጥቷል። ይህንኑ የምርጫ ቦርዱን ምላሽ ተከትሎ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በቦርዱ ላይ የአፈጻፀም ክስ እንደሚመሰርት አስታውቋል።
ቦርዱ እንዴትም አድርጎ ቢሆን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባ ያለከተው ፓርቲው፤ ቀድሞውንም ያለአግባብ የዜጎችን ህገ-መንግስታዊ መብት የጣሰ ተግባር ነው የፈፀመው። ይህ ደግሞ ፈፅሞ  ተቀባይነት  ሊኖረው አይገባም ብሏል።

Filed in: Amharic