ይህቺ የኢህአዴግ ሰዓት . . . !!!
አሰፋ ሀይሉ
ይህቺ የኢህአዴግ ሰዓት በ1983 ዓ.ም. ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ልጆች አድምቶና በየሜዳው ለአሞራ አስበልቶ፣ ኤርትራን አስገንጥሎ፣ አንቱ የተባሉ የሀገሪቱን ምሁራን ከዩኒቨርሲቲዎች አባርሮ፣ ሀገሬን ብለው ለሀገራቸው የሰሩና የለፉ ዜጎችን ከነቤተሰቦቻቸው ሜዳ ላይ በትኖ፣ ሲጠላውና ‹‹ጠላት›› እያለ ሲወጋው የኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹መንግሥት›› ሆኖ ሊያስተዳድር ሥልጣን ላይ ሲወጣ – መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው እያለች መቁጠሯን ጀመረች፤
ይህቺ የኢህአዴግ ሰዓት በ1987 ዓ.ም. ኢህአዴግ ኢትዮጵያን እንደ ዶሮ ብልት ገነጣጥሎ፣ ዜጎቿን በዘርና ቋንቋ የሚሸነሽን ህገመንግሥት አውጆ የሀገርን ምንነትና ትርጉም ሲያፋልስ፣ ኢትዮጵያዊነትን ሲቀብር፣ ኢትዮጵያን የመበታተን የቆየ ህልሙን ሲዘራ – መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው እያለች ትቆጥር ነበር፤
ይህቺ የኢህአዴግ ሰዓት በ1997 ዓ.ም. ኢህአዴ ሀገራዊ ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ በጀመረው የዕቃ-ዕቃ ጨዋታ፣ ሳያስበው ተበልቶ፣ ያን ዕቃ-ዕቃውን ለማፍረስ በሺኅዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በስናይፐር ደረትና ጭንቅላታቸውን እየፈጠረቀ በያደባባዩ ሲገድል፣ ወጣቶችን በየመንገዱ ሲረሽን፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሲያስርና ሲገርፍ – መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው እያለች ትቆጥር ነበር፤
ይህቺ የኢህአዴግ ሰዓት በ2009 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሶስት አሰርት ዓመታት ግፍ የወለደው ብሶት ተቀጣጥሎ ይህን ፋሺስታዊ አፓርታይዳዊ የኢህአዴግ ሥርዓት ለመጣል – ከወያኔ መፈልፈያ ቀዬ ከትግራይ በስተቀር – በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ በሁሉም ማዕዘናት በሥርዓቱ ላይ ቆርጠው ሲነሱ፣ ሥርዓቱን ከሥሩ መንግለው ለመጣል ሲጋደሉና ነፍሳቸውን ሲቀሙ፣ ሲደሙ፣ በየእሰርቤቱ ሲጋዙ፣ አካላቸውን ሲገዘገዙ፣ ያለፍርድ ሲረሸኑ፣ ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ – በመጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው እያለች ትቆጥር ነበር፤
ይህች የኢህአዴግ ሰዓት ዛሬ በግንቦት 2013 ዓ.ም. ላይ – የኢህአዴግን አፓርታይዳዊ የፋሺስት አገዛዝ ብልጽግና በሚል አዲስ የዳቦ ስም ቀይረን፣ ህዝቡን አታልለንና ሰንገን፣ ያነገብነውን ጠብመንጃ ደግነን፣ ያበቃለትንና ህዝብን ሰላሳ ዓመት ሙሉ ከዓመት ዓመት ወደ ውድቀቱና ወደመከራው፣ ወደ ዝቅታውና ወደ ውርደቱ፣ ወደ ደም ባህሩና ወደ መከራ አዘቅቱ የመራውን ሥርዓት በአዲስ መልክ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለው የተነሱ ሰብዓዊ አሳሞች – ሥልጣኑን የሙጥኝ ብለው – ከነአጫፋሪዎቻቸው ኢህአዴጋዊ አገዛዛቸውን በቀጠሉበት፣ የኢትዮጵያ ህዝብም ከመከራ ብዛት ሀሞቱ ፈስሶ እንደ አጋፋሪ እንደሻው ‹‹ሞት በደረሰበት አያድርሰኝ›› ብሎ ጀግንነትን የሚረከብ ክንድ በሀገር ምድሩ በጠፋበት በዚህ በአሁኗ ቅጽበት – መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው እያለች እየቆጠረች ነው፤
ህይወት ያላት ንብ በተሰባሪ አምፖል ተቀይራለች፤ ከመነሻው ጠብመንጃ ተኩሰው የኢህአዴግን አፓርታይዳዊ የዘር አገዛዝ በምድራችን ያነገሱት የናዚው ኢህአዴግ ድርጅት መሥራቾች ግንባራቸው ተቦድሶና በየጫካው የቀበሮ ጉድጓዶች ውስጥ መሽገው፣ ከእነርሱ ሥርዓቱን በአደራ የተረከቡት ሥልጣንና ንዋይ የተጠሙ ተጠባባቂ ናዚዎች የኢህአዴግን ሥርዓት ከነዘረኛ መንበሮቹ ተረክበዋል፤ ሥርዓቱ አሁንም አለ፤ የሥርዓቱ ሠዓት መቁጠሩን አያቆምም፤ የሠዓቱ ባትሪ እየተቀየረ፤ እየታደሰ፤ አዳዲስ ማጭበርበሪያና አዳዲስ ህዝብን ከፋፍሎ የመግዢያ፤ የማንበርከኪያ ስልቶችን እያራገበ፤ ዕድሜውን መቁጠሩን ቀጥሏል!
የናዚን ሰዓት ያቆመው የማያወላዳ ነፃነትን የሚወዱ የሰው ልጆች ተጋድሎ ነው፡፡ አፓርታይድን ያቆመው የማያወላዳ የሰው ልጅ እኩልነትንና ነጻነትን የተጠሙ የሰው ልጆች ቆራጥ ተጋድሎ ነው፡፡ ፋሺዝምን ከነመሪዎቹ ጠራርጎ ያጠፋው ነጻነትን የተጠማ የሰው ልጅ ቆራጥ ፍልሚያና ተጋድሎ ብቻ ነው፡፡ በደምና በዘር ቆጠራ የራሱን ነገዳዊ ዘረኛ ገዢነት በመቶ ሚሊየን ሕዝብ ላይ ያሰፈነ አፓርታይዳዊ፣ ናዚያዊ፣ ፋሺስታዊ ሥርዓት የሚገረሰሰው ነጻነትን በሚወዱ፣ ሀገርን በሚያፈቅሩ፣ ዘረኝነትን በሚጸየፉ፣ እኩልነትንና ሰብዓዊነትን በተጠሙ ዜጎች ቆራጥ ተጋድሎና ፍልሚያ ብቻ ነው፡፡ አለዚያ የአፓርታይዳዊው አገዛዝ ንቦች፣ በአምፖል እየተተኩ፣ አምፖሎች ደግሞ ገና በችግኞችና በዛፎች እየተተካኩ፣ ኢህአዴጋዊው የመከራ ጉዞ ገና ይቀጥላል!
«Nulla servitus turpior est quam voluntaria»! «No slavery is more disgraceful than that which is self-imposed»! «በፈቃድ ከመጣ ባርነት የበለጠ የሚያሳፍር የለም»!
ነጻነትን ለአፍሪካውያን በፈነጠቀች ሀገር፣ አፓርታይዳዊ ዘረኛና አፋኝ ፋሺስታዊ ሥርዓት ተቀብሎ አሜን ብሎ መኖር ያሳፍራል! ፈጣሪ ከዚህ በፈቃድ ከተወዘትንበት ውርደትና መከራ ያውጣን!