>

ከዲፕሎማሲያዊ ግትርነት ወጥቶ የማለዘብ ፓሊሲ... !!! (ሔቨን ዮሐንስ)

ከዲፕሎማሲያዊ ግትርነት ወጥቶ የማለዘብ ፓሊሲ… !!!

 
ሔቨን ዮሐንስ

የአሜሪካ ማዕቀብ መጣል ባለስልጣናት ላይ ብቻ የሚቆም የሚመስላቸው አሉ፤ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የመንግስትን አካላት የችግሩን ግዝፈት የተረዱት አልመሰለኝም። ተጨማሪ ማዕቀብ እንዳይጣልብን መስራት ያስፈልጋል። የተጣለው ማዕቀብ እንኳን ለማስነሳት ብዙ ጊዜ እንደሚያስፈልገው መዘንጋት የለበትም። ነገሩን በደንብ ሳይረዱ አካኪ ዘራፍነቱ አያዋጣም።
እንደ አገር የውስጥ ስንጥቃችን ሰፊ ነው። የውስጥ ችግራችንን ተጠቅመው ለከፋ ችግር እንዳይዳርጉን የውስጥ ችግሮችን መፍታት እና ለጊዜው በጋራ ጉዳይ ላይ ማለትም #ብሔራዊ_ክብራችን አሳልፎ ባለመስጠት እና #በብሔራዊ_ጥቅማችን አለመደራደር ያስፈልጋል! #ከሶሪያ እንማር። የሶሪያ ችግር በጣም ትንሽ የሚባል ቢሆንም ያችን የውስጥ ችግር አስፍተው አባላቸው ዛሬ አገሬ ሀብቴ የሚሉት የላቸውም። አገራችን ስትኖር የምንጣላበት አናጣም። አገራችን ከሌለች እኛም የምንጣላበትም አይኖርም።
ስለዚህ የውስጥ ችግርን በአግባቡ መፍታት የግድ ነው። አሜሪካን ለማስደሰት ሳይሆን አገራችን ከገባችበት ቅርቃር ለማውጣት #ብሄራዊ_መግባባት የግድ ነው። መንግስት ዲፕሎማሲውንም መፈተሽ አለበት። እውነት እኔ ጋር ናት የሚል ብሂል አሸናፊ አያደርግም። ዓለም በሃሳባውያን (idealism) አትመራም። ተጨባጫዊነት/እውናዊነት ያለው ፖሊሲ ማድረግ ይጠይቃል። የውስጥ ችግር እና ተጋላጭነት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ፣ ቀጣናዊ ባላንጣችን ዲፕሎማሲያዊ ከበባ ከማድረግ አልፋ ወታደራዊ ልምምድ አጠገባችን በምታደርግበት ሰዓት፣ አንድ አገር እንኳን ከአጠገባችን ሳይሰለፍ፣ እኛም በእውር ድንብር ደመነፍሳዊ አካሄድ የግደለሽነት እየሄድን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳሉት አበው #የምዕራባውያን_የዲፕሎማሲ ጫና ተጨምሮበት አሁንም ከእውናዊው አለም መራቅ የትም አያደርሰንምና ቆም ብለን አሰላለፋችንን እንፈትሽ።
ከዲፕሎማሲያዊ ግትርነት ወጥቶ የማለዘብ ፖሊሲ፣ conspiracy ማድረግ፣ አጋርነትን ማስፋት፣ የውስጥ ችግርን ቅድሚያ ሰጥቶ ለመፍታት መሞከር ለነገ የማይባል ነው። የውስጥ ችግሮቻችንን ከፈታን ሌላው እዳው ገብስ ነው። የእኛ ስብራት ከጠገንን ሌላውን በጋራ ለመስራት ብዙም አንቸገርም፤ ለጠላትም መጠቀሚያ አንሆንም። ስለዚህ ዛሬ ነገ ሳይባል #አገራዊ_መግባባት ላይ ስራ ይሰራ።
አገራዊ መግባባት
የበለፀጉ አገሮች የአገራዊ መግባባት ውጤት ናቸው ለማለት የሚያስረዱ ብዙ አብነቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአንጻሩ፣ በድህነት ውስጥ የሚዳክሩ እና መረጋጋት ያልሰፈነባቸው አገሮች የአገራዊ የጋራ መግባባትን አጀንዳ ከግቡ ያላደርሱና ያልተጠቀሙበት ተብለው እንደሚጠቀሱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ አገራችን የሚመራው ገዥው ፓርቲ የጋራ መግባባትን ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራበት በአጭር ጊዜ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ውጤት ለማምጣት ስራን በአግባብ መስራት እንጂ አገራዊ መግባባት #በፕሮፖጋንዳ ጋጋታ ሊመጣ ይችላል ማለት ዘበት ነው፤ ምክንያቱም አገራዊ መግባባት መሰረቱ እውነት እንጅ ውሽት ሊሆን አይችልምና፡፡
አንዱን እያገለገሉ፣ ሌላውን እያብጠለጠሉ፣ ገሚሱን እየፈጁ፣ ብዙሀን አቤቱታ እና እይታ ጆሮ ዳባ ልበስ እያሉ መጠነ ሰፊ የወጣት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ መሞከር ለህውሃትም አልጠቀምና የተሻለ በመስራት ውጤት በማስመዝገብ አገርን ማሰዳግና ህዝብን ማስደሰት ይቻላል፡፡ አሁን ያሉት ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ወርቃማ እድሎችን በጥንቃቄ በመጠቀም ትልቅ ታሪክ መስራት ይቻላል፡፡
ስሜትን መፍጠር ሳይቻል፣ የወጡት ውጥኖችን በተገቢው ሁኔታ በመተግበር መሞከር አለባብስው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ብለው አበው እንደሚተርቱት ተረት ነው የሚሆነው፡፡ ገዥው ፓርቲ አገራዊ መግባባትን በተመለከተ በደንብ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ትናንት የህውሃት የተንሽዋረረ እይታን የተነሳ፣ አገራችን ብዙ ሳትጠቀም ቀርታለች፡፡ አገራዊ መግባባት ከሌለ #ፍርሃትና #ጥርጣሬ ይነግሳል፡፡ ብዙሃኑ አንገቱን ደፍቶ ይኖራል፤ ጥቂቶች ደግሞ የአገሪቱን ሀብትና ንብረት እንደ ግል ንብረታቸው ቆጥረው የሚንፈላሰፉበት ሥረዓት የአገሪቱ መለያ ይሆናል፡፡ ለአገሩ የሚቆረቆሩ ወደ ጎን ይገፋሉ፤ ብዙዎች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ጫና ይፈጠርባቸዋል፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ነው የአገራችን የተማረና የሰለጠነ የሰው ሀይል አገሩን ጥሎ የሚሰደደው በእንደዚህ አይነት ምክንያት መሆኑ የህውሃት ዘመን አሰራር ምስክር ነው፡፡
አገራዊ መግባባት ባልሰፈነበት ሥርዓት የተሻለ ህይወት መፍጠር የሚችለው ሌት ተቀን በመልፋት ሣይሆን፣ ሌት ተቀን በማጎብደድና በመቅጠፍ ይሆናል፡፡ የጋራ መግባባት ከፕሮፖጋንዳ እና ከዘመቻ ርብርቦሽ ጋር የተለያየ ነው፡፡ ደርግ በዘመቻ ችግኝ ይተክላል፤ በዘመቻ ለጦር ስንቅ እንዲዘጋጅ ያደርግ ነበር፡፡ የጽዳት ዘመቻ በተደጋጋሚ እንዲካሄድ ያደርግ የነበረ ሲሆን፣ በዘመቻ የድጋፍ ሠልፎች እንዲካሄድ ያስገድድም ነበር፡፡ አሁንም እንደ ደርግ በግዳጅ የዘመቻ ልማት ይኑረን ሳይሆን የጋራ ተቋማት፣ የጋራ የስራ መድረኮች እና መሰል የጋራ መድረኮች ለጋራ መግባባት ጥሩ እድል ይፈጥራሉና ይታሰብበት ለማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ #አገራዊ_መግባባት ከመንግስት የሚሰጥ መና ሣይሆን፣ ሁሉም ዜጋ እና ተቋማት በተስማሙበት ስልት ደረጃ በደርጃ የሚመጣ አጀንዳ ነው፡፡ ይሁን እንጅ መንግስት አንድ የጋራ #የኢኮኖሚ ማህበርሰብ በመገንባት እንደሚሰራ በተደጋጋሚ እየገለጸ ቢገኝም፣ ይህም ቢሆን አገራዊ መግባባት ከሌለበት ሥርዓት ለማስፈን ከቶም አይታሰብምና ጊዜ ሳይሰጥ ቢሰራበት እንደ አገርም ያስከብራል።
Filed in: Amharic