ሥልጣን ያሳበደው አረመኔ ማንነት ሲረጋገጥ
ከይኄይስ እውነቱ
ኢትዮጵያ እንደ አገር ሕዝቧም እንደ ዜጋ ሉዐላዊነታቸው አደጋ ላይ የወደቀው ቀድሞ በሕወሓት አሁን ደግሞ በኦሕዴድ የሚመራው ኢሕአዴግ የተባለው አጋንንታዊ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነ ጊዜ ነው እንጂ ደኸ አገርና ሕዝብ ሉዐላዊነት የላቸውም የሚለው እጅግ የድንቁርናና የስንፍና ንግግር ነው፡፡
እንደኔ እምነት ኢትዮጵያ ከኃያላኑ አገራት (ከአውሮጳም ሆነ ከአሜሪቃ) የምትፈልገው ርጥባንና ብድር ሳይሆን (ላለፉት 30 ዓመታት የጎረፈው ተአምር በሠራ ነበር) ጠላቶቻችንን (የውስጡንም ሆነ የውጩን) እንዳይደግፉብን እና ድክመታችንን እንዳያጠናክሩብን ብቻ ነው፡፡ ይህን ቢያደርጉልን ከርጥባኑ እጅግ የላቀ ውለታ በዋሉልን ነበር፡፡
ትናንት ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ላይ አንድ ያልገረመኝ ሆኖም ሰበር የሚባል ዜና ከኢትዮ-360 ሜዲያ አደመጥሁ፡፡ እነ ሀብታሙ ‹‹ዛሬ ምን አለ?›› የሚለው ዕለታዊ ዝግጅታቸው እንደጀመረ ስለ ዜናው ከሌላ ሜዲያ መስማታቸውን ቢነግሩንም በመሀል በድብቅ እንደወጣ የተነገረውን፣ በድምጽ የተቀረፀውን እና ራስን የመውደድ ለከት የሌለውን የአረመኔውን (selfish beast) ዐቢይ ንግግር አሰሙን፡፡ በአረመኔው ዐቢይ ፊታውራሪነት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሠራ ያለ ኦሕዴድ/ብል(ጽ)ግና የተባለ ድርጅቱ ገና ከጅምሩ ስለተጨናገፈው ሐሰተኛ ምርጫ ሲያወራ የተበላ ዕቁብ ስለመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ውስብስብ ችግር በምርጫ የሚፈታ አለመሆኑን፣ ይልቁንም በሕዝብ የተባበረ ጫና አገዛዙ ወደ ውይይት እንዲመጣ አስገድዶ እምቢም ካለ አስወግዶ በቅድሚያ የአገርን ህልውና እና በመላ አገሪቱ በዐቢይ የኦሮሙማ ኃይሎች ፍጅት እየተፈጸመበት፣ ቤት ንብረቱ እየተዘረፈበት ያለውን፣ አገርህ አይደለም እየተባለ በሚሊዮን የሚፈናቀለውንና ለከፍተኛ ረሃብ የተጋለጠውን ሕዝባችንን መታደግ፤ ሲቀጥልም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት አገራዊ ጉባኤ ተደርጎ ብሔራዊ መግባባት፣ ብሔራዊ ዕርቅ፣ እውነት ነጥሮ የሚወጣበት የሽግግር ፍትሕ እና የሽግግር ሥርዓት እንዲመሠረት እኔን ጨምሮ በውስጥም በውጭም የምንገኝ የአገራቸን ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሣን ኢትዮጵያውያን ደጋግመን ስንወተውት ቈይተናል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ታሪካዊት አገር ዘረኝነት በተጣባቸውና የበታችነት ስሜት እጅጉን በሚያሰቃያቸው ድውያን እና በዱርዬ ጎረምሶች እጅ ወድቃለች፡፡ ሕዝብ የቸራቸውን የፖለቲካ ጥሪት ቅርጥፍ አድርገው በልተው ከጨረሱና ከሕዝቡ ጋር ሆድና ጀርባ ከሆኑ በኋላ በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ዋና ችግር አገዛዙና እሱም የፈጠረው ምስቅልቅል መሆኑን ለመሸፈን የማያዋጣ የ‹ሉዐላዊነት› ካርድ መዘው ካድሬዎቻቸውን ዐደባባይ ወጥተው እንዲጮኹ አድርገዋል፡፡ የማይጠቅም ከንቱ ጩኸት፡፡ ይህንን ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይታዘባል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሕዝቧም እንደ ዜጋ ሉዐላዊነታቸው አደጋ ላይ የወደቀው ቀድሞ በሕወሓት አሁን ደግሞ በኦሕዴድ የሚመራው ኢሕአዴግ የተባለው አጋንንታዊ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነ ጊዜ ነው እንጂ ደኸ አገርና ሕዝብ ሉዐላዊነት የላቸውም የሚለው እጅግ የድንቁርናና የስንፍና ንግግር ነው፡፡ የውጩ ተጽእኖ (የምዕራቡም ሆነ የምሥራቁ እንዲሁም የዐረቡ ዓለም) በእኛ ጥበባዊ አያያዝ፣ በበሰለ አመራር እና ላገርና ለሕዝብ ባለን ፍቅር መጠን የሚወሰን በመሆኑ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ እንደኔ እምነት ኢትዮጵያ ከኃያላኑ አገራት (ከአውሮጳም ሆነ ከአሜሪቃ) የምትፈልገው ርጥባንና ብድር ሳይሆን (ላለፉት 30 ዓመታት የጎረፈው ተአምር በሠራ ነበር) ጠላቶቻችንን (የውስጡንም ሆነ የውጩን) እንዳይደግፉብን እና ድክመታችንን እንዳያጠናክሩብን ብቻ ነው፡፡ ይህን ቢያደርጉልን ከርጥባኑ እጅግ የላቀ ውለታ በዋሉልን ነበር፡፡ ጐሣና ሃይማኖትን መሠረት ያላደረገ የእኩልነት ሥርዓት መፍጠር ከቻልን ሌላው እዳው ገብስ ነበር፡፡ ሠርቶ ለመለወጥ የሚያስችለን የሕዝብ እና የተፈጥሮ ሀብት በእጃችን ነው፡፡
ይሁን እንጂ በሥልጣን ስካር ናላው የዞረው አረመኔው ዐቢይና በኢትዮጵያ ጥላቻ ዐቅላቸውን የሳቱት የኦሮሙማ ኩባንያ አባላት በመላ ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሽብር በማስፋፋት በሥልጣን ላይ ለመቈየትና ኢትዮጵያን የማፍረስ ዘመቻቸውን ከፍጻሜ ለማድረስ በኅቡዕና በገሃድ በተግባር ሲተረጕሙ የነበረ አፍራሽ ዕቅዳቸውን አሁን በአረመኔው ዐቢይ በኩል በይፋ ማኅተም አሳርፈውበታል፡፡ በድምጽ የሰማነው ንግግር ትክክል አይደለም ቢባል እንኳ ያለፉት ሦስት ዓመታት ተግባርና ንግግር አሁን እግዚአብሔርን ሳይፈሩና ሰውን ሳያፍሩ በዐደባባይ የወጡበት ንግግር ሃሳባቸውና ፍላጎታቸው መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በድምጽ የተላለፈው የንግግር ክፍል ቃል በቃል ከዚህ በታች ተመልክቷል፡፡
‹‹በዚህ ምርጫ በኛ በኩል በተወሰነ ደረጃ ብልሽት እንዳይኖር ጥረት ይደረጋል፡፡ እንደምታውቁት ምርጫው እንዲራዘም ፍላጎት የነበረው ዋነኛው ፓርቲ ብልጽግና ነው የነበረው፡፡ በብዙ ምክንያት በጥቅሉ ኮሮና ባይመጣ ኖሮና ምርጫ ቢደረግ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ያስቸግራል፡፡ አሁን ደግሞ ምርጫውን አለማድረጉ መልሶ ከነበረው ሁኔታ የዘቀጠ ነገር እንዳይፈጠር ምርጫን እንደ አንድ አማራጭ እንወስዳለን፡፡ እንደምታውቁት ፖለቲከኛ የሚባለው ኃይል አክቲቪስትን ጨምሮ ሥልጣን ለመያዝ ነው እሚሠራው፡፡ ስለዚህ የኛ ካድሬዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ትናንሽ እሚባል ስህተት ትናንሽ እሚባል ጥፋት በየዕለቱ ገምግመን ማረም መቻል አለብን፡፡ አንድ ፋውል አደገኛ ነው፡፡ እሚያስፈራኝ ጉዳይ በዚህ ምርጫ ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሜዲያዎች ከምትገምቱት በላይ ብዙ ኃይሎች ከቅርብም ከሩቅም አሉ፡፡ እስከሚቀጥለው 10 ዓመት ድረስ ማንም ሰው መንግሥት መሆን አይችልም፡፡ እሞታለሁ እንጂ ሥልጣን አልሰጥም፡፡ ብዙ ርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ ለዚህ የተዘጋጀው ግብረ ኃይል ሥራውን ጀምሯል፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ የሆነ ፍጅት ደም መፋሰስ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ከወዲሁ ርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ምንም ጥርጣሬም ምሥጢርም የለውም ምርጫውን አሸንፈናል፡፡ በቀላሉ ነው ያሸነፍነው፡፡ በተቻለ መጠን ምርጫውን አጨናግፈን እሚፎካከሩ ኃይሎች ተስፋ እንዲቆርጡ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ ካለፍንባቸው ፈተናዎች አንፃር ይህን ማሳካት ብዙ ከባድ አይደለም፡፡ ይህ ብቸኛው መንገድ እንዳይበላሽ ድርብ ኃላፊነት ወስደን ብናሳካው ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡›› (አጽንዖት በኔ የተጨመረ)
ዘረኛውና አረመኔው ዐቢይ አጽንዖት ያደረግኹበትን ንግግሩን ሲያደርግ ተሰብሳቢዎቹ የጋለ ጭብጨባ ሲያደርጉ ይሰማ ነበር፡፡ አፈርሁ ተሸማቀቅሁ፡፡ ዐቢይና ድውያን የኦሮሙማ ብል(ጽ)ግና አባላቱን ማንነት አጥቼአቸው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ሳስብ፣ ሕዝቧን ሳስብ ውስጤ በእጅጉ ቈሰለ፡፡ ምን ዓይነት መረገም ቢሆን ነው በነዚህ ምናምንቴዎች ላይ የወደቅነው? እንዴት እፍኝ የማይሞሉ ዘረኞች መቶ ኃያ ሚለዮን በሚጠጋ ሕዝብ ላይ በንቀት ይሸኑብናል? ከኢትዮጵያ ምድር እንዴት ሱሪ ታጣቂ ‹ወንድ› ይጥፋ? አንዳንዶች እገሊት ‹ወንድ› ናት፣ እገሌ ‹ወንድ› ነው ሲባል ይሳቀቃሉ፡፡ ለምን? አንበሳ ነው፤አንበሳ ናት እንል የለም እንዴ፡፡ ኢትዮጵያዊ የጀግንነት ይትበሃል እኮ ነው፡፡ ለምን እንሳቀቃለን? ለምን እናፍርበታለን? ለምን ሁሉን ነገር በፈረንጆች ባህል ተገብተን እናስባለን? ይህ ከፆታ እኩልነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ የሚያኮሯት የሴት ነገሥታትና ጀግኖች አርበኞች ነበሯት፡፡ አሁንም በሁሉም መስክ ሴቶች ጀግኖች አሏት፡፡ እንደ አረመኔው ዐቢይ ያሉ አገዛዞች ለባርነት የሚመለምሏቸውን ግን አይመለከትም፡፡
ለማጠቃለል ከንግግሩ መካከል አንድ ሁለት አባባሎችን በመምዘዝ በጨረፍታ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ በቅድሚያ ‹እሞታለሁ እንጂ ሥልጣን አልሰጥም› የሚለው ነው፡፡ በርእሰ መጽሐፉ አባባል ‹አንተው አልክ?› እንበለው? ለዚህም ደም መፋሰስን የሚያስከትል ብዙ አረመኔያዊ ርምጃዎች ለመወሰድ መዘጋጀቱንና ግብር ኃይል አቋቋሞ ሥራ መጀመሩን በንግግሩ አሳውቆናል፡፡ ይንንም አድርጎ የሥልጣኑ ጉዳይ ካልተሳካ ግን ፈሪው ዐቢይ ሞትን መርጧል፡፡ የኋለኛውን እንደ ፍላጎቱ ያድርግለት፡፡ መቼም ከሚያሳርዳቸው ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንት ነፍስ የሱ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡
ሌላው ‹‹…ከወዲሁ ርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ምንም ጥርጣሬም ምሥጢርም የለውም ምርጫውን አሸንፈናል፡፡ በቀላሉ ነው ያሸነፍነው፡፡›› ብሎናል፡፡
የተበላ ዕቁብ ማለት እኮ ይሄ ነው፡፡ ታዲያ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ/የአገር ሀብት በምርጫ ማስፈጸም ስም ለምን ይባክናል? ያውም በአገዛዙ ክሹፍነት ምክንያት በተንኮታኮተ ኢኮኖሚ፡፡ ‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ› ለሚባለው እንዳንል እነሱ በኤምባሲዎቻቸውም ሆነ በውስጥ ሰላዮቻቸው አማካይነት ከበቂ በላይ መረጃና ማስረጃ ጭምር እንደሚኖራቸው ይገመታል፡፡ በሞተ ኢኮኖሚ ‹ላለቀ ምርጫ› መተወኛ ተብሎ የሚደርሰው የሀብት ብክነት የአገዛዙ መንግሥታዊ ንቅዘት መገለጫ ከሚባል በቀር ሌላ ትርጕም ለመስጠት ይቸግራል፡፡
የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ይባላል፡፡ የአረመኔው ዐቢይ ንግግር ውስጥ ፍራቻና ዛቻ እንደ ሠምና ፈትል ተጣምተው ይገኛሉ፡፡ ፍራቻ የጨካኞች ዓይነተኛ መለያ ነው፡፡ ያሠማራቸው አሸባሪዎች የእርጉዝ ሆድ ሲመትሩ እና ሕፃናትን በስለት ሲቀሉ ምንም የማይሰቅቃቸው ለዚህ ነው፡፡ ዘረኛው ዐቢይ ሊመጣ ላለው ከፍተኛ የሕዝብ እልቂትና የአገር ውድመት የሦስት ዓመቱን ጊዜ እንደ ቅድሚያ ማሳያ (preview) ሊያለማምደን ሞክሯል፡፡ በ‹ቀላሉ ካሸነፈው ምርጫ› በኋላ ምን እንጠብቅ? በጊዜው ጊዜ እናየዋለን፡፡ ውጤቱ ይቈየንና አሁን ምን ማድረግ አለብን? አስቀድመን ‹ስለበሰበስን› መጪውን ‹ዝናብ› ሳንፈራ፣ ከዝናቡ ጋር የሚመጣው ነጐድጓድ ሳያስደነግጠን፤ ነፋስ፣ ጎርፍ፣ ወጀብ በየቤታችን ደጃፍ መጥቶ ጠራርጎ ሳይወስደን በፊት እያንዳንዳችን በተናጥልና በኅብረት ራሳችንን እንድንሸክፍ ወንድማዊ ምክሬን ለግሳለሁ፡፡ እኛ (አንድ የጋራ አገር÷ ነገደ ብዙ አንድ ሕዝብ አለን ብለን የምናምን፤ በታሪካችን ጨቋኝና ተጨቋኝ ጐሣ የለም ብለን የምናምን፤ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት የሀገረ-መንግሥትነት ታሪክ አላት ብለን የምንመሰክር፤ በፀረ ፋሺስታዊ እና ፀረ ቅኝ ግዛት ታሪክ ያሸበረቀ የነፃነት ታሪክ ያለን፤ ጭቆናንና ጨቋኝ አገዛዞችን አምርረን የምንጠላ፤ የጐሣ አገዛዝ ሥርዓት ከነ ሕጋዊ መሠረቱና መዋቅሩ ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት አለበት ብለን የምናምን ኢትዮጵያውያን) ክቡርና የተቀደሰ ዓላማ አለን፡፡ አገርና ሕዝብን የመታደግ፡፡ ፍልሚያው የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የ‹ጦርነት› ስኬት ደግሞ ከስንቅና ትጥቁ በላይ የሚሞቱለት በጎ ዓላማ መኖር ይመስለኛል፡፡ ጎበዝ አንዘናጋ!!! አረመኔውን እንወቅበት፡፡