“የኢህአዴግ ቀይ እስኪርቢቶ…!!!”
ርዕዮት አለሙ
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 10 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል ርእዮት አለሙ ትጠቀሳለች፡፡ ርእዮት ባህር ማዶ ከመሄድዋ በፊት የኢህአዴግን አገዛዝ በመቃወም ብዙ ጽፋለች፡፡ አሳትማለችም ፡፡ በሚድያ ዘርፍ ርእዮት ታሪኳ የሚዘከር ሲሆን እንዲያነቡት ተጋብዘዋል፡፡
በስለት የተገኘች
ርዕዮት አለሙ በ1972 አ.ም ናዝሬት(አዳማ) ከእናቷ ከወ/ሮ አሰለፈች ተክለማርያምና ከአባቷ አቶ አለሙ ጎቤቦ ተወለደች።ለወላጆቿ በስለት የተገኘች የመጀመርያ ልጅ ነች።አየነው አለሙ የተሰኘ ወንድምና እስከዳር አለሙ የተሰኘች እህት አላት።ወላጆቿ በተቻላቸው ሁሉ የልጆቻቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚታትሩ መካከለኛ የሚባል የኑሮ ደረጃ የነበራቸው ናቸው።በመሆኑም ለልጅ የሚገባውን ፍቅርና እንክብካቤ በአግባቡ አግኝታ አድጋለች።
ኑ እስቲ ዜና ላንብብላችሁ
በዳኝነት ስራ ላይ በነበሩት የአባቷ የስራ ዝውውር ምክንያት ቤተሰቡ ኑሮውን ከናዝሬት አዲስ አበባ አድርጎ የነበረ በመሆኑ አንደኛ ክፍልን የተማረችው ቄራ በሚገኘው ያሬድ ትምህርት ቤት ነበር።በአመቱ ወደ ናዝሬት ተመልሰው መኖር ስለጀመሩ ናዝሬት መንፈሰጉባኤ ወይም ቁጥር ሰባት ተብሎ በሚታወቀው ት/ቤት ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተምራለች።በአባቷ ስራ ምክንያት ቤተሰቡ ወደ አርባምንጭ ስለተዛወረም ከአምስተኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል ሼቻ ከተማ በሚገኘው ሀይሌ ደጋጋ ት/ቤት ተማረች።ቤተሰቦቿ እንደገና ወደ ናዝሬት በመመለሳቸው ናዝሬት ቁጥር ሁለት ት/ቤት ስምንተኛ ክፍልን ዘጠኝና አስርን ደግሞ ናዝሬት አፄ ገላውዴዎስ ት/ቤት ተምራለች።ቤተሰቧ እንደገና ወደ አዲስአበባ በመዛወሩ አስራ አንደኛ እና አስራ ሁለተኛ ክፍልን አብዮት ቅርስ ት/ቤት ተምራ አጠናቃለች። ርእዮት አለሙ ገና በልጅነት የሰፈር ልጆችን ሰብሰብ አድርጋ ኑ እስቲ ዜና ላንብብላችሁ ትል እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ኮተቤ መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ በመግባት በሁለገብ መምህርነት በሰርተፊኬት ተመርቃ ላቀ አድገህ የመጀመርያ ደረጃ ት/ቤት ማስተማር ጀመረች።አዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ያስተማረች ሲሆን ከስራዋ ጎን ለጎን ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በማታው ክፍል ጊዜ በመማር በእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ስነ ፅሁፍ በዲፕሎም ተመርቃለች። ከዚያም ትምህርቷን በመቀጠል ከአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ በክረምት መርሀ-ግብር በእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ስነፅሁፍ የመጀመርያ ዲግሪዋን ይዛለች። በተመሳሳይ አመትና ወር በማታው መርሀግብር በትያትር አርትስ ከአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ተመርቃለች።የትያትር አርት የዲግሪ ማሟያ ፅሁፏም ሴት ደራሲያን በድርሰቶቻቸው ውስጥ ሴት ገፀባህርያትን እንዴት እንደሚስሉ ጥናት ያደረገችበት ነበር።ሴቶች በኪነጥበብ ስራዎች ውስጥ ፣በእምነት ስፍራዎች እና በፓለቲካ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምን እንደሚመስል በተለያየ ጊዜ ጥናቶችን በማድረግ ፅሁፎችን ለተለያዩ የህትመት ውጤቶች አቅርባለች።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዲግሪዋን ከያዘች በኋላ ቀጨኔ ደብረሰላም መድሀኒአለም የዘጠነኛና አስረኛ ክፍል ተማሪዎችን አስተምራለች።
“የኢህአዴግ ቀይ እስኪርቢቶ”
ርዕዮት ከማስተማር ስራዋ ጎንለጎን ለተለያዩ ጋዜጦች ፅሁፎቿን እየላከች ይታተሙላት የነበረ ሲሆን የልጅነት ህልሟ ወደነበሩት የጋዜጠኝነት እና የደራሲነት ህይወት ውስጥ ለመግባት ይረዱኛል ብላ የምታስባቸውን መጻሕፍትንም በገፍ ታነብ እና ስልጠናዎችንም ትወስድ ነበር።ያሰበችው ተሳክቶ በፍትህ ጋዜጣ በቋሚ አምደኝነት፣በአዲስፕሬስ ጋዜጣ በአዘጋጅነት እና በኢትዮጵያን ሪቪው ድረገፅ በሪፓርተርነት ሰርታለች።ትፅፋቸው በነበሩት የህወሓት/ኢህአዴግን አገዛዝ የሚተቹ ፅሁፎች ምክንያት ሰኔ14,2003 አ.ም ለእስር ተዳርጋለች።እንደታሰረች ይቅርታ ጠይቃ እንድትወጣ በተደጋጋሚ በእስር ቤቱ ሀላፊዎችና ከመንግስት ተወክለው በሚመጡ አካላት ብትጠየቅም አሻፈረኝ በማለቷ የተለያዩ ስቃዮችን እየተቀበለች ከአራት አመት በላይ በእስር ቆይታለች።በእስር ላይ ሆናም አገዛዙን የሚሄሱ ፅሁፎችን በድብቅ እያዘጋጀች ታወጣ ነበር።ከመታሰሯ በፊት በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ትፅፋቸው ከነበሩ ፅሁፎች ውስጥ የተወሰኑት ተለይተው “የኢህአዴግ ቀይ እስኪርቢቶ” በሚል ርዕስ በእስር ላይ እያለች ታትመው ለአንባቢ ቀርበዋል። ይህ መጽሀፍ በ210 ገጽ የተሰናዳ ሲሆን በብዙዎችም ለመነበብ የቻለ ነው፡፡ ከአራት አመት እስር በኋላ ለመለቀቋ ምክንያት የነበረው በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ ወደኢትዮጵያ መምጣት ነበር።
“የመጻሕፍት ገበታ” እና “የፀሀፊያን ድምፆች“
ርዕዮት በእስር ላይ እያለች ሽልማትና እውቅና ከሰጧት አለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ የአለም አቀፍ ሴት ጋዜጠኞች ፋውንዴሽን (IWMF)፣ የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት(Human Rights Watch) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት እና የሳይንስ ማዕከል (UNESCO) ይገኙበታል። ከእስር ከወጣች በኋላም በሀገር ውስጥ በቆየችባቸው ጥቂት ወራት መፃፏን እና ቃለመጠይቆችን መስጠቷን ባለማቋረጧ የአገዛዙ ወከባ ተከትሏታል። በተለያዩ የኢትዮጵያውያን እና አለምአቀፍ ተቋማት ግብዣ ወደአሜሪካ የሄደችው ርዕዮት ህክምና ለማግኘትና የጡት ቀዶጥገና ለማድረግም ችላለች።
ከሰርጀሪው በኋላ የጋዜጠኝነት ስራዋን በስደት በመቀጠል በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ባልደረባ በመሆን የተለያዩ ፓለቲካ ተኮር ፕሮግራሞችን ማዘጋጀቱን ቀጠለች።መፅሀፍትን ማንበብ ከልጅነቷ ጀምሮ የተለከፈችበት በመሆኑ ከንባቧ ሌሎችም ይጠቀሙ ዘንድ የምታነባቸውን ለሌሎች የምታካፍልበት ሳምንታዊ ፕሮግራም ዘረጋች። በየሳምንቱ ሀሙስ በርዕዮት እየተዘጋጀ የሚቀርበው “የፀሀፊያን ድምፆች” የተሰኘው ፕሮግራም ኢሳትን እስከለቀቀችበት ጊዜ ድረስ ለ3 አመታት ያህል ሲተላለፍ ቆይቷል። ኢትዮ 360 ሚዲያን ከሌሎች ከኢሳት ከለቀቁ ጋዜጠኞች ጋር ከመሰረተች በኋላ ላለፉት ሁለት አመታት መፅሓፍት ላይ የሚያተኩር ፕሮግራም እያዘጋጀች በማቅረብ ላይ ናት። “የመጻሕፍት ገበታ” በተሰኘው በየሳምንቱ ረቡዕ በሚቀርበው በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት የንባብ ባህልን በማበረታታት የራሷን አሻራ በማሳረፍ ላይ ትገኛለች።በዚህ ፕሮግራም ጀማሪና አንጋፋ ፀሀፊዎችና ደራሲያን እየቀረቡ ስራዎቻቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።ርዕዮት ላለፋት አምስት አመታት የሰራችውን መፅሀፍት ላይ የሚያተኩረውን ፕሮግራሟን አጠናቅራ የመቀጠል እቅድ አላት።እንደ ድልድይ በመሆን የሀገር ቤት እና የዲያስፓራ ፀሀፊዎችንና አንባቢዎችን ማገናኘት አንዱ የፕሮግራሟ አላማ መሆኑን ትገልፃለች።
ርዕዮት በፕሮግራሟ በምታቀርባቸው እንግዶች የትምህርትና የሙያ ልምድ ብዙ እየተማረች ስለመሆኗም ትናገራለች።
ርዕዮት በስደት በምትኖርበት አሜሪካ ሆናም የጋዜጠኝነት ሙያዋን ለማሻሻል የተለያዩ ስልጠናዎችን የወሰደች ሲሆን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይም በበጎ ፍቃደኝነት የተለያዩ ተሳትፎዎችን ታደርጋለች። ርእዮት የተለያዩ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ ያደረገች ሲሆን ከእነዚህም መሀል አለምጸሀይ ወዳጆ ፤ በላይነህ አቡኔ እና ዶክተር ገበየሁ ተፈሪ ይገኙበታል፡፡ ካመነችበት ነገር ጋር ጸንታ የምትቆመው ርእዮት አለሙ የኢትዮጵያን ታሪክ አውቃ ለማሳወቅ የተቻላትን ታደርጋለች፡፡ ወደፊት ሁኔታዎች ሲመቻቹ ደግሞ ከአሁን በላይ አቅሟን ጨምራ የመስራት ህልም አላት፡፡