የሚሊዮን ቤቶች ፕሮጀክት !
ባልደራስ. ለእውነተኛ ዴሞክራሲ
የቤት እጦት ከአዲስ አበቤ ግንባር ቀደም ፈተናዎች አንዱ ነው፡፡ ከ76% በላይ የሚሆነው ህዝብ በቀበሌ /በመንግስት ቤት/ እና በግለሰብ ቤት ውስጥ ተከራይቶ የሚኖርና የራሱ መጠለያ የሌለው ነው፡፡ ከግማሽ በላይ ቤቶችም ከዲዛይንና ግንባታቸው ጀምሮ እስከ መሰረተ ልማትና አገልግሎት አቅርቦታቸው ድረስ ከደረጃ በታች የሚባሉ ናቸው፡፡ ከከተማዋ ህዝብ 79 በመቶ የሚሆነው በመናኛ ሰፈሮች ‹‹slum›› ይኖራል፡፡
ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ-ብልፅግና በከተማ ፖሊሲው የሚመፃደቅበት ብቸኛው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ቢከፍቱት ተልባ ነው፡፡ የጥራት መናኛነቱና የኃብት ብክነቱን ፣ ፍትሀዊነት የጎደለው የማስተላለፍ ሥርዓቱን ፣ በተጠያቂነት ማነስና በብልሹ አሰራር መጨማለቁን ሳንዘነጋ በከተማው ሕዝብ የቤት ፍላጎትና በአስተዳደሩ አቅርቦት መካከል ያለውን ርቀት ለማስተናገድ ከ50 ዓመታት በላይ እንደሚወስድ መረዳት ይቻላል። በብልፅግና አስተዳደር ከቀጠልን በመጭዎቹ ዘመናት ወደማይፈታ ማሕበራዊ ቀውስ መሻገራችን አይቀሬ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እስከዛሬ በቤት ልማት ዘርፍ ከታዩ ችግሮችና ስህተቶች ተምሮ ሁለንተናዊ መፍትሄ ለመስጠት ቁርጠኛ ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባን የሁሉምና ለሁሉም የምትመች የማድረግ ራዕዩ ቁልፍ አካል የሆነ ሥርነቀል የመኖሪያ ቤት ልማት ፖሊሲ ይዞ መጥቷል፡፡
✅ ፍትሃዊ የቤት ልማት
ባልደራስ በመኖሪያ ቤት ረገድ ተቀዳሚ ተግባሩ ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ቀድሞ በደርግ መንግስት ቤታቸው አላግባብ የተወረሰባቸውና እጅግ አነስተኛ ካሳ ያገኙ ዜጎች ተመጣጣኝና ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲያገኙ ይደረጋል ።
በተመሳሳይ በወያኔ ዘመን በመልሶ ማልማት ስም የተደረገውን ዜጎችን በግዴለሽነት የማፈናቀልና የመውረስ ግፍ በመኮነን ከከተማው አይን ቦታ አላግባብና ያለፈቃዳቸው የተፈናቀሉና በየጥጋጥጉ የተጣሉ ነዋሪዎች የደረሰባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኪሳራ አስልቶ ተገቢ ካሳ በገንዘብና በአይነት እንዲያገኙ ይደረጋል።
✅ አማራጭ ከተማ ግንባታ
ባልደራስ በመኖሪያ ቤቶች ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን በየጊዜው የሚሰፋ ክፍተት ለማጥበብና በአዲስ አበባ ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር ለመቅረፍ ከተማዋን በአዲስ መልክ መገንባትና ሌሎች አማራጭ ከተሞችን በዙሪያዋ መመስረት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል፡፡
አዲስ አበባን የማደስም ሆነ አማራጭ ከተሞችን የመገንባቱ አቀራረብ ስብስባዊ የከተማ ግንባታ ስልትን (clustered city approach) የሚከተል ሲሆን ፣ ይህም አቀራረብ በስብስቦች መካከል መሰረተ ልማትን በጋራ ለመገልገልና የግንባታ ወጭዎችን ለመቀነስ እንዲሁም አጠቃላይ የሀብት ምንጮቻችንን በውጤታማነትና በቁጠባ ለመጠቀም ያስችለናል፡፡
ይህ ፕሮጄክት አዲስ አበባን በአዲስ መልክ መገንባትን የሚያካትት ሲሆን ፣ ሕዝባዊ ተቀባይነት (public trust) ለፕሮጄክቱ ማስቀመጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ ይሆናል። በዚህ ዜጎች በምንም መልኩ የሚገፉ ሳይሆን የሚጠቀሙ በማድረግ ለትውልድ በሚሻገር ልማቱ ዋነኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያበረታታል።
✅ የሚሊዮን ቤቶች ፕሮጀክት
ባልደራስ ቢመረጥ በከተማው ነዋሪ ፍላጎትና በቤት አቅርቦት መካከል ያለውን ርቀት በማጥበብ የቤትን ችግር ለመቅረፍ በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት ለከተማዋ ነዋሪዎች እንዲገነባ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ሲባል እስካሁን ለቤት ግንባታው ዘርፍ የዋለውንና ከሌሎች ሲነፃፀር ዝቅተኛ የሚባለውን መዋዕለ ንዋይ ከ3 በመቶ ወደ 5 በመቶ ያሳድጋል፡፡
ፓርቲያችን ያቀደው የሚሊዮን ቤቶች ግንባታ በአስተዳደሩ ፣ በማህበራትና በግል ተጠናክሮ ይሰራል፡፡ የግል ባለሀብቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች በሰፊው እንዲሳተፉ ዕገዛ ይደረጋል፡፡ በአስተዳደሩ የሚገነቡ ቤቶች ለሽያጭ ብቻ ሳይሆን በከፊል በተመጣጣኝ የኪራይ ዋጋ እንዲተዳደሩ ይደረጋል፡፡
የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ቤት ሰሪዎች በማኀበር እንዲደራጁ በማድረግ ፣ የባንክ ብድር በማመቻቸት ፣ የግንባታ ግብአት ከቀረጥ ነፃ በመፍቀድ ፣ የግንባታ ቁጥጥር እገዛ በመስጠትና በራሳቸው እንዲያስገነቡ በመፍቀድ ሁሉንም ቤት ፈላጊ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥራት ያለው ኮንዶሚኒየም/አፓርትመንት ባለቤት እናደርጋለን፡፡
ሁልጊዜም ለህዝባችን ቅድሚያ እንሰጣለን! የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችን በየክፍለ ከተማው ባሉን ክፍትና የመልሶ ግንባታ ቦታዎች ላይ እንገነባለን፡፡ ይህ ደግሞ ህዝቡ አላግባብ እንዳይፈናቀልና የመሰረተ ልማት አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኝ ይረዳል፡፡
የመልሶ ማልማት ቦታዎችን 25% ለመኖሪያ ግንባታ ፣ 25% ለንግድ ፣ 25% ለማህበራዊ አገልግሎትና ቀሪው 25% ለአረንጓዴ ቦታ በመከለል የአዲስ አበባ ህዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን፡፡
(ከባልደራስ የአዲስ አበባ ማኒፌስቶ)
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ