>

ህወሓትና የሶማሌ ህዝብ ...!!! (ሙክታሮቪች) 

ህወሓትና የሶማሌ ህዝብ …!!!

(ሙክታሮቪች) 

ህወሓት የሶማሌን ህዝብ በተለየ መልኩ እንደጠቀመች፣ እንደው አንዳንዶች ካድሬዎች ሰው ያደረግናችሁ እኛ ነን የሚሉት ነገር ያቅለሸልሸኛል። የሶማሌ ህዝብን አፍነው፣ ገድለው፣ አስረው፣ አሰቃይተው፣ ሞራሉን ሰብረው ያዋረዱት ህወሓቶች ናቸው።
ህወሓት የምትለው ክልል ሰጠናችሁ፣ በቋንቋችሁና በባህላችሁ መተዳደር አስጀመርናችሁ አይነት ሰራን የምትለው ነገርን ቋቅ የሚያደርገን እኛ ነን “የፈጠርናችሁ” አይነት መታበይና ትምክህት የሚመስል የድንቁርና ትዕቢት የደንቆሮ ስራ አድርገን ስለምናየው ነው።
የህወሓት ታጋዮችም ሆነ የመጡበት ህዝብ ከሶማሌ ህዝብ እና ከሶማሌ ታጋዮች አንፃር ስናያቸው እዚህ ግባ የሚያስብል የዘመናዊነት ልዩነት የለም።
ከወያኔ እንቅስቃሴ በፊት የሶማሌ ህዝብ በንጉሱ እና በስርዓቱ ላይ ነቅቶ ለለውጥ ማመፁን አያውቁም።
በ1956 የመሬት ለአራሹን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጥያቄ ለንጉሱ በፅሁፍ ያቀረቡት ሶማሌው ዶክተር አብደልመጂድ ሁሴን ነበሩ።
ያኔ እነ መለስ ዜናዊ የኢሊመንተሪ ተማሪ ነበሩ። ዋለልኝ ያንፅሁፍ ከመፃፉ በፊት በእስርቤት በኦጋዴን አመፅ የታሰሩ የሶማሌ ልጆችን አናግሮ ነበረ። (ባህሩ ዘውዴ በቅርቡ The quest for Socialist Utopia ባሉት የተማሪዎች ንቅናቄን የሚተርክ መፅሃፋቸው ላይ በግልፅ ይህን ሀቅ አስፍረውታል)
የተለየ ህዝባችን ያልታገለበት ነገር አልመጣም። የመጣው እንደውም ውርደት እና መሰቃየት፣ መደፈር እና ከአውሬ ጋር መታሰር ነው።
ልማት አመጣን ይሉሃል ልማት የታቀደለትን የሰው ልጅ ደፍጥጠው። ህልም ገድለው። ምናብ ገድለው። ከሰው በታች አድርገው። በጅምላ መቃብር ቀብረው።
ህወሓት ለሶማሌ ህዝብ የተለየ ነገር አላደረገችም፣ አሳነሰችብን እንጂ! በዘመኑ ለራሷ ስልጣን ስትል በቋንቋና ጎሳ ሀገር ስትሸነሽን የሶማሌ ክልልም በዚሁ መንገድ መጣ እንጂ ለእኛ የተለየ ተግባር ፈፅማ አይደለም። በዘመኑ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ክፍል ህዝቦች በራሳቸው ባህልና ቋንቋ መተዳደር፣ በራሳቸው ተወካዮች መመራት የዘመኑ የፖለቲካ ቅኝት፣ አጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ ይተገበር የነበረ የሰው ልጆች መብት ላቅ ያለ ትኩረት ያገኘበት ዘመን ነበረ።
የሶማሌ ህዝብም ይህን የታሪክ አጋጣሚ ነው ወደ ህዝቡ የመጣው።
ከህወሓት ሌላ መንግስት ቢመጣም ይህ የዘመናት የማንነት ጥያቄያችንን ሳይመልስ አይረጋጋም ነበረ።
ይህ ሲመጣ ግን ለሶማሌ ህዝብ ልክ እንደ ትግራይ ህዝብ እኩልነትም አልመጣለትም። በመንገድ ሽፋን፣ በትምህርትቤቶች ሽፋን፣ በጤና ሽፋን ቢታይ ከትግራይ የበለጠ ህዝብ ይዘን እጅግ ያነሰ እና የመነመነ የመሰረተ ልማት ሽፋን ነው የነበረው በክልሉ።
ይህ ልዩነት በቀላሉ የሚታይ፣ ከደርግና ሀይለስላሴ እየተነፃፀረ የሚሞካሽ መሆን የለበትም። ሌላው የኢትዮጵያ ክልል በለማበት መጠን የሶማሌ ክልል ያልለማው ህወሓት ለክልሉ የሚበጀተውን በእጅ አዙር እየተቀበለች የክልሉን ህዝብ ስለበደለች ነው።
እንግዲህ የህወሓት ስራን በክልሉ ውስጥ የሰራችውን ግፍ እና ለምን አሁንም የሶማሌ ህዝብ ጉዳይ እንደሚያክለፈልፋት ደጋግመን እንፅፋለን። ለውጡ ከቂምና ከጥላቻ ይፅዳ ብለን ዝም ብንል ጭራሽ የካድሬዎቿን ድንፋታ ስናይ በጣም የሚያስገርም ነው።
ህወሓት በክልላችን በፈፀመችው ወንጀል አለማቀፍ ፍርድቤት መገተር የሚገባት የአፍሪካ ናዚ መሆን ነበረባት።
Filed in: Amharic