>

የታሪክ ሌባው ኦሮሙማ (ጌጥዬ ያለው)

የታሪክ ሌባው ኦሮሙማ

ጌጥዬ ያለው

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ‹አዲስ አበባ› የሚለው ስያሜ ገሸሽ እየተደረገ ይመስላል፡፡ በኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት እና በኦሮሞ የፅንፈኛ ፖለቲከኞች ሁሉ ስያሜው ከብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ እና ከባለቤታቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር ተያይዞ በጥላቻ እየተገፋ ይገኛል፡፡ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራው የአዲስ አበባ የወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎችን ማስዋብ ፕሮጀክት ‹አዲስ አበባ› ከሚለው ስያሜ ይልቅ ‹ሸገርን ማስዋብ› በሚል እየተጠራ ነው፡፡ በከተማው አስተዳድር የሚመራው የ‹ሸገር ዳቦ› ፕሮጀክትና የ‹ሸገር ዘይት› ፕሮጀክትም ይጠቀሳሉ፡፡ የአዲስ አበባ ብዙሃን መገናኛ ድርጅትን ‹ሸገር ሚዲያ ኔትወርክ› ወደ ሚል ስያሜ ለመቀየር ታስቦ እንደነበርም ከድርጅቱ የውስጥ ምንጮች የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተቋሙ ጋዜጠኞችና ሌሎች ሰራተኞች ተቃውሞ ይሄኛው ስያሜ ቀርቶ ‹አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ› ወደ ሚል መቀየሩም ግልፅ ነው፡፡ ‹ሸገር› የሚባል ከተማ በሕግ አይታወቅም፡፡ ከተማችን በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀው አዲስ አበባ በሚል ነው፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ስያሜ ከየት አመጡት? ሸገር ምን ማለት ነው?
ዶክተር ሐብታሙ ተገኘ  ‹በራራ-ቀዳሚት አዲስ አበባ› በተሰኘው ጥናታዊ መፅሐፋቸው ሸገር፤ ሸጋ አገር ማለት ነው ይላሉ፡፡ መፅሐፉ በማጣቀሻነት የተጠቀመው ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሸዋ ይኖር የነበረው ፈረንሳያዊ ነጋዴ መፍሐፍ ነው፡፡ ፈረንሳያዊው ዡል ቦሬሊ ይባላል፡፡ በ1880ዎቹ በአዲሱ እንጦጦ ለሦስት ዓመታት ኖሯል፡፡ እንጦጦን አማራዎች ‹ሸገር ጨነቅ› ይሉት እንደነበር ፅፏል፡፡ እንደ ዶክተር ሐብታሙ ጥናት ይህ ሸገር ስለተባለው የቦታ ስያሜ በፅሁፍ የተገኘ የመጀመሪያው ሰነድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዡል ቦሬሊ ሸገር ጨነቅ ስለተባለው ቃል ትርጓሜ አልሰጠም፡፡ በአማርኛ የስርዎ ቃላት ትንታኔ ‹ሸገር› ሥር መሰረቱ ‹ሠገረ› ነው፡፡ የፅንሰ ሃሳቡ ትርጓሜም በመነሻና በመድረሻ መካከል ያለን ቦታ ማለፍን ወይም መዝነቅን የሚገልፅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹ጨነቅ› የሚለው ቃል መጨናነቅ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህም በደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት መሰረት መጠጋጋት ወይም መቀራረብ ከሚለው ትርጓሜ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ በእንጦጦ ሲከትሙ ቀደምት ነገስታት የነበሩበት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡  በመሆኑም ዳዋ ለብሶ የነበረውን አካባቢ እንደ አዲስ በማደራጀት ሰዎች እንዲሰፍሩበት አድርገዋል፡፡ በዚህ ወቅት ምድረ በዳ የነበረው አካባቢ ላይ ሰዎች ተጠጋግተው መኖር ጀመሩ፡፡ በመሆኑም ሰዎች አካባቢውን ሸገር ጨነቅ አሉት የሚል ነው እውነተኛ የታሪክ ትንታኔው፡፡
በሌላ በኩል የማሕበረሰብ የቃላት ፍች ትንታኔ (folk etymology) የቃሉን አመጣጥ ከሌላ ማዕዘን ሊያመላክት እንደሚችል ከላይ የተጠቀሰው መፅሐፍ ያብራራል፡፡ ለአብነትም ከ‹እግዜአብሔር› እግዚሔር፣ ‹ከደጅ አዝማች› ደጃማች/ደጃች የተሰኙ ቃላት በማሳጠር እንደተፈጠሩት ሁሉ ‹ሸገርም› ሸጋ አገር ከሚለው ሀረግ የመጣ እንደሆነ ይተነትናል፡፡
ከታሪካዊ ማስረጃው መረዳት የሚቻለው ሸገር ይባል የነበረው እንጦጦና አካባቢው ማለትም ዛሬ ድል በር እየተባለ የሚጠራው አካባቢ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሸገር የሚባል ከተማ አልፎ አልፎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአራዳ ቋንቋ ተደርጎ ከመጠቀሱ ውጭ  አይታወቅም፡፡ ይሁን እንጂ ስያሜውን እንደ ኦሮምኛ ቃል የሚረዱት የኦሮሞ ፅንፈኛ ፖለቲከኞችም አሉ፡፡ አብይ አሕመድ ከፕሮቶኮል ውጭ በሆነ መንገድ ይህንን በሕግም ሆነ በታሪክ እውቅና የሌለውን ስያሜ ለምን እንደሚጠቀሙ ግልፅ አይደለም፡፡ ‹ሸገርን ማስዋብ› ላሉት ፕሮጀክት ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደሚደረግም ይፋ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ጎሰም ያለ ገንዘብ የሚወጣበት ፕሮጅክት እንኳንስ ስያሜው ሌሎች ዝርዝር ነገሮችም በማያሻማ መልኩ መጠቀስ ይገባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተናገሩት የማደናገሩ ፕሮጀክት አንዱ ክፍል አድርገን ልንወስደው እንገደዳለን፡፡
ሌላኛው የታሪክ ሽሚያውና የወረራው መነሻ አዲስ አበባን ‹ፊንፊኔ› እያሉ የመጥራቱ አባዜ ነው፡፡ ይህም ከአማርኛ እና ከአማራ ለማራቅ የሚደረግ ጥረት ሲሆን በተመሳሳይ ቃሉን የኦሮምኛ ፍች ያለው አስመስለው በስህተት የዋጡት የኦሮሞ ብሔርተኞች በርካታ ናቸው፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ብሔርተኝነት አቀንቃኞችን የሚከተለው ጨዋው የኦሮሞ ሕዝብ እውነት መስሎት እየተቀበለው ነው፡፡ የታሪክም ሆነ የቋንቋ ሀቆች የሚያሳዩት ግን የአማርኛ ቃል መሆኑን ነው፡፡ እርሱም ከቤተ መግሥቱ ግርጌ የሚገኘው እና ፍል ውሃ የተባለውን መንደር ብቻ የሚወክል እንጂ አዲስ አበባን ከኬንተሪ እስከ ጣፎ፣ ከድል በር እስከ አቃቂ የሚወክል አይደለም፡፡ ከጠመንጃ ያዥ እስከ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ከምኒልክ አደባባይ እስከ በቅሎ ቤት፣ ከቦሌ ሚካኤል እስከ የካ ሚካኤል፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ምኒልክ አደባባይ የሚያጠቃልል አይደለም፡፡
‹ፊንፊኔ› የሚባለው እስከ ብዙ ዘመን ድረስ የአቦ ጠበል ሲባል የቆየ ነው፡፡ እንደ ዛሬው ፍል ውሃ ለሚጠቀመው ሕዝብ መከላከያና መጠለያ ቤት የሌለው ስለነበረ ውሃው ወደ ላይ ፊን ፊን ሲል ይታይ ነበር፡፡ ስያሜውን ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የሰጡት ከዚህ እሳቤ እንደሆነ ታሪክ ያወሳል፡፡ ቃሉ መሰረት ወይም ስርዎ ቃል ‹ፈነ› የሚል የሚል ነው፡፡ ቃሉ አማርኛ ቋንቋ ከተፈጠረ ጀምሮ የነበረ እንደሆነም ሊቃውንት ያትታሉ፡፡ ቆየት ያሉ የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ከላይ የተጠቀሰውን ትርጓሜ ሰጥተውታል፡፡ ለምሳሌ የከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‹ፊንፊኔ› የሚለውን ቃል ‹‹ፊን ፊን አለ፣ ውሃ ከመሬት ሲመነጭ ወደ አየር ፊን እያለ ከመሬት ላይ ዘነበ›› በማለት ተርጉሞታል፡፡  ደስታ ተክለ ወልድ እና ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ደግሞ በተመሳሳይ ‹ፊን ፊን አለ፣ ፊን አደረገ ፈነነ› ብለው ተርጉመውታል፡፡ በቅርቡ የታተመው የቶማስ ኬን የአማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ደስታ ተክለ ወልድ እና ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ከሰጡት ትርጓሜ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡  ሌሎች የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ይህንኑ ፍች በተመሳሳይ አፅንተውታል፡፡
በአንፃሩ በኦሮምኛ መዝገበ ቃላት ‹ፊንፊኔ› የሚል ቃል አይገኝም፡፡ የቦታ ስም ከሆነ በኋላም በኦሮምኛ መዝገበ ቃላት ሰፍሮ አይገኝም፡፡ ለምሳሌ ኢ. ሲ. ፉት በፃፈው የኦሮምኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ‹ፊንፊኔ› የሚል ቃል አይገኝም፡፡ ዮሀንስ ክራፕፍ በፃፈው የኦሮምኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ላይም በተመሳሳይ ቃሉ አይገኝም፡፡ ይህ ሰው ፍል ውሃ ድረስ ሄዶ ቦታውንም አይቷል፡፡ ስለዚህ ቃሉ በቋንቋው ውስጥ ቢገኝ ኖሮ ከዚህ ፀሐፊ መዝገበ ቃላት ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል መገመት አያሳስትም፡፡ ‹ፊንፊኔ› የኦሮምኛ ቃል ቢሆን ኖሮ ከዮሀንስ ክራፕፍ መዝገበ ቃላት ሊያመልጥ እንደማመይችል በራራ- ቀዳሚት አዲስ አበባ የተሰኘው መፅሐፍ ተንትኗል፡፡
ከተዘረዘሩት በተጨማሪ በ1945 ዓ.ም.  ሎውሮንስ ቱሽክ ያሳተመው የኦሮምኛ መዝገበ ቃላት፣ የካቶሊክ ወንጌላዊው እንድሪያስ ጃሮሶ በ1939 ዓ.ም. እንዲሁም በ2004 ዓ.ም. ጥላሁን ገምታ ባሳተመው የኦሮምኛ – እንግሊዝ መዝገበ ቃላት ላይም ቃሉ አይገኝም፡፡
በመሆኑም ‹ሸገር›ም ሆነ ‹ፊንፊኔ› የተባሉት ስሞች ሕጋዊ መሰረት የላቸውም፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ውስጥም አይገኙም፡፡ ይልቁንም በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ የማያሻማ እና ወጥ ትርጉም አላቸው፡፡ ይህ የተሳሳተ የታሪክ ትርክት ሁለቱን ቋንቋዎች በቅርበት ለሚያውቅ ሰው ይበልጥ ግልፅ እየሆነ የሚመጣ ሀቅ ነው፡፡ አዲሱ የቁቤ ትውልድም ይህንን ሀቅ መረዳት ይጠበቅበታል፡፡
ይህንን የታሪክ ሽሚያ ኦሕዴድ/ብልፅግና ከተማዋን ለመውረር፤ መውረር ካልቻለም ለማጥፋት እየተጠቀመበት እንደሆነ ደግሞ የአቶ ሽመልስ ንግግር የማያሻማ ምስክር ነው፡፡ የከተማዋን የሕዝብ ስብጥር መቀየሩ፣ ለኑሮም ሆነ ለሥራ የማትመች ማለትም የማትረባ ከተማ ማድረጉም ከላይ ከተገለፀው ማደናገሪያ ጋር የሚዳበሉ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባን ብሎም የኢትዮጵያን ቅርሶች እየመረጡ ማጥፋቱም የዚሁ አካል ነው ማለት ይቻላል፡፡
             የፈረሱ ቅርሶች
የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በ2003 ዓ.ም. እና በ2009 ዓ.ም ባደረገው ጥናት መሰረት በአዲስ አበባ ውስጥ በከተማዋ መሪ ፕላን የተካተቱ 440 በቅርስነት የተመዘገቡ ታሪካዊ ቤቶችና ሕዝባዊ ተቋማት አሉ፡፡ 33 አብያተ ክርስቲያናት፣ 2 መስጊዶች፣ 1 ታሪካዊ ድልድይ እና 10 ታሪካዊ ሀውልቶችም በከተማዋ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በቅርስነት ተመዝግበው በመሪ ፕላኑ ውስጥ ያልተካተቱ ደግሞ 135 ጥንታዊ ቤቶች አሉ፡፡ ይህ ሕወሓት/ኢህአዴግ ለራሱ አገዛዝ እንዲመቸው አድርጎ ያስጠናው ሲሆን የቅርሶች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ እንደሚል ይገመታል፡፡ ታዲያ ከእነዚህ ቅርሶች መካከል ጠቅላይ አብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከፊሎቹን መንግሥት አፍርሷቸዋል፡፡ ለአብነትም አድዋ ድልድይ አካባቢ የሚገኘው የራስ አበባ አረጋይ ቤት ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ ከዘጠና ዓመት በላይ ያስቆጠረው የልዑል ራስ ካሳ ልጅ የፊታውራሪ አምዴ አበራ መኖሪያ ቤት በከፊል ፈርሷል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎችም ለመከላከል ባደረጉት ጥረት በከፊል ተርፏል፡፡  የፊደል ገበታ አዘጋጅ የተስፋ ገብረ ስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ መኖሪያ ቤትና ማተሚያ ቤት የነበረውም ከፈረሱት መካከል ይጠቀሳል፡፡ ይህ ቤት ከመቶ አመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የለገሀሩ ቡፌ ዲላገር ፈርሷል፡፡ ኤግል ሂልስ ለተባለ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያ ሕንፃ እንዲገነባበት ያለጨረታ ተሰጥቷል፡፡ ይህ ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው ሌሎች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተጫራቾችን አግልለው ለአረብ ወዳጆቻቸው የሰጡት ነው፡፡ በነገራችን ላይ አብይ አሕመድ ለአረብ ሀገራት ያላቸው ሽክርና ወይም አገልጋነት የእናት ሀገራቸውን ቀዳዳ ለመሸፈን ደፋ ቀና ከሚሉት የኩይትና የኦማን እህቶቻች ቢልቅ እንጂ አያንስም፡፡ ልዩነቱ የፕሮቶኮል ነው፡፡ የኩይቷ እህቴም ‹ማዳም› ያዘዘቻትን ትፈፅማለች፤ አብይ አሕመድም ከሳውዲው ንጉስ የታዘዙትን ያደርጋሉ፡፡ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት ከቱርኩ የረሲፕጣይፕ ኤርዶጋን ፓርቲ የምርጫ ምልክት ጋር ፍፁም አንድ አይነት መሆኑን እያንሰላሰልን ወደ መዲናችን ቅርሶች እንመለስ፡-
 አዲስ አበባ የሚገኘውን ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ለማፍረስ ቢሞከርም ለጊዜው በሕዝብ ተቃውሞ ተርፏል፡፡ ሰይጣን ቤት የተባለው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲኒማ ቤትም እንዲሁ በባልደራስ እና በሌሎች አካላት ጥረት ከመፍረስ ተርፏል፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሐን ዘ ኢትዮጵያ መታሰቢያ ሀውልት በቆረቆሯት ከተማ አዲስ አበባ ላይ እንዳይሠራ ተከልክሏል፡፡ ሐረር ከተማ ውስጥ ከወራት በፊት የራስ መኮንን ሐውልት ፈርሷል፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ ደግሞ ጎሬ ከተማ አደባባይ ላይ የአቡነ ሚካኤል ሀውልት እንዳይቆም ተከልክሏል፡፡ ይህ ሐውልት ከተማዋን ከሁለት ከፍሎ ወደ መቱ እና ወደ ጋምቤላ የሚያልፈው አውራ ጎዳና አደባባይ ላይ እንዲቆም ነበር በከተማዋ ኗሪዎች የታሰበው፡፡ ሆኖም የወቅቱ የኦሕዴግ ካድሬዎች በመከልከላቸው ለከተማዋ የታሰበው የመታሰቢያ ሀውልታቸው በእዚያው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ አቡነ ሚካኤል የጣሊያን ወራሪ ኃይል በኢልባቡር በኩል ለመግባት ሲሞክር ፊት ለፊት ተዋግተው ሳምቤ ላይ ድል ያደረጉ የኃይማኖት መሪ ነበሩ፡፡ ታሪካቸው እምብዛም ጎልቶ ባይታወቅም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሁሉ ባዕዳን ወራሪዎችን ያሳፈሩ ቆራጥ አባት ናቸው፡፡ አካባቢውን ከሌሎች አርበኞች ጋር በመሆን ከወራሪ ታድገው  ሀገር ከእነ ክብሯ አስቀጠሉ፡፡ እሳቸው ባስቀጠሏት ሀገር የኦሕዴግ ካድሬዎችም ባለሥልጣን፤ አዛዥ ሆኑ፡፡ ከአመታት በኋላ ግን የእሳቸውን ታሪክ ከመዘከርና ከማመስገን ይልቅ ዘር ቆጥረው ሃውልታቸው እንዳይቆም ከለከሉ፡፡ የአቡነ ሚካኤል ሀውልት በቦታው እንዳይቆም ዋነኛው ምክንያታቸው አማራና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጠልነታቸው ነው፡፡ አቡኑ ጎንደር፤ ደብረ ታቦር ነው የተወለዱት፡፡ አማራ ነኝ ብለው ግን የኢልባቡርን ሕዝብ ለወራሪ አሳልፈው አልሰጡም፤ ፊት ለፊት ተጋፍጠው ከመገዛት አዳኑት እንጂ፤
በወቅቱ በአማራና በኦሮሚያ በኩል ጠንካራ ሕዝባዊ አመፆች ይነሱበት የነበረው  ኢሕአዴግ ማለትም ሕወሓት ኢሕአዴግ መሰል ጥፋቶችን ያቀነባብር እንደነበርም በግልፅ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ በተለይም የብአዴን እና የኦሕዴድ አመራሮች የውስጥ ለውስጥ ስውር ትግል ያደርጉበት እንደነበር ሲያውቅ ይህንን እንደ ማስፈራሪያም በግልፅ ይናገረው ነበር፡፡  በ2003 ዓ.ም. ባስጠናው ጥናት  መሰረት በቅርስነት የዘረዘራቸውን ታሪካዊ ቤቶች፣ ድልድዮች እና ቤተ ክርስቲያናት ሁሉ የኦሮምኛ ስም እየሰጠ ሊቀይራቸው እንደሚችልም በመግለጫ አስፈራርቷል፡፡ ይህ የሕወሓት መግለጫ ከማስፈራሪያነት በዘለለ እውን ሊሆን እንደሚችልም መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም  የሥልጣን ጊዜውን ለማራዘም ሲል በዙሪያው ያሉትን ሁሉ እርስ በእርስ ማጋጨት ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የአኖሌ ሀውልትን ገንብቷል፡፡ ምክንያቱም የኦሮሚያ ‹ክልል›ን ዋና ከተማ ከናዝሬት አንስቶ ወደ አዲስ አበባ ቀይሯል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ከሞት አላዳነውም፡፡ ወደ መጣበት በረሃ ተመልሷል፡፡ በሽብርም ተፈርጇል፡፡
በአዲስ አበባ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት አጠገብ የሚገኘው የደጃዝማት አስፋው ከበደ ቤት የነበረ ቅርስ በኦሕዴድ/ብልፅግና ፈርሷል፡፡ በምትኩም የኦሕዴድ  ወታደራዊ ካምፕ እንደሚሠራበት ተነግሯል፡፡ ታሪክ እያጠፉ የወታደር ጎጆ መቀለስ ሀገር አውዳሚነት ነው፡፡ ፀረ ኢትዮጵዊነት ነው፡፡
ከተረኝነት ወደ ወራሪነት የተቀየረው የአብይ አሕመድ ኦነጋዊ አገዛዝ የትፋት ክንዱን ከቤተ መንግሥት እስከ ቀበሌ አፈርጥሟል፡፡ ለዘመናት የዘለቀውን የሀገረ መንሥት መገለጫ፤ አንበሳ ምንነቷ በማትታወቅ ወፍ ዘራሽ ወፍ ቀይሮታል፡፡ ኦሕዴድ/ብልፅግናን ጨምሮ የኦሮሞ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ‹አዲስ አበባ ኬኛ› ከሚሉት ያልተናነሰ ‹አድዋ ኬኛ› ማለት ጀምረዋል፡፡ የዘንድሮው የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ የተከበረው አብይ አሕመድ ከጀግኖች አርበኞች ለመስተካከል እየተንጠራሩ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በከተማዋ እየተደረገ ያለው የአድዋ ሙዚየም ግንባታም ታሪክ ሰርዞ ምኞት ለመፃፍ ያለመ ነው፡፡
Filed in: Amharic